የጅማ ዩኒቨርሲቲ በ19 ሚሊዮን ብር የገዛው ህንፃ ካርታ ተሰወረ ተባለ

የጅማ ዩኒቨርሲቲ በኦዲት ግኝቶች ላይ እየወሰደ ያለው የእርምት እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ  ባካሄደው ይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባ ገለጸ፡፡ ይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የዩኒቨርሲቲውን የፋይናንስ ስርዓትና ንብረት አያያዝ አስመልክቶ በ2011 በጀት ዓመት ባካሄደው ኦዲት የተገኙ ግኝቶችን መሠረት ያደረገ ሲሆን ቋሚ ኮሚቴው የዩኒቨርሲቲው አመራሮች ማብራሪያ እንዲሰጡ ዋና ዋና ግኝቶችን አቅርቧል፡፡

<የሲዳማ ክልል ከክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አገኘ>

በዚህም በጥሬ ገንዘብ ብር 34,771.40፣ በተሰብሳቢ ብር 2,184,379.73 እንዲሁም በተከፋይ ብር 34,140,330.65  ያልተለመደ የሂሳብ ሚዛን በመያዝ ወደ 2011 በጀት ዓመት የዞሩ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ ከዚህም ሌላ ለዩኒቨርሲቲው ማስፋፊያ በሚል በጥቅሉ ብር 19,470,100.60 ወጪ የሆነበት የህንፃ ግዥ ቢደረግም ኦዲቱ እስከተከናወነበት ጊዜ ድረስ ዩኒቨርሲቲው የባለቤትነት ካርታ ያልተረከበ መሆኑ፣ በድምሩ ብር 18,982,919.86 ወጪ በማድረግ ለዩኒቨርሲቲው ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሚውሉ የህክምና እቃዎችን ለመግዛት በአለም አቀፍ የጨረታ ዘዴ ግዥ ለመፈጸም ቀደም ብሎ የባንክ “ሌተር ኦፍ ክሬዲት” ተከፍቶ ሂሳቡ በተሰብሳቢ የተያዘ ቢሆንም ንብረቱ ለዩኒቨርስቲው ገቢ ሳይደረግ  ሂሳቡ በወጭ ተመዝግቦ ሪፖርት የተደረገ መሆኑ እንዲሁም አስፈላጊ መረጃ ያልተሟላለት ብር 40,275.00 የሙያ እገዛ ላደረጉ 9 ግለሰቦች በሚል ወጪ ተደርጎ መገኘቱ ተመልክቷል፡፡

እንደዚሁም ለመድሀኒት ግዢ 1,074,300 ወጪ ተደርጎ እያለ  በሞዴል 19 ገቢ የተደረገው መድሀኒት የብር 1,039,510 በመሆኑ ብር 34,790.00 ብልጫ ተከፍሎ መገኘቱ እና በውል የተገባን አገልግሎት ወይም እቃን በወቅቱ ባለማቅረብ ምክንያት በጉዳት ካሳነት መሰብሰብ የነበረበት ብር 192,354.24 በወቅቱ ሳይሰበሰብ መቅረቱ ተጠቅሷል፡፡ በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው በ2010 በጀት ዓመት ለተከናወነ የጽዳት ስራ አገልግሎት ለአንድ የጽዳት አገልግሎት ሰጪ ድርጅት ከከፈለው ሂሳብ በብልጫ ብር 1,492,952.60 በ2011 ዓ.ም የወቅቱ የገበያ ዋጋ ሳይጠና ይሄው ድርጅት ለሰጠው አገልግሎት የተጋነነ ክፍያ ከፍሎ ተገኝቷል፡፡

<ጎጆ ብሪጅ ሃውሲንግ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ከሪል ስቴት በተለየ መልኩ ሊገነባ ነው>

ቋሚ ኮሚቴው የዩኒቨርስቲው አመራሮች በኦዲት ግኝቶቹ ላይ  ማብራሪያ እንዲሰጡ የጠየቀ ሲሆን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ.ር ጀማል አባፊጣና ሌሎች በመድረኩ ላይ የተገኙ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ አመራሮቹ በሰጡት ምላሽም የኦዲት ግኝቶቹ ከ2010 በፊት የነበሩና ሲንከባለሉ የመጡ 6 ግኝቶችን ጨምሮ የ2011 በጀት ዓመት 12  በድምሩ 18 ግኝቶች መሆናቸውን ገልጸው በኦዲት ግኝቱ መሰረት የማስተካከያ መርሀ ግብር ተዘጋጅቶ ለሚመለከታቸው አካላት መላኩን፣ የክትትልና የእርምት እርምጃዎችም እየተወሰዱ መሆኑንና በዚህም መሻሻሎች መታየታቸውን አመላክተዋል፡፡

ትክክለኛ የሂሳብ ሚዛን ሳይጠብቁ ወደ 2011 በጀት ዓመት የዞሩ ሂሳቦችን በተመለከተ ክፍተቱ ከሂሳብ አመዘጋገብ ጋር የተያያዘ መሆኑን የጠቀሱት አመራሮቹ በአሁኑ ወቅት የማስተካከያ እርምጃዎች እየተወሰዱና ችግሩ እየተስተካከለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከሚመለከተው አካል የካርታ ርክክብ ሳይደረግ የህንፃ ግዥ ክፍያ መፈጸሙ ከአሠራር አንፃር ትክክል ያለመሆኑን የጠቀሱት አመራሮቹ ዩኒቨርሲቲው ካለበት የሠራተኞች ከስራ የመልቀቅ ከፍተኛ ችግር አንፃር በተለይም በስፔሻላይዝድ ሆስፒታሉ የሚሰሩና ሌሎች አስፈላጊ ባለሙያዎችን ለማቆየት ሲባል ህንፃው ባለበት ሁኔታ ለባለሙያዎች መኖሪያነትና ለተረኛ ሀኪሞች ማደሪያነት እንዲያገለግል ግዢ መፈፀሙን አስረድተዋል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe