‹ድምፄ ወጣት የነበረኩ ጊዜ የነበረኝን ያህል እንዳልሆነ ይታውቀኛል›

እውነተኛ ስሙ ዓሊ መሀመድ ሙሳ መሆን ነበረበት፡፡ የሚጠራውና በሙዚቃ ስራዎቹ የሚታወቀው ግን ‹‹ዓሊ መሀመድ በራ›› ተብሎ ነው፡፡ ፓስፖርቱ ላይ ሳይቀር የገባቸው ‹‹ቢራ›› የምትለዋ ስም ከመደበኛው የቢ መጠጥ ጋር ምንም ግንኙነት የላትም፡፡ ከፀሐይ መውጫ የፈለቀው ይህ ምስራቃዊ ድምፅ ሁሌም በየማለዳው አዲስ ፀሐይ ስትወጣ እየተመለከተ ነው ያደገው፡፡ አባቱ አቶ መሀመድ ሙሳ የቴክኒክ ትምህርት እንዲማር አልያም አናፂ እንዲሆን ነበር ምኞታቸው፡፡ እሱ ግን የኦሮሚኛ ሙዚቃ አናፂ  ነው የሆነው፡፡

ከህንዶች ዋሽንትና ከአረቦች አዛን ጋር የሚመሳሰል የሐረር ኦሮሞ ቅላፄ ያለው ዓሊ በኦሮሚኛ ሙዚቃ ውስጥ ምስጢራዊ ስሜትን ትቶ የሚያልፍ ድምፃዊ ነው፡፡ በረዥሙ የከተማችን ሆቴል ኦ ፖል ሰባተኛ ፎቅ ባለፈው ቅዳሜ መቅረፀ ድምፃችንን ይዘን ወደ ክፍሉ ስንገባ ከበር ላይ ነው የተቀበለን፡፡ በቢጃማ በነጠላ ጫማ ሆኖ ዘና ብሎ ሶፋ ላይ የተቀመጠው ዓሊ ውይይታችንን ስንጀምር አሁን አሁንም ከሚጮኸው ስልኩና ከሚያጨሰው ሲጋራ በቀር ትረካውን አላቋረጠም ነበር፡፡ ከዓሊ ጋር በሁለት ሰዓታት በላይ ያደረግነው ቆይታ ይህንን ይመስላል

ቁምነገር፡- እስኪ ከስምህ እንጀምር?

ዓሊ፡- ስሜ ያው የታወቀ ነው፡፡

ቁምነገር፡፤

ቁም ነገር፡- እውነተኛ ስምህ ግን አሊ መሀመድ መሠለኝ?

አሊ፡- ልክ ነህ፤ አሊበራ የሚለው የአርቲስትነት ስሜ ነው፡፡ ትክክለኛ ስሜ እንደውም አባቴ ያወጣልኝ አሊ መሀመድ ሙሳ ነው፡፡ አሊ የእኔ ስም፤ መሀመድ አባቴ ነው፤ ሙሳ ደግሞ አያቴ ነው፡፡

ቁም ነገር፡- አሊቢራ የሚለው ስም ታዲያ እንዴት መጣ?

ዓሊ፡- ቢራ የሚለውን ስም ያገኘሁት የዛሬ 40 ዓመት ገደማ ነው፡፡ በወቅቱ ድሬዳዋ እያለሁ ኡርጂ በኩልቻ የሚባል አንድ የሙዚቃ ባንድ ነበር፡፡ሌላ አሊ የሚባልም ሙዚቃ መሣሪያ የሚጫወት አርቲስት ነበር፡፡ ከዚያ በባንዱ ውስጥ ስዘፍን እኔን ከእነሱ ለመለየት አንድ ስም መስጠት ነበረባቸው፡፡ በወቅቱ እዚያ ባንድ ለመጀመሪያ ጊዜ ገብቼ የዘፈንኩት ‹ቢራ ዳ ብሬ› የሚል ዘፈን ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ ‹ቢራ› የሚለው የእኔ ስም መለያ ሆነና አሊቢራ ሆንኩ፡፤ ፓስፖርቴን ራሱ ዓሊ ቢራ መሀመድ ቢራ ነው የሚለው፡፡

ቁም ነገር፡- ወደ ሙዚቃ ዓለም ከመግባትህ በፊት መምህር ነበርክ አይደል?

አሊ፡- አዎ ድሬዳዋ እያለሁ አረብኛ ቋንቋ እማር ስለነበር በአከባቢያችን ያሉ ህፃናትን ሰብስቤ አረብኛ አስተምር ነበር፡፡

ቁምነገር፡- ትምህርትህን እስክ ስንተኛ ክፍል ነው የተማርከው?

ዓሊ፡- እኔ ፍላጎቴ ሙዚቃ መጫወት ስለነበር ብዙም አልገፋሁበትም፤ እስከ ስምንተኛ ክፍል ብቻ ነው የተማርኩት፡፡ አባቴ ግን ወይ በትምህርቴ እንድገፋ አለበለዚያ የቴክኒክ ትምህርት ተምሬ ባለሙያ እንድሆን ነበር የሚፈልገው፡፡ ብዙም አልተሳካለትም፡፡ ያኔ ፍላጎት እንደ እሱ ፍላጎትማ ወይ መካኒክ አለበለዚያ አናጢ እንድሆን ነበር ምኞቱ፡፡

423 kumneger
423 kumneger

ቁምነገር፡- እሳቸው በምን ስራ ላይ ነበር የተሠማሩት?

ዓሊ፡- እሱ በአብዛኛው የህንፃ ብረቶችን ነበር የሚሰራው፡፡ ብረታ ብረት መስራት ያውቃል፡፡ የውሃ ቧንቧ ስራም  ያውቃል፡፡

ቁምነገር፡- ብዙ ጊዜ ስለ አባትህ ብቻ ነው የምትናገረው፤እናትህስ?

ዓሊ፡- ጥሩ ጥያቄ አመጣህ፤እናትና አባቴ የተለያዩት እኔ የሶስት ዓመት ልጅ እያለሁ ነው፡፡ እንደተለያዩ በእኔ ጉዳይ ፍ/ቤት ድረስ ተካሰው ስለነበር መጨረሻ ላይ እኔን አባቴ እንዲወስደኝ ተፈረደለት፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እንግዲህ የማውቀው አባቴን ብቻ ነው፡፡ እናቴ ከዚያ በኋላ ወደ ከተማ ሄዳ ሌላ ባል አግብታ ልጆች ወልዳ መኖር ጀመረች፡፡ አባቴ ግን ከዚያ በኋላ ሌላ ሚስትም አላገባም ከእኔም ሌላ ልጅ አልወለደም፡፡

ቁምነገር፡- እናትህን አታውቸውማ?

ዓሊ፡- ልክ በ11 ዓመቴ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ ያየኋት፡፡ ከዚያ በኋላ አልተገናኘንም፡፡ ስለዚህ ብዙም ስለ እናቴ አላውቅም፡፡

ቁምነገር፡- አዲስ አበባ እንደመጣህ የተቀጠርከው የት ነው?

ዓሊ፡- ክቡር ዘበኛ ነው የተቀጠርኩት፡፡ የዛሬ 40 ዓመት ገደማ ማለት ነው፡፡

ቁምነገር፡- በወቅቱ እነማን እነማን ነበሩ?

ዓሊ፡- ጥላሁን ገሠሠ፣ብዙነሽ በቀለ፣ማህሙድ አህመድ፣ተዘራ ሀይለሚካኤል፣ተፈራ ካሳ፣እሰቱ ተሰማ፣ብዙ ናቸው፡፡

ቁምነገር፡- አንተ የተቀጠርከው ኦሮምኛ ለመጫወት ብቻ ነው ወይስ?

ዓሊ፡- በዋንኛነት ኦሮምኛ ተጫዋች ነኝ፣ግን የአማርኛ ዘፈኖችም እጫወት ነበር፡፡ የዜማ ድርሠቶችም እሠራ ነበር፡፡ እንደውም አንድ ስድስት ያህል የአማርኛ ዘፈኖችን ሠርቼ ነበር፡፡

ቁምነገር፡- ለማን ሰጠህ?

ዓሊ፡- ሁለቱን የአማርኛ ዘፈኖች እኔ ራሴ ነኝ የዘፈንኳቸው፡፡ ‹‹ትዝ ትዝ እያለኝ›› የሚለውን ለማህሙድ የጠሠሁት እኔ ነኝ፡፡ ለጥላሁን ገሠሠ ደግሞ ‹‹አዝናለሁ በእድሌ›› የሚለውን ሰጥቼዋለሁ፡፡ ለእሳቱ ተሰማም እንደዚሁ አንድ ዘፈን ሠርቼለታለሁ፡፡ ለሙሉጌታ ሀ/ሚካኤል አንድ የማላስታውሰውን ዜማ ሠጥቼዋለሁ፡፡

ቁምነገር፡- ግጥምስ አትሞካክርም?

አሊ፡-ዜማ ይሻለኛል፡፡ ግጥም እስከዚህም ነኝ፡፡ ጥሩ ግጥም ከሰጡኝ ግጥሙን አንብቤ ከግጥሙ መንፈስ ጋር የሚሄድ ዜማ መስራት ነው የሚቀለኝ፡፡ አብዛኛዎቹን የኦሮምኛ ዘፈኖች ዜማ የሠራሁት በዚሁ መልኩ ነው፡፡

ቁምነገር፡- ለመጀመሪያ ጊዜ የኦሮምኛ ዘፈኖችን በሸክላ ያስቀረፅከው አንተ ነህ?

ዓሊ፡- በኦሮሚኛ ዘፈን ብቻ ሳይሆን እኛ ያን ጊዜ ሽክላ ስናስቀርፅ ኢትዮጵያ ውስጥ ሸክላ ብዙ አይታወቅ ነበር፡፡በ1956 ዓ.ም ገደማ ይመስለኛል ድሬደዋ ውስጥ እኔ አሊሽጎርና ሌላ አንድ ልጅ ሆነን ነው በአንድ አረብ ኩባንያ አማካኝነት ግሪክ ወይም ቤሩት የተቀረፀው፤ ሸክላ ማጫወቻ ራሱ የዚያን ጊዜ ብዙ ሰው ቤት የለም፡፡ ከአምስትና ከስድስት ዓመት በኋላ ነው አዲስ አበባ ውስጥ ሸክላ በስፋት መታተም የተጀመረው፡፡ እኔ እዛ አሳትሜ መጥቼ እዚህ ሌላ አሳትሙልኝ ስል የኦርምኛ ዘፈን ገዢ የለም በሚል አይፈልጉም ነበር፡፡

ቁምነገር፡- ከሀገር ከመውጣትህ በፊት ምን ያህል ካሴቶችን አሳትመሀል?

ዓሊ፡- ስድስት ወይም ሰባት ካሴት ይሆናል ያሳተምኩት፡፡ ቀም ሲል ግን በወቅቱ ሸክላ የሚያሳትሙ የግል ኩባንያዎች ጋር የኦሮሞ ዘፈኖችን ለማሳተም ፈቃደኝነት ስላልነበሩ በግሌ በጊታር የተለያዩ ዘፈኖችን እየተጫወትኩና እየዘፈንኩ ለተለያዩ ሰዎች አሠራጭ ነበር፡፡ እነዛ ሁሉ ዘፈኖች በትክክለኛ መንገድ ስላልተቀረፁ ነው እንጂ ቁጥሩ ብዙ ነው፡፡ የዘፈንኳቸው ዘፈኖች ከዚህ ሀገር ስሄድ በተለያዩ ሰዎች እጅ ያለውን ሁሉ ባለቤቴ ስትሰበስብ ወደ 17 ያህል ካሴቶች ይሆኑ ነበር፡፡

ቁምነገር፡- ናይት ክለብ የት የት ሰርተሃል?

ዓሊ፡- በክቡር ዘበኛ ሶስት ዓመት ሠርቼ እንወጣሁ የተለያዩ ቦታዎች ሠርቻለሁ፡፡ መጀመሪያ ሙዚቃንም ትቼ ወደ አዋሽ ነው የሄድኩት፡፡ አዋሽ የውሀ ማውጫ ማሽን ያለበት ዝቅተኛ ቦታ ነበር፡፡ የእዛ ማሽን ሀላፊ ሆኜ ለሁለት ዓመት ያህል ሠራሁ፡፡ ግን እዛ በነበርኩበት ወቅት የሙዚቃ ፍላጎቱ እያለ ሲመጣ አንድ ጊታርና አኮርዲዮን ስለነበረኝ ስጫወት የሚሰሙ ሰዎች ሲያደንቁ እንደገና ወደ አዲስ አበባ ተመለስኩ፡፡ አዲስ አበባ እንደመጣሁ የገባሁት ካቴድራል ት/ቤት ማታማታ እንግሊዝኛ እየተማርኩ ሀራምቤ ሆቴል መዝፈን ጀመርኩ፡፡ እዛ ስጫወት በወቅቱ የደርግ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት እንደነጀነራል አማን ሚካኤል አንዶም፣እና ከተማ ይፍሩ ሌሎቹም ይመጡ ነበር፡፡ ሽልማት አገኝ ነበር፡፡

ቁምነገር፡- የማንን ዘፈን ነበር የምትጫወተው?

ዓሊ፡-የራሴም የኦሮምኛ ዘፈን አለኝ፣ሱዳንኛም እጫወት ነበር፡፡

ቁምነገር፡- ብዙዎች የኦሮሚኛ ወጣት ድምፃውያን ያንተን ዘፈኖች በማጎራጎር ወደ ሙዚቃው ዓለም እንደገቡ ነው የሚናገሩት፡፡ አንተስ አርአያዎቼ የምትላቸው በወቅቱ የነበሩት የኦሮሚኛ ድምፃውን እነማንናቸው?

ዓሊ፡- ብዙ አሉ፡፡ የእኔ ታላላቆች ጥሩ የሚዘፍኑ ድምፃውያን ነበሩ፡፡ ከነዚህም ውስጥ እኔ የማደንቀውና ስከተለው የነበረው ኡርጂ በከልቻ ውስጥ ይዘፍን የነበረው አሊ ሽጎርን ነው፡፡ የእኔ አርአያ እሱ ነው፡፡ ወደ ክቡር ዘበኛ ስመጣ ደግሞ እነ ጥላሁን ገሠሠና ማህሙድ አህመድን ነበር የምከተለው፡፡

ቁምነገር፡-መጀመሪያ ወደ ውጪ ሀገር የሄድከው የት ነው?

ዓሊ፡- ካሊፎርኒያ ነው በ1977 ዓ.ም ገደማ የሄድኩት፡፡

ቁምነገር፡-የሙዚቃ ትምህርት መማር ዕድል አልገጠመህም?

ዓሊ፡- ተምሬአለሁ፡፡ እንደሄድኩ አንድ የሙዚቃ ኮሌጅ ውስጥ ገብቼ ለአምስት ዓመታት ከተማርኩ በኋላ በአሶሺየት ዲግሬ ነው የተመረቅሁት፡፡

ቁምነገር፡- የሙዚቃ ሥራ እየሰራህ ነበር የምትማረው?

ዓሊ፡- አቁሜ ነበር፡፡ በግል ምክንያት ሥራ አልሠራም ነበር፡፡

ቁምነገር፡-የመጀመሪያ ባለቤትህ ስዊዲናዊት ነበረች? እንዴት ተገናኛችሁ?

ዓሊ፡- አዲስ አበባ ነው የተገናኘነው፡፡ የስዊድን ዲፕሎማት ነበረች፡፡ ራስ ሆቴል ከነማህሙድ ጋር ናይት ክለብ ስሰራ ነው የተዋወቅነው፡፡ እኔ ስጫወት እየመጣች ታይ ነበር፡፡ ከዚያ ተቀራረብንና አንድ ሁለት ቀን ራት በላን፡፡ ከራስ ሆቴል ሌላ ቬነስ ክለብም እሠራ ስለነበረ እዛም እመጣች ታየኝ ነበር፡፡ ከዚያ ሁለታችንም ጋር ፍላጎቱ አደረብንና አስፈላጊውን ነገር አድርገን ተጋባን /ሳቅ/

ቁምነገር፡- በማዘጋጃ ቤት ነው የተጋባችሁ?

