ይልቅ ወሬ ልንገርህ፡- የኢቢሲ የቦርድ አባላት ሹመት ፓርላማውን ሲያጨቃጭቅ ዋለ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጋቢት 12 ባደረገው መደበኛ ስብሰባው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የቦርድ አባላትን ለመሾም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የተሰየሙ የቦርድ አባላትን ለማፅደቅ ሲጨቃጨቅ መዋሉ ተሰማ፡፡ ጠቅላይ ሚስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ለኢቢሲ የቦርድ አባላት እንዲፀድቅላቸው የላኳቸው ሰዎች ዝርዝር ከፓርላማ አባለቱ ብርቱ ተቃውሞ ቀርቦባቸዋል፡፡ በዋናነት ተቃውሞ የቀረበባቸው የቦርዱ ሰብሳቢ ሆነው እንዲሰሩ በተመደቡት የኦዴፖ ማዕከላዊ ኮሚቴና የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ አባል በሆኑት አቶ ፋቃዱ ተሰማ ላይ ነው፡፡ ለምክር ቤቱ ተያይዞ የቀረበው የግለሰቡ የህይወትና የስራ ልምድ ታሪክ እንደሚያስረዳው ከሆነ አቶ ፍቃዱ በወረዳ አመራርነት እና በዞን አመራርነት ጀምረው በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ የስራ ሀላፊነቶች ላይ ማገልገላቸው ተመልክቷል፡፡ የግለሰቡ ሹመት ፖለቲካዊ ካልሆነ በስተቀር ኢቢሲን ያህል ትልቅ የመንግስት ሚዲያ ለመምራት ብቁ አይደሉም ተብሏል፡፡ ግለሰቡ በአካውንቲንግና በሊደርሽፕ መማራቸው የተገለፀ ቢሆንም አቶ ፍቃዱም ሆነ ሌሎች የቦርድ አባላት የስራ መስኩ የሚጠይቀው የጋዜጠኝነት ትምህርት የተማሩ ወይም በሙያው አንድም የሰራ ሰው አለመኖሩ የቦርዱን የስራ እንቅስቃሴ ደካማ እንደሚያደርገው በመጥቀስ ለሌሎች ሰዎች ሊቀየሩ ይገባል የሚል ጥያቄ በምክር ቤቱ አባላት ተሰንዝሯል፡፡ ተቃውሞ ከቀረበባቸው ሰዎች መሀከል በሌሎች መንግስታዊ የስራ መደብ ላይ ብዙ ሀላፊነት የተሰጣቸው ሰዎች በቦርድ አባልነት መልሶ ማቅረብ ምን ያህል ጠቃሚ ነው በሚል የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯን ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬን በእጩነት መቅረብ እንዲሁም ባለፈው በጠቅላይ ሚኒስተር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ጊዜ የኢቢሲ ቦርድ አባል ሆነው ሲሰሩ የነበሩት የቀድሞ የግብርና ሚኒስትር አቶ ተፈራ ደርበው ስም ተጠቅሷል፡፡ ሌላው ተቃውሞ የቀረበባቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ አባልና በቅርቡ በተቋቋመው የሰላምና እርቅ ኮሚሽን ምክትል ሰብሳቢ በመሆን በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የተሾመች ወ/ሮ የትነበርሽ ንጉሴ እንዲሁም በድንበር ኮሚሽኑ አባልና የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቋማዊ ለውጥ አባል የሆነው ኡዝታዝ አቡበክር አህመድም ኢትዮጵያ ሌላ ሰው የላትም ወይ በሚል ተቃውሞ ከቀረበባቸው ሰዎች መሀከል ይገኛሉ፡፡ ጉዳዩን በተመለከተ ምላሽ የሰጡት የምክር ቤቱ የመንግስት ተጠሪ አቶ ጫላ ለሚ ለሁሉም ጉዳይ ተደጋጋሚ ሰዎች የሚሾሙት ለምንድነው ለሚለው ጥያቄ የቦርዱ አባላት ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጡ ይሆናሉ ስለሚል እንደሆነ ገልፀው ሰዎቹ እዚህ ቦታ በቦርድ አባላት ሲመደቡ የያዙት አቋም ታይቶ ሳይሆን ባላቸው ተቀባይነት ነው ብለዋል፡፡ የሰብሳቢውን አቶ ፍቃዱን ጉዳይ ተቋሙ በፖለቲካ ሰው መመራት ስለለበት ነው ብለዋል፡፡ የትምህርት ደረጃን በተመለከተ አንድም የቦርድ አባል በጋዜጠኝነት ሙያ የተመረቀ የለም በሚል ለቀረበው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት አቶ ጫላ ‹ለምሳሌ ዶ/ር ኤርጎጌ ከሁለተኛና ከሶስተኛ ዲግሪያው ውጭ የተማሩት ጋዜጠኝነት ነው› ብለዋል፡፤ አቶ ጫላ እንዲያ ይበሉ እንጂ ለምክር ቤቱ የቀረበው የዶ/ር ኤርጎጌ የትምህርት ማስረጃ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጋዜጠኝነት ሳይሆን በውጭ ቋንቋዎችና ስነ ፅሑፍ የትምህርት መስክ በ1996 ዓ. ም መቀበላቸውን ያሳያል፡፡ በመጨረሻም በቀረበው የቦርድ አበላት ላይ ድምፅ እንዲሰጥ ተደርጎ በ10 ተቃውሞና በ28 ድምፀ ተአቅቦ ሹመቱ ፀድቋል፡፡ ሹመቱ ከፀደቀ በኋላ በምክር ቤቱ የአሰራርና የስነ ምግባር ድንብ መሠረት ተሷሚዎቹ በምክር ቤቱ ቀርበው ቃለ መሀላ መፈፀም የነበረባቸው ቢሆንም ቃለ ማህላውን ሳይፈፅሙ ቀርተዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱን የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ሽታዬ ምናለ ሲናገሩ አዳራሹ በምክር ቤቱ አባላት ሳቅ ተሞልቷል፤ የሳቁ ምክንያት ቀደም ሲል ተሳሚዎቹ ተደራራቢ የስራ ሀላፊነት ያለባቸው በመሆናቸው በሌሎች ሰዎች ይቀየሩ የሚለውን የምክር ቤቱን አባላት ጥያቄን ወደ ጎን በማለፍ በጥድፊያ እንዲፀድቀው በመደረጉ ነው፡፡ በመጨረሻም ወ/ሮ ሽታዬ ‹በተደራራቢ ስራ ምክንያት ተሻሚዎቹ ተሟልተው ለዛሬ ሊቀርቡ ስላቻሉ ለሌላ ጊዜ ይፈፀማል ›ብለዋል እንደሌሎቹ የምክር ቤት አባላት ሳቅ እያፈናቸው፡፡

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe