ያለምንም ግጭትና ደም መፋሰስ ዕርቅ በማውረድ ሰላምና አንድነት እንዲመጣ ቅዱስ ሲኖዶስ አሳሰበ

በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ያሉት የግጭት አቅጣጫዎች የሚመስሉ ትንኮሳዎች የኋላ ኋላ ፀፀት እንዳያስከትሉ፣ ሁሉም ወገን ወደ ዕርቅ፣ ወደ ሰላምና አንድነት መምጣት እንዳለበት ቅዱስ ሲኖዶስ አሳሰበ፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ የጥቅምት መደበኛ ጉባዔውን ጥቅምት 12 ቀን 2013 ዓ.ም. ሲጀምር በንግግር የከፈቱት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ፣ የኢትዮጵያን ወቅታዊና አሳሳቢ ሁኔታን በቃኙበት ንግግራቸው፣ ከዚህ ቀደም ያጋጩ ነገሮች ብዙ ማሳጣታቸውን ለማይመለስ ፀፀትም መዳረጋቸውን አስታውሰው፣ አሁንም ተመሳሳይ ስሕተት ላይ እንዳይወደቅ የፈለገውን ያህል ጊዜ ይወስድ፣ የፈለገውን ያህል ዋጋ ያስከፍል፣ ያለ አንዳች ግጭትና ደም መፋሰስ ሁሉም ነገር ወደ ዕርቅ፣ ወደ ሰላምና አንድነት መመጣት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ጉዳዩ እጅግ ግዙፍ የሆነ የአገር ህልውና ጉዳይ ስለሆነ በጥልቀት፣ በስፋት፣ በሰከነ አዕምሮና አስተሳሰብ በመሆን በተረጋጋ መንፈስ ሊታይ እንደሚገባውም ጠቁመዋል፡፡

‹‹ጠንክረን ከሠራን ፍሬ እናጣለን ተብሎ አይገመትም›› ያሉት ፓትርያርኩ ሲኖዶሱ እንደ ካሁን ቀደሙ ኮሚቴ አቋቁሞ መለያየት ሳይሆን፣ የአገር ሰላም ጉዳይ በቀጥታ ይመለከተናል በሚል ቅን መንፈስ፣ በተቃርኖ ያሉ ኃይሎችን በግንባር በማግኘትና በማነጋገር፣ የአንድ ሰው ሕይወት እንኳ እንዳይጠፋ ሁሉም የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠንክሮ መማፀን አለበት›› ሲሉም አፅንዖት ሰጥተውበታል፡፡

አያይዘውም የሁሉም ምርጫ ውይይትና ውይይት ብቻ እንዲሆንም ቅዱስ ሲኖዶሱ በርትቶ በመሥራት ሁሉንም ማሳመን እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡ ከአቅሙ በላይ ከሆነም ልምዱና ጥበቡ ያላቸው አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ገለልተኛ ወገኖችን በማሳተፍ የዕርቁና የሰላሙ ተልዕኮ ግብ እንዲመታ ማድረግ አለበት ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡

ቅዱስ ፓትርያርኩ በንግግራቸው እንደገለጹት፣ በአሁኑ ጊዜ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለከፋ አደጋ የዳረጋት መሠረታዊ ምክንያት የአክራሪዎችና የተቃራኒዎች እንቅስቃሴ መሆኑ በውል መታወቅ አለበት፡፡ በቤተ ክርስቲያኒቱ የሚታዩ ልዩ ልዩ የአሠራር ጉድለቶችም ማለትም የአስተዳደር ስልት፣ የፋይናንስና የንብረት አያያዝ ምዕመናንን እያበሳጨ መሆኑን መዘንጋት እንደማይገባ ጠቁመዋል፡፡

እነዚህንና ሌሎች ችግሮችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስተካከል ዕውቀቱ፣ ልምዱና ችሎታው ባላቸው ባለሙያዎች፣ በጊዜያዊም ቢሆን ተመድበው በጥናት ላይ የተመሠረተ መሪ ዕቅድ ዘመናዊ አሠራርን አዘጋጅተው እንዲያቀርቡ መደረግ እንዳለበት መክረዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት በተካሄደው ሠላሳ ዘጠነኛው የሰበካ ጉባዔ ስብሰባ ላይ ቤተ ክርስቲያኒቱ በከባድ ፈተና ላይ መሆኗን መገለጹን ዳግም ያስታወሱት ቅዱስ ፓትርያርኩ፣ የጥፋት ድርጊቱ እንዲቆም ሲኖዶሱ ሁነኛ መፍትሔ ማስቀመጥ ይኖርበታል ብለዋል፡፡

የቤተ ክርስቲያኒቱ አጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባዔ ጥቅምት 3 ቀን ሲጀመር በክርስቲያኖች ላይ የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መበራከት፣ የቤተ ክርስቲያንን ዕጣ ፈንታ አስጊ እንዳደረገው የገለጹት ፓትርያርኩ፣ ለሦስት ሺሕ ዘመናት አገርን የጠበቀችና የገነባች በማንም ላይ ግፍ ያልፈጸመች ቤተ ክርስቲያን ላይ ግፍ ተፈጽሟል፡፡ ቤተ ክርስቲያንንም ከምድረ ገጽ ለማጥፋት የተነሱ ኃይሎች በመኖራቸው ‹ፍትሕ ፍትሕ› እያልን ብንጠይቅም፣ በክርስቲያኖች ላይ በሃይማኖታቸው ምክንያት የግፍ ግፍ እየተፈጸመባቸው መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

ምንጭ፡ ሪፖርተር

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe