በግል ባንክ ኢንዱስትሪው መስክ ግንባር ቀደም ሚና የተወጣው ዳሸን ባንክ የተመሰረተበትን 28ኛ ዓመት እንዲሁም የሰራተኞች ቀን ዛሬ ጥር 26 ቀን 2016 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ ከባንኩ ሰራተኞች እና አመራሮች ጋር በልዮ ልዮ መሰናዶ አከበረ።
በመርሐ-ግብሩ ላይ የተገኙ የዳሸን ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው አለሙ እንደገለጹት ባንኩ በተጠናቀቀው የፈረንጆች ዓመት ላይ ስኬታማ የነበረ መሆኑን ገልጸው ለዚህ ውጤት መብቃት ጉልህ ሚና ለተጫወቱት የባንኩ ሠራተኞች እና አመራሮችን አመስ ግነዋል።
“አንድ እርምጃ ቀዳሚ“ በሚል መርህ የሚታወቀው ዳሽን ባንክ ባሳለፍነው አመት የ18 ቢሊዮን ብር ገቢ ያስመዘገበ ሲሆን ከትርፍ አኳያ ከግብር በፊት 5 ቢሊዮን ብር ትርፍ አግኝቷል።
10 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል የፈጠረው ዳሽን ባንክ የእንግሊዙ ፋይናንሻል ታይምስ የሚያሳትመው ዘ ባንከር መጽሔት ለተከታታይ ሁለተኛ ዓመት በጠቅላላ ለ13ኛ ጊዜ የ2023 የኢትዮጵያ አሸናፊ ሆኖ የመረጠው ሲሆን በባህሬን በተከናወነ ሥነ ስርዓት የ2023ቱ የኢስላሚክ ሪቴይል ባንኪንግ ሽልማት (IRBA) አሸናፊ ጭምር ነው።
ጥር 26 2016 በሚሊኒየም አዳራሽ ከጠዋቱ 5 ሰአት እስከ ምሽቱ 12 ሰአት በተደረገው በአል 4000 የሚጠጉ የድርጅቱ ባልደረቦች የታደሙ ሲሆን ልዩ ልዩ የሙዚቃ ዝግጅት ነበር፡፡ በእለቱ ለፕሮግራሙ ድምቀት ለመስጠት ድምጻውያን ፍቅርአዲስ ነቅአጥበብ ፤ ኤልያስ ተባባልና ጌታቸው ሀይለማርያም እና ሌሎችም የእለቱን ታዳሚያን ሲያስደስቱ ውለዋል፡፡
በዳሸን ባንክ ከ25 አመት በላይ ያገለገሉ 17 ነባር ባልደረቦች እውቅና የተሰጣቸው ሲሆን አብዛኛዎቹ ከጀማሪ ተነስተው በአሁኑ ሰአት ከፍተኛ የስራ አመራር ለመሆን የቻሉ ናቸው፡፡

