የጉና ተራራ ጥብቅ ስፍራ አደጋ ላይ ነው ተባለ

(አብመድ) የጉና ተራራ ማኅበረሰብ አቀፍ ጥብቅ ሥፍራን በዘላቂነት ለማልማትና ለመጠበቅ የማኅበረሰቡን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል እንደሚገባ ተመራማሪዎች ተናገሩ።

የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ከጉና እስከ ጣና የመስክ የምርምርና የልማት ማዕከል አቋቁሞ እየሠራ ይገኛል። በኢትዮጵያ ከባሕር ጠለል በላይ 3 ሺህ 200 ሜትር እና ከዚያ በላይ ከፍታ ያለው ቦታ 8 ሺህ 677 ኪ.ሜ ይሆናል፤ ከዚህ ውስጥ 210 ኪሎ ሜትሩን የሚሸፍነው የጉና ተራራ ነው።

ጉና ተራራ 30 አካባቢ አጥቢ እንስሳት፣139 የአእዋፍ ዝርያዎች እና በርካታ የእፅዋት ዓይነቶች የሚገኙበት ሥፍራ ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ስድስቱ አጥቢ እንስሳትና 13 የአዕዋፍ ዝርያዎች በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ብርቅዬ ናቸው። ጉና ተራራ ከፍተኛ የውኃ ማማ ከሆኑ የኢትዮጵያ ደጋማ አካባቢዎችም አንዱ ነው፡፡

ይሁን እንጅ የጉና ተራራ አካባቢን በዘላቂነት ማልማትና መጠበቅ ካልተቻለ በርሃማነት እንደሚሰፋና እና ጣና፣ ዓባይ፣ ርብ እና ተከዜ በደለል የመሞላት ዕድላቸው ከፍተኛ መሆኑን ነው ምሁራን የተናገሩት፡፡ ጉናን በጥብቅ ስፍራነት መጠበቅ የእነዚህን ወንዞች ኅልውና መታደግ መሆኑንም ጥናቶች አመላክተዋል።

የጉና ተራራን በዘላቂነት ለማልማት ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመሆን በጥብቅ ስፍራነት እንዲጠበቅ ጥረት አድርጎ በሁለት ዓመታት ውስጥ ጥሩ ሥነ ምኅዳር መፍጠር ተችሎ ነበር። ነገር ግን ጥብቅ ስፍራውን ለማስፋፋት በተደረገ እንቅስቃሴ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር አለመግባባት በመፈጠሩ ጥብቅ ስፍራው ወደ ልቅ ግጦሽነት ተቀይሯል።

በመሆኑም ጥብቅ ሥፍራውን በዘላቂነት ለማስቀጠል ጉና ተራራን ከሚያካልሉ የእሥቴ፣ ላይ ጋይንት፣ ጉና በጌምድር እና ፋርጣ ወረዳዎች ከተውጣጡ የሃይማኖት አባቶችና አመራሮች ጋር በደብረ ታቦር ዩኒቨርስቲ ውይይት ተደርጓል። በውይይቱም ጉና ለደቡብ ጎንደር ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ብሎም ለምሥራቅ አፍሪካ ስላለው ጠቀሜታ በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የጉና ጣና የተቀናጀ የምርምር ማዕከል ተመራማሪ አቶ ኃይሉ ምናለ የውይይት መነሻ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡

ተሳታፊዎችም ‹‹የጉና ተራራ በጥብቅ ስፍራነት ተከብሮ ቢቆይ ለእኛም፣ ለቀጣይ ትውልድም እንደሚጠቅም ተረድተናል፤ ነገር ግን አካባቢው ምርታማ ባለመሆኑ ማኅበረሰቡ የሚተዳደረው በእንስሳት እርባታ ነው። ስለሆነም አማራጭ መፍትሄ ቢፈጠርልንና ቦታው በጥብቅ ስፍራነት ቢጠበቅ›› ብለዋል፡፡ ከዚህ በፊት የተወሰነው የጉና ተራራ ክፍል ሲጠበቅ መንግሥት ለማኅበረሰቡ ‹‹መሠረታዊ ፍላጎት ይሟላላችኋል፣ ለማኅበረሰቡም አምራጭ ሁኔታዎች ሊመቻቹለት ይገባል›› ቢልም ቃሉ ተፈጻሚ አለመሆኑን ነዋሪዎቹ አንስተዋል፡፡ የተገባው ቃል ካለመፈጸሙም ባሻገር ማኅበረሰቡን በስፋት ሳያወያዩ የማስፋፋት ሥራ በመሠራቱ ቦታው ተመልሶ ወደ ልቅ ግጦሽነት እንዲመለስ እንዳደረገውም ነው ተወያዮቹ የተናገሩት፡፡

‹‹አሁን ላይ ጉና እየሞተ በመሆኑ ከሞተበት ለማስነሳት ውይይቱ እስከታች ወርዶ መተማመን ላይ መድረስ አለብን። መድረክ ላይ አውርተን የምንቀር ከሆነ ጉናን መታደግ አንችልም›› የሚል የመፍትሔ ሐሳብም ተወያዮቹ አቅርበዋል። በመንግሥት በኩልም ቦታውን ቁርጠኛ ሁኖ ማስከበሩ ላይ ክፍተት እንዳለ ተጠቁሟል።

የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሲሳይ ዳምጤ ጉና ተራራን በዚህ ሁኔታ ማስቀጠሉ ለማኅበረሰቡ ጠቃሚ ባለመሆኑ በነበረው ክልል ልክ ሊከበር እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የአማራ ክልል የአካባቢ፣ ደንና የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በላይነህ አየለ በጉና ላይ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት በመነጋገር ካልሆነ በመፎካከር ችግሩን መፍታት አይቻልም። ጣና አሁን ላይ እምቦጭ ወርሮታል፤ እምቦጩን መቆጣጠር ካልቻልንባቸው ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ከጉና ተራራ ታጥቦ የሚሄደው አፈር ከፍተኛ ማዕድን ይዞ ስለሚሄድ እምቦጭን የማፋፋት ኃይል ስላለው ነው፤ ስለዚህ ጉናን ጠብቀን ጣናንም መታደግ ይኖርብናል ብለዋል።

የጉና ተራራ የማኅበረሰብ የወል መሬት እንጅ የግለሰብ አይደለም፤ ስለዚህ ካሳ ይከፈለን የሚለው ሐሳብ ትክክል አይደለም፤ ካሳ የሚከፈለው አርሶ አደሩ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ባወጣበት መሬቱ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ማኅበረሰቡ ጥብቅ ስፍራውን እየጠበቀ ከጥብቅ ስፍራው ሳር እያጨደ እንስሳቱን በመቀለብ የተሻሻለ ኑሮ በመኖር የአካባቢውን ሥነ-ምኅዳር ማስጠበቅ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በውይይቱ የክልል እና የዞን ከፍተኛ አመራሮች፣ የባሕር ዳር እና የጎንደር ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች ተሳትፈዋል።

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe