ዳጋ እስጢፋኖስ – የመነነው ገዳም!

ዳጋ ዝምተኛ ገዳም ነው፡፡ እንደ ሌሎቹ ገዳማት ምዕመናን ሆ.. እያሉ ለንግስ እንዲሄዱለት የሚቀሰቅስ ገዳም አይደለም፡፡ ጸጥታውንና እርጋታውን ይፈልገዋል፡፡ ከካህናቱ ጸሎት፣ ከአዕዋፍቱ ዝማሬ፣ ከጣና ውኃ ግምሻሬ ያለፈ ድምጽ አይፈልግም፡፡ ሰው ለጸሎት እንጂ ለሆታ፣ ለሱባኤ እንጂ ለእልልታ እንዲሄድለት አይሻም፡፡ የውጭ ቱሪስቶች ከሚገረሙባቸው ነገሮች አንዱ ይህ ነገሩ ነው፡፡
.
ከዓለም የራቀ እውነተኛ ገዳም ነው፡፡ ዙሪያውን በባሕር የታጠረና ከአዕዋፍት ድምጽና ከሐይቁ የማዕበል ድምጽ በቀር ምንም የማይሰማበት፣ ሥራ፣ ትምህርት እና ጸሎት አንድ ሆነው የተገመዱበት ገዳም ነው – ዳጋ፡፡ በገዳሙ ከሚገኙት በላይ በአውሮፓ አብያተመጻሕፍት ተበትነው የሚገኙት መጻሕፍቱ የገዳማውያኑን ዕውቀትና ትጋት ይመሰክራሉ፡፡ ገዳማውያኑ ከጠዋትና ከማታው ጸሎት በሚተርፈው ጊዜያቸው አትክልት ይተክላሉ፣ ፍራፍሬ ያመርታሉ፣ ከዚያም አልፈው ዳጋን የተሳለመ ቱሪስት ሳይገዛው የማይወጣውን ቢለብሱት የሚሞቅ፣ ቢያለብሱት የሚያስመርቅ ጋቢ ይሰራሉ፡፡
.
የተመሰረተው የሐይቅ እስጢፋኖሱ የአቡነ ኢየሱስ ሞአ ደቀ መዝሙር እና የአጼ ይኩኖ አምላክ ወንድም በነበሩት በአቡነ ኂሩተ አምላክ በ1268 ዓ/ም ነው አሉ፡፡ ዳጋ የኢትዮጵያ ታሪክ ማዕከል ነው፡፡ ከመካከለኛው ዘመን መጀመሪያ አንስቶ ነገሥታቱ፣ መኳንንቱ፣ ጳጳሳቱና ምዕመኑ የሀገሪቱ ታሪክ ባለ አደራ አድርገውታል፡፡ የመስቀሉን ክፋይ ጨምሮ አያሌ ንዋየተ ቅድሳትን፣ የነገሥታት የወግ ዕቃዎችን፣ ካባዎችንና አክሊሎችን በክብር ጠብቆልናል፡፡ የአጼ ዘርዓ ያዕቆብ፣ የአጼ ሱስንዮስ እና የአጼ ፋሲለደስ አጽም የሚገኘው በዚሁ ገዳም ነው፡፡ አጼ ዘድንግልም ያደገውና በኋላም የተቀበረው በዚሁ በዳጋ ደሴት ነው፡፡ ገዳሙ በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነገሥታቱና የንጉሣውያን ቤተሰቦች መቃብር ነበር፡፡ በሀገሪቱ የደረሱ የእርስ በርስ ጦርነቶችና ወረራዎች ወደ ገዳሙ ባለመዝለቃቸው ከ800 ዓመታት በላይ የተጠበቁ ቅርሶችን አቅፎ ይዟል፡፡
.
ከአጼ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመን ጀምሮ እየተሰራ ሲጠገን፣ እየፈረሰም ሲሰራ የኖረው ይህ ገዳም ሙሉ በሙሉ በምስጥ ተበልቶ በመፍረሱ የአማራ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በጥንታዊው ዲዛይኑ መሰረት እንደገና መልሶ ለመስራት ስራ ጀምሯል፡፡ ስራው በተጀመረበት ወቅት ታዲያ አከራካሪ የነበረ አንድ ዐብይ ጉዳይ ተፈጥሮ ነበር፡፡ ይኸውም ጥንታዊው የገዳሙ ዲዛይን ምን ዓይነት ቅርጽ ነበረው የሚለውን የሚመልስ መዝገብ አለመገኘቱ ነበር፡፡ ይህን ጥያቄ ለመመለስም የተሞከረው የቤተክርስቲያኑን ጥንታዊ መሰረት በመቆፈር የወለሉን ቅርጽ ማግኘትና ከወለሉ ተነስቶ የግድግዳውንና የጣራውን ቅርጽ መገመት ነበር፡፡
.
የገዳሙ ማኅተም ብዙ እንቆቅልሾችን ፈቷል፡፡ ከመቶ ዓመታት በፊት ይህ ጥያቄ እንደሚመጣ ቀድሞ የተገለጠላቸው ጠቢባነ ዳጋ ጥንታዊውን የቤተክርስቲያኑን ዲዛይን በዚህ ማኅተም ላይ በንድፍ አስቀምጠውልን ኖሯል ለካ ያለፉት፡፡ ማኅተሙን ያዘጋጀው ጠቢብ ለመልሶ ግንባታ እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ሦስት ነገሮችን ያካተተ መረጃ ጥሎልን አልፏል፡፡ የጣራው ቅርጽና ዓይነት፣ የበሮቹ ቅርጽና ዓይነት እንዲሁም የቤተክርስቲያኑን መልክና ቅርጽ የያዘ መረጃ፡፡ ቤተክርስቲያኑ የጎንደሩ ደብረ ብርሃን ሥላሴ መልክ ነው የነበረው፡፡ ይህም በገዳሙ ትውፊት ‹ዳጋ እስጢፋኖስ ጥንት የደብረ ብርሃን ሥላሴን ይመስል ነበር› እየተባለ ከሚነገረው ቃላዊ ተረክ ጋር ተስማሚ ነው፡፡ ያ ጠቢብ ንድፉ የዳጋ መሆኑን ለማመልከት የዓሣ ምልክትን ከስሩ አስቀምጧል፡፡ ደብሩ በባሕር ላይ ነው ማለቱ ነው፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe