የግማሽ ሚሊዮን ብር ጉቦ ተቀብለዋል ተብለው የተከሰሱት የEBC የኦሮምኛ ዝግጅት ክፍል ሀላፊና ተባባሪ እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ

 በምስል የተደገፈ ጥቆማ ለኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (EBC) የደረሰ በማስመሰልና በማስፈራራት ከውሀ አምራች ባለቤት የግማሽ ሚሊዮን ብር ጉቦ ተቀብለዋል ተብለው የተከሰሱት የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የኦሮምኛ ዝግጅት ክፍል ሀላፊ በላቸው ጀቤሳ እና በግል ሥራ ይተዳደራል የተባለው 2ኛ ተከሳሽ አለማየሁ ቂጥሶ በተከሰሱበት አንቀጽ ላይ እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ።
የዓቃቢህግ ምስክሮችን ቃል መርምሮ በዛሬው የችሎት ቀጠሮ ተከሳሾቹ እንዲከላከሉ ብይኑን የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።
ተከሳሾቹ የወንጀል ህግ አንቀጽ 32(1)ሀ ና አንቀጽ 33 እንዲሁም የሙስና ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 10(1)ሀ እና 2 ን ተላልፈዋል ተብለው በመጋቢት 9 ቀን 2014 ክስ እንደቀረበባቸው ይታወሳል።
የቀረበባቸው የሙስና ወንጀል ክስ ላይ እንደተመላከተው፤ ኩኒስ ጠቅላላ የንግድ ሥራ ድርጅት የሚያመርተው የሸገር ውሀ ባለቤት ዶ/ር ሀሰን መሀመድ ጋር 2ኛ ተከሳሽ ስልክ በመደወል በአዳማ ከተማ ከአንድ ሱቅ የገዛው የሸገር የታሸገ ውሀ ውስጥ ሶፍት መሰል ባዓድ ነገር ቆሻሻ እንዳገኘበት እና ጥቆማ ለEBC መስጠቱን ገልጾ፤ የኦሮምኛ ዝግጅት ክፍል ኃላፊን አናግሩት በማለት የ1ኛ ተከሳሽ ስልክ ቁጥሩን ለባለሀብቱ መስጠቱ በክሱ ተዘርዝሯል።
ዶ/ር ሀሰን መሀመድ በተሰጣቸው ስልክ ቁጥር ለአንደኛ ተከሳሽ በመደወል አ/አ ከተማ ብሔራዊ ቴያትር ቤት አካባቢ ራስ ሆቴል ውስጥ በጥር 27 ቀን በአካል በመገናኘት የEBC የኦሮምኛ ዝግጅት ክፍል ኃላፊ በላቸው ጀቤሳ በምስል የተደገፈ ጥቆማው ለክፍሉ እንደደረሰው ለባለሀብቱ በመግለጽ፤ ነገር ግን ጉዳዩ በሚዲያው እንዳይተላለፍ ከፈለጋችሁ ገንዘብ ክፈሉ በማለት ጉቦ ጠይቋል ሲል ዓቃቢህግ በክሱ አመላክቷል።
በጥር 28 ቀን ደግሞ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ለቡ ጋርመንት አካባቢ በሚገኝ አንድ ካፍቴሪያ ውስጥ ተከሳሾቹ ከውሀ አምራች ባለቤት ጋር በመገናኘት ጥቆማው እንዳይተላለፍ ግማሽ ሚሊዮን ብር ጉቦ እንዲከፍሉ መደራደራቸውን የጠቀሰው ዓቃቢህግ፤ በሌላኛ ቀን ደግሞ በድርድሩ መሰረት 100 ሺህ ብር በጥሬ ቀሪ 400 ሺህ ብር ደግሞ በቼክ ከባለሀብቱ ሲቀበሉ ቀደም ብሎ በደረሰ ጥቆማ ክትትል ሲያደርጉ የነበሩ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አባላት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ከሳሽ ዓቃቢህግ በክሱ ዘርዝሯል።
ተከሳሾቹም ክሱ ግልጽ አደለም ሲሉ እንዲሻሻል የክስ መቃወሚያ ለችሎቱ አቅርበው ነበር።
ክሱ ግልጽ መሆኑን እና የተሳትፎ ደረጃ በዝርዝር መካተቱን ጠቅሶ ዓቃቢህግ መልስ ሰጥቷል። ፍርድ ቤቱ መርምሮ የተከሳሾች ክስ እንዲሻሻልላቸው ያቀረቡት ጥያቄ የህግ አግባብ ያለው ጥያቄ አደለም ሲል ውድቅ አድርጓል።
ተከሳሾቹ ወንጀሉን አልፈጸምንም ሲሉ የሰጠቱን የዕምነት ክህደት ቃል ተከትሎ ከአንድ ወር በፊት ዓቃቢህግ ለወንጀሉ መፈጸም ያስረዱልኛል ያላቸውን ስድስት ምስክሮችን አቅርቦ አሰምቷል።
የምስክር ቃል ያዳመጠው ፍርድ ቤቱ፤ የምስክር ቃል በጽሁፍ ተገልብጦ መርምሮ ብይን ለመስጠት ለዛሬ በሰጠው ተለዋጭ ቀጠሮ መሰረት መርምሮ ተከሳሾቹ በተከሰሱበት አንቀጽ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል።
ተከሳሾች የሚሰሙት የመከላከያ ማስረጃ ካለ ለመጠባበቅ ለሐምሌ 26 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ መሰጠቱን ጋዜጠኛ ታሪክ አዱኛ ዘግባለች።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe