ዳንኤል አራፍ ሞይ – የአፍሪካ የመጨረሻው ‹ትልቅ ሰው›

ምሥራቅ አፍሪካዊቷን ሀገር እ.ኤ.አ ከ1978 እስከ 2002 የመሩት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዳንኤል አራፍ ሞይ በ95 ዓመታቸው ከሰሞኑ ይህቺን ዓለም ተሰናብተዋል፡፡ ሞይ ከጆሞ ኬንያታ መሞት በኋላ ነበር የኬንያ ሁለተኛ ፕሬዚዳንት የኾኑት፡፡ ከአንድ ወር በላይ በሆስፒታል ተኝተው ህክምና ሲከታተሉ ቢቆዩም ከናይሮቢ ሆስፒታል መልካም ዜና ሳይሰማ ቀርቷል፡፡ ኬንያን የሚመሩት የወቅቱ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ሲቲዝን በተባለው የሀገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ባሰሙት ንግግር የቀድሞው ፕሬዚዳንት በሞት መለየታቸውን አብሥረዋል፡፡ ‹‹የታላቁን አፍሪካዊ የሀገር መሪ ከዚህ ዓለም በሞት መለየት ስነግራችሁ ከፍተኛ ኀዘን እየተሰማኝ ነው፡፡ ክቡር የቀድሞ ፕሬዚዳንቱ የካቲት 4 ቀን 2020 (እ.ኤ.አ) በናይሮቢ ሆስፒታል ቤተሰቦቻቸው በተገኙበት ዐርፈዋል›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ኬንያን ለ24 ዓመት የመሩት ዳንኤል አራፍ ሞይ ሀገሪቱ ከቅኝ ግዛት በወጣችባቸው የመጀመርያ ዓመታት ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው አገልግለዋል፡፡
ለመኾኑ እኚህ ሰው ማን ናቸው? የሥልጣን ዘመን አበርክቷቸውስ ምን ይኾን? እነኚህንና ሌሎች የሕይወት ገጾቻቸውን እየገለጥን ማንነታቸውን እንቃኛለን፡፡
‹ሞይ እና እኔ›
የቀድሞው ፕሬዚዳንት 90ኛ ዓመት የልደት በዓላቸውን ባከበሩበት ወቅት ‹ሞይ እና እኔ› በሚል ርዕስ የግል ትውስታውን በዶቼዌሌ ድረገጽ ያሰፈረው ዳንኤል ፔልዝ ‹ሰውየው የትም ይገኛሉ፡፡ ኮስታራ ፊታቸው በየትኛውም ቢሮ ውስጥ የተሰቀለ ፎቷቸው ላይ ይታያል፡፡ የወጣትነት ዘመን ምስላቸው በየትኛውም የገንዘብ ኖት ላይ ታትሞ ይታያል፡፡ ዓለም የቱንም ዓይነት የተፈጥሮ አደጋ ብታስተናግድ የሀገሪቱ ብሔራዊ ጣቢያ እያንዳንዷን ርዕሠ አንቀጽ ‹ፕሬዚዳንት ዳንኤል አራፍ ሞይ ዛሬ እንዳሉት . . . ›› በማለት ነው የሚጀምረው፡፡› ሲል ሰውየው በወቅቱ የነበራቸውን የገዘፈ ሥልጣን አሳይቷል፡፡
እ.ኤ.አ በ2000 በጎዳና ተዳዳሪዎች ሕይወት ላይ የሚያተኩር ፕሮጀክት ላይ ለመሥራት ወደ ሀገሪቱ መግባቱን የሚገልጸው የዶቼዌሌው የአፍሪካ አገልግሎት የእንግሊዘኛ ቋንቋ ክፍል ኃላፊ ዳንኤል ፔልዝ በወቅቱ የነበረችውን ኬንያ እንዲህ ሲል ነበር የገለጻት፡፡ ‹‹ሰውየው የሚመሯት ሀገር መንገዶቿ ሙሉ በሙሉ የተቆፋፈሩ ነበሩ፡፡ በኤሌክትሪክ እጦት በእያንዳንዷ ምሽት በጨለማ እንቀመጣለን፡፡ በየቀኑ ለተወሰኑ ሰዓታት የመብራት መጥፋት የተለመደ ነበር፡፡ ውሃ የምናገኘው በሁለት ሳምንት አንድ ጊዜ ሲኾን በዲግሪ የተመረቁ ወጣቶች ኑሯቸውን ለመግፋት አውቶቡስ ማሽከርከር እና ግሮሰሪ ውስጥ በሻጭነት መሥራት ነበረባቸው፡፡ ድሆች የሚኖሩባቸው ቆሻሻ ሰፈሮች በየቀኑ ቁጥራቸው የሚጨምር ይመስላል፤ ሰዎች በቀትር ፀሐይ ይገደላሉ፤ ሙስና በየጊዜው መጠኑ እያደገ ሲሔድ መንግሥትን የሚተቹ ሰዎች ወይ ይገደላሉ ወይም ድምጻቸውን አጥፍተው እንዲቀመጡ ይደረጋል፡፡››
የዶቼዌሌው ጋዜጠኛት ውስታውን ይቀጥልና ሰውየው በፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው ‹‹የሕዝቡ አባት›› ብለው ራሳቸውን ይጠሩ እንደነበር ይገልጻል፡፡ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ለሀገራቸው የሠሩት ብቸኛ ጥሩ ነገር እ.ኤ.አ በ2002 ስልጣናቸውን በሰላም መልቀቃቸው ብቻ እንደነበር ያስረዳል፡፡ ‹‹ኬንያ እንደሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ወደ ብጥብጥ ሳታመራ ስልጣን በሰላም በመልቀቃቸው አደንቃቸዋለሁ፡፡ በስልጣን ዘመናቸው የነበሩት ሙስና፣ ኢ-ፍትሐዊ አሠራርና ግጭቶች የኬንያ የወደፊት ችግሮች ሆነው ይቀጥላሉ፡፡›› በማለትም ጽሑፉን አጠቃልሏል፡፡
የመጨረሻው ‹ትልቅ ሰው›
ዋሺንግተን ፖስት የዳንኤል አራፍ ሞይን በሞት መለየት በዘገበበት ጽሑፍ ሰውየውን በጠንካራ ክንድ ሀገራቸውን ከመሩ የአፍሪካ መሪዎች የመጨረሻው ‹ትልቅ ሰው› ሲል ገልጾአቸዋል፡፡ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ስልጣን ላይ ሲወጡ በሀገሪቱ ይታይ የነበረውን ጎሰኝነትና ሙስና ለማስቀረት ቃል ገብተው የነበረ ቢኾንም እርሳቸው የመሠረቱት መንግሥት መጨረሻም የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን ማሳደድ፣ የዘረኝነት ግጭቶችን ማስፋፋትና ሕዝቡን ለጉዳት መዳረግ ነበር፡፡ ከባድ በነበረው የ24 ዓመት የሥልጣን ዘመናቸው የፖለቲካ ነፃነትን አግደዋል፣ የኬንያን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ቁጥጥራቸው እንዳያድግ አድርገዋል እንዲሁም ስማቸውን በሀገሪቱ ገንዘብ፣ በት/ቤቶች፣ በዓለማቀፍ አየር መንገድ እና በሀገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች በማስፈር አምባገነንነትን በሚገባ አሳይተዋል ይባላል፡፡
በሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ድርጅቶች በሰብአዊ መብት ጥሰት ለወቀሳ የተዳረጉና ኬንያ በዕርዳታ ያገኘችውን በሚሊየን የሚቆጠር ዶላር ዘርፈዋል በሚል ክስ የሚነሳባቸው ቢኾንም በፀረ – ኮሙኒዝም አቋማቸውና በወቅቱ በተለያዩ ግጭቶች ትናጥ በነበረችው አህጉር በአንጻራዊነት ሰላሟ የተጠበቀ ሀገር በማስፈናቸው ከአሜሪካ ጋር የነበራቸው ግንኙነት ጥብቅ ነበር፡፡
ከልጅነት እስከ ዕውቀት
ቶርቲች አራፕ ሞይ እ.ኤ.አ መስከረም 2 ቀን በ1924 በሰሜን የናይጄሪያ አካባቢ ተወለዱ፡፡ አባታቸው እረኛ ነበሩ፡፡ የጥምቀት ሥርዓት ከተከናወነላቸው በኋላ ዳንኤል የሚል ስያሜ ተሰጣቸው፡፡ አባታቸው ሞይ፤ በልጅነታቸው በሞት ከተለዩዋቸው በኋላ አጎታቸው እያስተማሩ አሳድገዋቸዋል፡፡ በርቀት ትምህርት ለንደን ውስጥ ከሚገኝ አንድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም በአካውንቲንግ ትምህርት ሠርተፍኬት አግኝተዋል፡፡ በዚህም በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ውስጥ በመምህርነትና በአስተዳደር አገልግለዋል፡፡
ከብርሃን ወደ ጨለማ
እ.ኤ.አ በ1960 ኬንያ ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነፃ መውጣቷን ተከትሎ በተመሠረተው አዲስ መንግሥት የገንዘብ ሚኒስቴር ረዳት ኾነው ሀገራቸውን አገልግለዋል፡፡ ከሠሩባቸው የተለያዩ ኃላፊነቶች አንዱ የኾነው የሀገር ውስጥ ሚኒስትርነት እ.ኤ.አ በ1967 ወደ ምክትል ፕሬዚዳንትነት እንዲሸጋገሩ የረዳቸው መኾኑ ይነገራል፡፡
ከፕሬዚዳንት ጆሞ ኬንያታ ሞት በኋላም የሀገሪቱ ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት ኾኑ፡፡ ብሔራዊ አንድነትን መስበካቸው፣ ሙስናን ለመቅረፍና በሀገሪቱ ብሔሮች መካከል የሚነሱ ግጭቶችን ለማስቆም ቃል መግባታቸው በኬንያውያን ዓይን ተወዳጅ አደረጋቸው፡፡ በ1978 (እ.ኤ.አ) በሺህ የሚቆጠሩ የ‹ኬንያ አፍሪካን ዲሞክራቲክ ዩኒየን› ፓርቲ አባላት ‹ተወዳጁ ሞይ› የሚል ጽሑፍ የያዙ ካናቴራዎች ለብሰው ድጋፋቸውን ቸሯቸው፡፡ በቀላሉም ፕሬዚዳንት ኾነው ተመረጡ፡፡ ተወዳጅና ሀገር ወዳድ ኾነው ይታዩ የነበሩት ሰው ጭምብላቸውን አውልቀው ወደ አምባገነንነት ለመለወጥ ጊዜ አልፈጀባቸውም ነበር፡፡
ነፃ ምርጫ ለሚጠይቁ አካላት የሞይ መንግሥት ምላሽ ተቃዋሚዎችን ማሠር፣ ማሰቃየትና መግደል ኾነ፡፡ የተቃዋሚዎችን ቤቶች ማቃጠልና መንግሥትን የሚተቹ መገናኛ ብዙኀንን ማጥፋት ሥራው ኾነ፡፡ እጅግ ዝቅተኛ ድምጽ አግኝተው ያሸነፉባቸው የ1992ቱ እና የ1997ቱ ምርጫዎች የአምባገነንነታቸው ማሳያዎች ናቸው፡፡ የ1979፣ የ1983 እና የ1988ቱ ምርጫዎች እንዲያውም ካለምንም ተቃውሞ ፓርቲያቸው ኬንያን አፍሪካን ናሽናል ዩኒየን (ካኑ) ያሸነፈበት ነበር፡፡
ሰውየው እ.ኤ.አ በ2002 ከሥልጣን ሲወርዱ በምሥራቅ አፍሪካ ያደገ ኢኮኖሚ አላት የምትባለው ሀገራቸው ኬንያ በሙስና ተንኮታኩታና ዕድገቷ ከዜሮ በታች ኾኖ ነበር፡፡ ኬንያን ለሩብ ምዕተ ዓመት ያስተዳደሩት ‹ትልቁ አምባገነን› ዳንኤል አራፍሞይ በ95 ዓመታቸው በሞት ሲለዩ ስማቸው በመሪነት ብቻ አይታወስም፡፡ በሙስና፣ በጨቋኝነትና ከዜሮ በታች የኾነ ኢኮኖሚን ለሀገራቸው በማውረስም ጭምር እንጂ፡፡ ነፍስ ይማር!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe