ዳሸን ባንክ ደንበኞች በአቅራቢያቸው ያሉ የንግድ ተቋማትን በቀላሉ በማግኘት ክፍያ ለመፈፀም የሚያስችል “ዳሸን ኤር ፔይ” የተሰኘ አዲስና ዘመናዊ የክፍያ አገልግሎት ትላንት በሸራተን አዲስ ሆቴል አስተዋወቀ፡፡
ዳሸን ኤር ፔይ በዳሸን ሱፐር አፕ ውስጥ የተካተተ አዲስ፣ ቀላልና ዘመናዊ አገልግሎት ሲሆን ደንበኞች የዳሸን ሱፐር አፕ መተግበሪያቸውን ከፍተው ዳሸን ኤር ፔይ የሚለውን ሲነኩ በአቅራቢያቸው ያሉ የንግድ ተቋማትን ያሳያቸዋል፡፡ በመቀጠልም ክፍያ የሚፈፅሙለትን የንግድ ተቋም በመመምረጥ የክፍያ መጠኑን አስገብተው ከፍያቸውን በቀላሉ መፈፀም ይችላሉ፡፡
ዳሸን ኤር ፔይ ደንበኞች ያለ አካውንት፣ ኪውአር ኮድ ወይም ስልክ ቁጥር ክፍያ ለመፈፀም የሚያስችል በመሆኑ እስካሁን ከነበሩት አገልግሎቶች ሁሉ የተለየ እና ቀላል ያደርገዋል፡፡
የዳሸን ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አስፋው ዓለሙ በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ዳሸን ባንክ የዲጂታል ክፍያ ስርዓትን ለማዘመን የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠሉን ጠቁመው ዛሬ የተዋወቀው አገልግሎት በደንበኞችንና የንግዱ ማህበረሰብ መካከል ያለው ግብይት በቀላሉና በአጭር ጊዜ እንዲከናወን ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት አመልክተዋል፡፡
አቶ አስፋው “በኤር ፔይ የክፍያ መፈጸሚያ መንገድ ብቻ እያቀረብን አይደለም፤ ይልቁንም ደንበኞቻችንን ከሀገር ውስጥ የንግድ ተቋማት ጋር በቀጥታ የሚያገናኝ አማራጭ ጭምር እየፈጠርን ነው” ብለዋል።

