“የፍትሕ አካላት የምርመራ ጋዜጠኝነት ሥራን ሊያግዙ እንጂ ሊያደናቅፉ አይገባም!”፦ የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን

የፍትሕ አካላት የምርመራ ጋዜጠኝነት ሥራን ሊያግዙ እንጂ ሊያደናቅፉ አይገባም ሲል የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን አሳሰበ።

ባለስልጣኑ ዛሬ ታሕሳስ 24/2015 ባወጣው መግለጫ፤ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 29 ንዑስ አንቀጽ 2፤ 3/ለ እና 4 እንዲሁም በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 አንቀጽ 48 መሠረት መገናኛ ብዙኃን የሕዝብን ጥቅም የሚመለከት መረጃ የማግኘት መብት እንዳላቸው መገለጹን ጠቁሟል።

ለዲሞክራሲያዊ እና ተጠያቂነት ለሰፈነበት ሥርዓት ግንባታ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን የማግኘትና የመመርመር የአሠራር ነጻነት አልፎ ተርፎም የሕግ ጥበቃ እንደሚደረግላቸውም መደንገጉንም ጨምሮ ገልጿል።

በተጨማሪም፤ የምርመራ ጋዜጠኝነትን ከማበረታታት አንፃርም ከሕጋዊ ማሕቀፎች ባለፈ እንደ መንግሥት አቅጣጫ ተይዞ እንዲሠራ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ማሳሰባቸውን ባለስልጣኑ አስታውሷል።

በመርሕ ደረጃ የዜጎች መብት የተረጋገጠበት የዲሞክራሲ ባህል የሚጎለብትበት እና ተጠያቂነት የሚሰፍንበት ሥርዓት ለመገንባት የፍትሕ አካላት ከመገናኛ ብዙኃን ጋር እጅና ጓንት ሆነው መሥራት እጅግ ጠቃሚ መሆኑንም ጠቁሟል።

ይህ ሊረጋገጥ የሚችለው ደግሞ መገናኛ ብዙኃን ያለምንም መታወክና እንቅፋት ብቁ የምርመራ ጋዜጠኝነት ሥራ መሥራት እንዲችሉ መረጃ የማግኘት፣ የመሰብሰብ፣ የመመርመር እና የማሠራት መብታቸው ከማንም በላይ በፍትሕ አካላት ሲረጋገጥ እና ጥበቃ ሲደረግለት መሆኑን ባለስልጣኑ በመግለጫው አብራርቷል።

ከዚህ በተቃረነ አግባብ የመገናኛ ብዙኃን ባለሞያዎች የምርመራ ጋዜጠኝነት ሥራ ላይ በማንኛውም መንገድ እክል መፍጠር፣ የዜጎች መብትን መደፍጠጥ፣ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ መፍጠር እንዲሁም ተጠያቂነት እንዳይሰፍን ከአጥፊዎች ጋር እንደመተባበር እንደሚቆጠርም ገልጿል፡፡

ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የምርመራ ጋዜጠኝነት ሥራዎች እንዲቆሙ ትዕዛዝ የመስጠት አዝማሚያ እየስተዋለ መምጣቱን ባለስልጣኑ አንስቷል።

የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ለመገናኛ ብዙኃን ሥራ አስቻይ ሁኔታ እንዲፈጠር በሕግ የተጣለበትን ኃላፊነት ከመወጣት አንፃር መገናኛ ብዙኃን በሚያከናውኗቸው የምርመራ ጋዜጠኝነት ሥራዎች ላይ በማንኛውም አካል የሚፈጸም ማዋከብ እንዲቆም በመግለጫው አሳስቧል፡፡

በተለይም የምርመራ ጋዜጠኝነት ሥራ አጋዥና ተዋናይ መሆን የሚጠበቅባቸው የፍትሕ አካላት ለዚህ ሥራ አጋዥ እንጂ እክል እንዳይሆኑም ባለሥልጣኑ ጥሪውን አቅርቧል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe