ዲሻቸውን  ወደ ኢትዮ ሳት የሚቀይሩ ቤተሰቦች በክፍያ የሀገር ውስጥ ቲቪዎችን ይመለከታሉ

ከናይል ሳት ሳተላይት ተከራይው የቴሌቪዥን ፕሮግራሞቻቸውን የሚያሰራጩ የሀገራችን የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዲሽ አቅጣጫቸውን እንዲቀይሩ የሚያሳስቡ ማስታወቂያዎችን በየጣቢያዎቻቸውን እያስተዋወቁ ሲሆን አዲሱ ኢትዮ ሳት የተባለው የኤስ.ኢ.ኤስ ሳተላይት ቻናልን በግማሽ ዓመታዊ ክፍያ አገልግሎቱን እንደሚያገኙ እየተገለፀ ነው፡፡:

ሰሞኑን የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን የሀገራችን የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በዓመት ለሳተላይት ኪራይ እስከ 400 ሚሊዩን ብር እንደሚያወጡ የገለፀ ሲሆን  ኤስ.ኢ.ኤስ የተባለው የሳተላይት አከራይ ድርጅትን በግማሽ ዓመታዊ ክፍያ የአገለግሎቱ ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚችሉ  ተናግሯል፡፡

<ሌ/ጀነራል ጻድቃን ገብረ ትንሳዔን ጨምሮ 40 የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ሃይልና የፖሊስ…>

ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ከፍተኛ  ባለሙያ እንደገለፁት ኤስ.ኢ.ኤስ የተባለው መቀመጫውን ደቡብ አፍሪካ ያደረገው የፈረንሳይ ኩባንያ የሀገር ውስጥ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ዲሻቸውን  ቀደም ሲል ይጠቀሙበት ከነበረውና ዓለም አቀፍ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ከሚገኙበት ናይል ሳት  ወደ ኢትዮ ሳት ሲያዛሩ እስከ አንድ ዓመት ለሚደርስ ጊዜ ከሳተላይት ክፍያ ነፃ እንደሚያደርግላቸው በመግለፁ ብዙዎቹ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የዲሻቸውን አቅጣጫ እያስቀየሩ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

ኤስ.ኢ.ኤስ የተባለው የሳተላይት አከራይ ካምፓኒ ለመጀመሪያ ዓመት ሁሉንም ጣቢያዎች ከክፍያ ነፃ ካደረገ በኋላ በቀጣዩ ዓመት እያንዳንዱ የቴሌቪዥን ተመልካች የሀገር ውስጥ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን ለመመልከት ከዲኤስ ቲቪ አነስተኛ  የክፍያ ዋጋ (220 ብር) በግማሽ የሚቀንስ ክፍያ በማስከፍል የጣቢያዎቹን ፕሮግራሞች ለመመልከት እንደሚገደድ ታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ በተደረገ ጥናት 56 ሚሊዮን ቤተሰቦች የቴሌቪዥን ተመልካቾች ሲሆኑ ኤስ.ኢ.ኤስ በየወሩ የሀገር ውስጥ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን መመልከት ከሚፈልጉ ቤተሰቦች በየወሩ ቢያንስ 100 ብር ይሰበስባል ተብሏል፡፡

<የእናት ወግ የበጎ አድራጎት ማህበር  ከኃይለማርያም እና ሮማን ፋዉንዴሽን  ጋር ተዋሀደ>

አቅም የሌላቸው የቴሌቪዥን ተመልካቾች መንግስት የሚያስተላልፈውን መረጃ ሳያገኙ እንዳይቀሩ እንደ ኢቲቪ እና ፋና ያሉ የመንግስት ጣቢያዎች በቻናሉ ላይ በነፃ የሚተላለፉ ሲሆን በናይል ሳት ላይም ያላቸው ፍሪኩዌንሲ ለጊዜው እንደማይቋረጥ ተመልክቷል፡፡ በሌላ በኩል ግን ከኤስ.ኢ.ኤስ ጋር በቅርበት የሚሰራው ኢቢኤስ ቲቪ ከጥቂት ቀናት በኋላ ከናይል ሳት ላይ እንደሚጠፋ ማስተዋወቅ ከጀመረ ቆይቷል፡፡

ከለውጡ በፊት ሁሉንም የሀገሪቱን የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በኢንሳ በኩል በማድረግ ለመቆጣጠር ብሮድካስት ባለስልጣንን ይመሩ በነበሩት በእነ አቶ ዘርአይ አስከዶም ተወጥኖ የነበረው አሰራር የአፈና ዘዴ ነው በሚል ተቃውሞ ገጥሞት የነበረ ሲሆን አሁንም በኤስ.ኢ.ኤስ አማካይነት  የሀገሪቱን የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በአንድ ቋት ላይ ማስቀመጥ የሚዲያዎቹን ነፃነት ይፈታተናል፤ በቀላሉ ከስርጭት ውጭ ለማድረግ ቅርብ ነው የሚሉ ወገኖች ከወዲሁ ብቅ ብለዋል፡፡

ይህንኑ መነሻ በማድረግም በኤስ.ኢ.ኤስ  ቻናል ላይ የሚገቡት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የመዝናኛና መንግስትን የማይተቹ እንዲሁም  በሀገር ውስጥ ፍቃድ ያወጡ ብቻ ስለሚሆኑ እንደ መረጃ ቲቪ አይነት የተለየ አመለካከት የሚያስተላልፉ ጣቢያዎች ቦታ እንደማይኖራቸው ተመልክቷል፡፡ በዚህ ሳቢያ ህብረተሰቡ  በኢትዮ ሳት ቻናል ላይ የማይገቡ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን ፍለጋ ከዚህ በፊት  ኢሳትንና ኦኤም ኤንን ለመመልክት  እንደሚያደርገው ተጨማሪ ዲሽ አልያም ኤልኤን ቢ ለማስገጠም ይገደዳሉ ሲሉ ስጋታቸውን ከወዲሁ ይገልፃሉ፡፡

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe