ይልቅ ወሬ ልንገርህ የአድዋን ጀግኖችን ስለማመስገን ተጨማሪ አጋጣሚ

ከአመታት በፊት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ይተላለፍ የነበረውን የኩንታ ኩንቴ ፊልም የሚያስታውስ ቦታ ላይ ተገኘሁ። በምእራብ አፍሪካዊቷ ጋና ። በዋና ከተማዋ አክራ ግርጌ በአትላንቲክ ውቅያኖስ ዳርቻ የሚገኘው Cape Coast Castle ምእራባውያን ቅኝ ገዥዎች ጋናውያንን እጅና እግራቸውን በብረት ሰንሰለት እየጠፈሩ የባሪያ ንግድ ያከናወኑበት ታሪካዊ ስፍራ ነው።
ምእራባውያን አገር አሳሾች በቀዳሚነት በፖርቹጋሎች እየተመሩ በጋና አትላንቲክ ዳርቻ መልህቃቸውን ከጣሉበት እኤአ 1489 ጀምሮ ሆላንዶች ዴንማርኮችና በመጨረሻም ብሪታንያ ለ400 አመታት ያህል ጥቁሮችን ወደ አሜሪካና ወደ ካሪቢያን ሀገራት እየተፈራረቁ አግዘዋቸዋል።፣ሸጠዋቸዋል።
እዚህ ቦታ ላይ መገኘት ያስቆዝማል፣ ያሳቅቃልም። የሙቀት መጠኑ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ከውቅያኖሱ ዳርቻ የሚነፍሰው ንፋስ እያለ እንኳ ለደቂቃ መቆም ያውካል። ጥቁር አፍሪካውያንን ወደ መርከብ ለመጫን ከመሬት በታች የተገነቡት እስር ቤቶችና ማቆያ እጅግ ጠባብ ዋሻዎች/ ታናሎች/ አሉ። ታነሉን ለመመልከት አንድ በአንድ ደረጃውን መውረድ ነበረብን ልብሳችን በላብ ረጥቦ እስክንወጣ ድረስ።
አስጎብኛችን እንደገለፀልን አፍሪካውያን ጥቁሮች ወደ መርከቡ ላለመግባት ስለሚያገራግሩ አስቀድመው እጅና እግራቸው በብረት ሰንሰለት እንደታሰሩ እየተገፈተሩ ነው ወደ ታናሉ የሚወረወሩት። በዚህ ሂደት የሚረጋገጡና ህይወታቸው የሚያልፉ ሰዎች ብዙ ናቸው። የተረፉት ወደ መርከቡ ሲጫኑ ህይወታቸው ያለፉት በእርሻ ስፍራ ይቀበራሉ ለማሳው ማዳበሪያ። ይህ ነበር አፍሪካዊነት።
ከዚህ ሁሉ አልፈው ወደ መርከቡ የሚገቡት ተጋዦች የሚጫኑት ሶስት ደረጃ ባለው መርከብ ሲሆን ህፃናት ከወላጆቻቸው ተነጥለው ከላይ ይጫናሉ ።ከመሃል እናቶች ሲጫኑ ከስር ወላል ላይ የመርከቡን መዘውር እንዲያሽከረክሩ ወንዶች ይገባሉ። ወራት የሚፈጀውን የመርከብ ጉዞ የሚዘውሩት ባሮች እጃቸው ይዝላል፣ አንዳንዶቹም እጃቸው ደም ቋጥሮ ህክምና በማጣት ታመው ይሞታሉ። ህይወታቸው ያለፉት በሚያሳዝን መልኩ ውቅያኖሱ ላይ ይጣላሉ። ለሻርክ።

ጋና አትላንቲክ ውቅያኖስ
ሀገራችን የዚህ አሰቃቂ ታሪክ አካል አለመሆኗን አሰብኩ። ግን ከዚህ ማን ጠበቀን ? ቅኝ ገዢዎች ስላልፈለጉ አልነበረም፣ ስላልቻሉ እንጂ። እድሜ ለአፄ ምንልክና ለአድዋ ጀግኖች ፣ ቅኝ የመግዛት ሙከራ ያደረጉትን የፋሺሽት ጣሊያን ወታደሮችን ጀግኖቹ በጦር ከተራራው ጋር አጣብቀው እንደሰፏቸው ታሪክ ይናገራል።
ጋናውያን ከረጅም ዘመናት ትግል በኋላ ነፃነታቸውን ከመጨረሻዋ ቅኝ ገዢ ከእንግሊዝ እኤአ በ1957 ሲቀዳጁ ለዚህ ነፃነት ያበቋቸውን መሪዎቻቸውን ተገቢ ክብር አላብሰዋቸዋል። ከነፃነት በኋላ የታተመውና አሁንም ድረስ ስራ ላይ ባለው የ50 ብር ኖታቸው ላይ /ብራቸው ሲዲ ይባላል /የባሪያ ንግድ ማከናወኛው ህንፃና የጀግኖቻቸውን ምስል አትመው ትውልድ ያስተምሩበታል። ዩኔስኮም ይህን ህያው ታሪክ የተፈፀመበትን ስፍራ በአለም ቅርስነት መዝግቦ ይዞታል።
ሆኖም እኛ ኢትዮጵያን እንደነሱ በአካል አንጋዝ እንጂ ዛሬ በመንፈስ መሰደዳችንን ሳስብ ቅኝ ያለመገዛታችን ኩራቴ ጣጥሎኝ ነው የበረረው። ዛሬ በየኤምባሲው ደጃፍ ያለውን የዜጎቻችንን ሰልፍ እያዩ ኩራት ከወዴት ይመጣል?

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe