ዓለም አቀፍ ዝናን ያተረፈው ኢትዮጵያዊው የባህላዊ ውዝዋዜ ባለሙያና የፈንድቃ ባህል ማዕከል መስራች መላኩ በላይ፤ ከፈረንሳይ መንግሥት የተበረከተለትን ከፍተኛ የክብር ሜዳሊያ ሽልማት በክብር ተቀብሏል።
አርቲስቱ የፈረንሳይን “ኦፊሴር ዴ ላ ኦርደሬ ዴስ አርትስ እና ዴስ ሌትረስ” (Officier de l’Ordre des Arts et des Lettres) ሜዳሊያ የተቀበለው በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ከሆኑት አሌከስ ላሜክ እጅ ነው።
ይህ የክብር ሜዳሊያ ሽልማት በፈረንሳይ መንግሥት የባህል ሚኒስቴር እ.ኤ..አ በ1957 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን በፈረንሳይና በመላው ዓለም በሥነ-ጥበብና በሥነ-ጽሁፍ ዘርፍ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ግለሰቦች የሚበረከት ከፍተኛ ዕውቅና ነው።
አርቲስቱ ሽልማቱን በማግኘቱ የተሰማውን ጥልቅ ደስታ ገልጾ፣ ሽልማቱ የጋራ ስኬት መሆኑን ተናግሯል፡፡
“ይህ ክብር እኔንና ፈንድቃን ለደገፉን ሁሉ ነው” ያለው አርቲስት መላኩ በላይ፤ በዓለም ዙሪያ ያሉ ታዳሚዎች በፈንድቃ ላይ ላሳዩት እምነት አመስግኗል፡፡
አክሎም፤ “የፈንድቃ ቤተሰብ፣ ጠንክሮ መሥራታችሁና ጥልቅ ፍቅራችሁ ሁሉንም ነገር እውን አድርጎታል። ይህ አዲስ ጅምር ነው። አብረን ታላላቅ ነገሮችን እናደርጋለን!” ሲል መልዕክት አስተላልፏል፡፡(አ.አ)

