ይልቅ ወሬ ልንገርህ ስለ እድለ ቢሱ ጥላሁን ገሠሠ አደባባይ

ይህ ፎቶ ሸራተን ሆቴል ፊት ለፊት የነበረው አደባባይ ነው፤ አደባባዩ በጥላሁን ገሠሠ ስም ተሰይሞ ነበር፤ ያው ነበር ሆናል ዛሬ፤ ጥላሁን ገሠሠ በህይወት እያለም ሆነ ከዚህ አለም በሞት ከተለየ በሃላ የመታሰቢያ ሃውልት ሊቆምለት ያልቻለ እድለ ቢስ የጥበብ ሰው ነው፤ በሞቱ ማግስት ሁሌም እንደሚደረገው በጥላሁን ስም ይህ ይሰራል ያ ይሰራል ተባለ፤ ከተባለው ውስጥ በስሙ አደባባይ ተሰይሞ ሃውልቱ ይቆማል ተብሎም ነበር፤ አደባባዩም መሻለኪያ አካባቢ በስሙ ተሰየመ ተባለ፤ ብዙም ሳይቆይ የከተማው ቀላል ባቡር ፐሮጀክት ሃዲዱን  በአደባባዩ ላይ ዘረጋ፤ የጥላሁን ሃውልት አለመቆሙ በጀ እንጂ ሃውልቱ ቆሞ ቢሆን ኖሮ ሃዲዱ ጥላሁንን ይጨፈልቀው ነበር፤

አመታት ነጎዱ፤ ጥላሁን ካረፈ ከ12 አመታት በሃላ ጥላሁንን የሚያስታውስ ነገር ተከሰተ፤ ከሁለት አመታት በፊት ሀገራችን ለገባችበት ጦርነት የጥላሁን ዘፍኖች አስፈላጊ ስለነበሩ ከየነበሩበት ተፈልገው ወጡ፤ ግን በቂ ሆነው ስላልተገኙ ከመሞቱ 3 አመት በፊት የሰራው <ቆሜ ልመርቅሽ> የተሰኘው ዜማና ሌሎች ዘፈኖች በጥድፊያም ቢሆን ታትመው ለህዝብ እንዲቀርብ ሲደረግ ለውሳኔው ማጀቢያ የአደባባይ ስያሜ አብሮ ብቅ አለ፤

Tilahun square 1

የአልበሙ ምረቃ በወዳጅነት ፓርክ በዋናነት በቀድሞ ወዳጁና አሁን በማረሚያ ቤት በሚገኙት አቶ አብነት ገ/መስቀል መሪነት ሲካሄድ አደባባዩ ከፓርኩ ብዙም ሳይርቅ ሽራተን ሆቴል ደጃፍ ያለው አደባባይ ላይ ይሆናል ተባለ፤ በአጭር ጊዜ የጥላሁን ሃውልትን እናቆምበታለን ከሚል መግለጫ ጋር ተባለ፤ ያው ተባለ፤

ጥላሁን በህይወት እያለ የልማት ተቃዋሚ አልነበረም፤ አሁንም የልማት ተቃዋሚ አለመሆኑን ለማሳየት ይመስላል ሃውልቱ የሚቆምበት አደባባይ የተወገደው፤ እድሜ ልኩን ስለ ፍቅርና ስለ ኢትዮጵያ ሲያዜም ለኖረው ለጥላሁን ገሠሠ አዲስ አበባ ስሙ የሚጠራበት አደባባይና ክብሩን የሚገልጽ ሃውልት ለማቆም አለመቻላ አስገራሚ ብቻ ሳይሆን አሳፋሪም ነው፤

ደግነቱ ጥላሁን ገሠሠ እድሜ ልኩን ሲያዜም የኖረው እዚህ ወይም እዚያ ቦታ ሃውልቴ ይቆምልኛል ብሎ አይደለም፤ የራሱን ሃውልት በድምጹ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ ያቆመ ሰው ነው፤ አሌክሳንደር ፑሽኪን እንዳለው፤

ግርማ ሞገስ ያለው እጅግ የሚያኮራ

በእጅ ያልተቀረጸ በሰው ያልተሰራ

ከእስክንድር ምሰሶ በቁመት የላቀ

በአሰራሩም ቢሆን እጅግ የረቀቅ

ሃውልት አቁሜያለሁ ለመታሰቢያዬ

ለሚመጣው ትውልድ ለወደሃላዬ

(አያልነህ ሙላቱ እንደተረጎመው)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe