የዓለም እግር ኳስ ጨዋታን ለመዳኘት ወደ ዩናይትድ ስቴትስ አቅንተው ከአውሮፕላን ማረፊያ ሳይወጡ ወደ መጡበት እንዲመለሱ የተገደዱት ሶማሊያዊው የእግር ኳስ ጨዋታ ዳኛ በሶማሊያ የጀግና አቀባበል ተደረገላቸው ። ዩናይትድ ስቴትስ እንዳይገቡ ባይከለከሉ እና ጨዋታውን ቢዳኙ ኖሮ የእግር ኳስ ጨዋታ ዳኛው ዖማር አብዱልቃድር አርታን የዓለም እግር ኳስ ጨዋታን በመዳኘት ከአገራቸው ሶማሊያ የመጀመሪያው ሰው ይሆኑ ነበር ። ወደ ዩናይትድ ስቴትስ እንዳይገቡ ተገድደው ግን ከሚያሚ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ ባለፈው ቅዳሜ ወደ መጡበት ቱርክ እንዲመለሱ ተገድደዋል ።
የዩናይትድ ስቴትስ የጉምሩክ እና ድንበር ጥበቃ መሥሪያ ቤት ሶማሊያዊው ዳኛን ወደ አገሩ እንዳይገቡ ሲከለክል «ጥልቅ የማጣራት ሒደት» ላይ ነን ከማለት ውጪ ዝርዝር ማብራሪሪያ አለመስጠቱን አሶሺየትድ ፕሬስ የዜና ምንጭ ዘግቧል ። የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበርም (FIFA) በኋላ ላይ ሶማሊያዊው ዳኛን ከዳኞች ዝርዝሩ ውስጥ አንስቷል ። ሮይተርስ የዜና ምን ጭ በበኩሉ፦ የፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ሶማሊያዊው ዳኛን ወደ ዩናይትድ ስቴትስ እንዳይገቡ የከለከለው «ከተጠርጣሪ አሸባሪ ቡድኖች አባላት» ጋር ግንኑኘት አላቸው በሚል ነው ሲል አትቷል ።
የእግር ኳስ ዳኛው ዖማር አብዱልቃድር አርታን ምንም እንኳን ዩናይትድ ስቴትስ እንዳይገቡ ቢከለከሉም፤ አገራቸው ሶማሊያ ሞቃዲሹ አውሮፕላን ማረፊያ ሲገቡ ግን የጀግና አቀባበል እንደተደረገላቸው አሶሺየትድ ፕሬስ የዜና ምንጭ ዘግቧል ። ዩናይትድ ስቴትስ እንዳይገቡ መከልከላቸውን በብርቱ በመተቸት፦ ለሶማሊያ መንግሥት፤ ሕዝብ እና ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበር ላሳዩት ድጋፍ አመስግነዋል ።
የዓለም እግር ኳስ ውድድር ከሦስቱ አዘጋጆቿ አንዷ በሆነችው ሜክሲኮ እና ደቡብ አቀፍሪቃ መካከል ነገ በሚደረገው የመክፈቺያ ግጥሚያ ይጀምራል ። ውድድሮቹ በአዘጋጆቹ ዩናይትድ ስቴትስ እና ካናዳ ውስጥም እየተከናወኑ ለአንድ ወር ያህል ይቆያሉ ።
ዩናይትድ ስቴትስ እንዳይገቡ የተከለከሉት የእግር ኳስ ዳኛ በሶማሊያ የጀግና አቀባበል ተደረገላቸው
SourceDW

