የፀጥታው ምክር ቤት ኢራን በባህረ ሰላጤው አገራት ላይ የምታደርሰውን ጥቃት እንድታቆም አሳሰበ፤ ሩሲያ ውሳኔውን ሚዛናዊ ያልሆነ ብላዋለች
የተመድ ፀጥታው ምክር ቤት በ13 ድምፅ ያፀደቀውና ሩሲያ እና ቻይና ድምፀ ተአቅቦ የመረጡበት ይህ ውሳኔ፣ አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት በዝርዝር አይጠቅስም። በምትኩም፣ ኢራን በባህሬን፣ በኩዌት፣ በኦማን፣ በኳታር፣ በሳዑዲ አረቢያ፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና በዮርዳኖስ ላይ የምታደርሰውን ጥቃት በአስቸኳይ እንድታቆም ይጠይቃል።
📄 ሰነዱ በተጨማሪም ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚካሄደውን ዓለም አቀፍ የባህር ጉዞ ለመዝጋት፣ ለማደናቀፍ ወይም ጣልቃ ለመግባት የምታደርገውን ማንኛውንም እንቅስቃሴ ወይም ዛቻ ያወግዛል።
🔊 በተመድ የኢራን ቋሚ መልዕክተኛ አሚር ሰኢድ ኢራቫኒ ውሳኔውን በመተቸት፣ “አንዳንድ የፀጥታው ምክር ቤት አባላት የተጠቂን እና የአጥቂን ሚና ለመቀያየር እየሞከሩ ነው” ብለዋል። አክለውም፣ ሀገራቸው ይህንን ሰነድ እንደማትቀበለው አስታውቀዋል።
በተመድ የሩሲያ ቋሚ መልዕክተኛ ቫሲሊ ኔቤንዚያ በበኩላቸው፣ ውሳኔውን “እጅግ ሚዛናዊ ያልሆነ ” እና “ዓለም አቀፍ ሰላምንና ስርዓትን ለማስጠበቅ የማይጠቅም” ሰነድ ነው ሲሉ አጣጥለውታል።