ዓሊ፡-በወቅቱ ልደታ አከባቢ አንድ የሙስሊሞች ፍ/ቤት ነበር፡፡ እዛ ነው ሄደን በ1975 ዓ.ም የተጋባን፡፡

ቁምነገር፡- ሙስሊም ነች እሷ?

ዓሊ፡- አይደለችም፡፡ እሷ ምንም ሀይማኖት አልነበራትም፡፡ ቤተሰቦቿ ግን ክርስቲያኖች ነበሩ፡፡

ቁምነገር፡-    በወቅቱ የኮር ዲፕሎማቲክ መኪና ነበር የምትነዳው ይባላል?

ዓሊ፡- የእሷ እኮ ነው! ተጋብተን አብረን መኖር መኪናዋን ሰጠችኝ፡፡ እሷ ትዘው የነበረውን መኪና የኮር ዲፕሎማቲክ መኪና ስለነበር ያንን ይዤ ከተማ ውስጥ መዞር ጀመርኩ፡፡ አንድ ጊዜ ታዲያ ምን ተፈጠረ መሰለህ? ራስ ሆቴል በር ላይ ቆሜ ሳለ አንድ ትራፊክ መጥቶ አንተ እኮ ይህንን መኪና መንዳት አትችልም አለኝ፡፡ ለምን? ስለው የኮር ዲፕሎማቲክ መኪና ነው አለኝ፤ ታዲያ አንተ ምን አገባህ የባለቤቴ መኪና ነው ስለው፤ ይዤህ ጣቢያ እሄዳለሁ አለ፡፡ ከዚያ አለቅም ሲለኝ እሷ ጋር ደወልኩና ነገርኳት፡፡ እሷ ደግሞ ስዊዲን አምባሳደር ጋር ደውላ ስለ ሁኔታው ስትነግረው እሱ በፍጥነት ለፖሊስ ሀላፊዎች ትራፊኩን ሊበሉት ደረሱ፡፡ እንዴት የኤምባሲ መኪና ትይዛለህ አሉት፡፡ አደጋ ሳያደርስ እንዴት ትይዘዋለህ? ሲሉት ተኩራርቼ ወጣሁ /ሳቅ/

ቁምነገር፡- ከዚያ አሜሪካ አንድ ላይ ነው የሄዳችሁት?

ዓሊ፡- የዚህ ሀገርን ሥራ ስትጨርስ መንግስታቸው በየሀገሩ ለአራት ዓመት ብቻ ስለነበረ የሚመድባቸው አሜሪካ ስትመደብ አንድ ላይ ሄድን፡፡ አሜሪካ አራት ዓመት ተጨመረላት፡፡ እኔ የዛን ጊዜ ትምህርቴን እየተማርኩ ነበር፡፡ ከዚያ ተያይዘን ወደ ስዊድን ቆየን፡፡ ከዓመት በኋላ ሳውዲ አረቢ ወደ ዘጠኝ ወር ያል ከቆየን በኋላ እኔ ሀገሩ ስላልተስማማኝ ወደ ስዊድን ተመልሼ ቋንቋና የጎልማሶች ትምህርት እየተማርኩ ስራ ስሰራ ቆየሁ፡፡ በ1983 ዓ.ም ላይ ተፋታን፡፡

ቁምነገር፡- ልጅ አልወልዳችሁም?

ዓሊ፡-አልወለድንም፡፡

ቁምነገር፡- የዛሬ 14 ዓመት ደርግ ሲወድቅ ሲል መጥተህ ነበረ፤ ምን ያህል ነበር የቆየኸው?

ዓሊ፡- ለ12 ቀን ብቻ ነበር የቆየሁት፤ ወቅቱ ጥሩ አልነበረም፡፡ ኢህአዴግ አዲስ አበባ ለመግዛት ሳምንት ብቻ የቀረው ጊዜ ነበር፡፡ እኔ ከአዲስ አበባ እሁድ ስመለስ መንግስቱ ሀይለማርያም ማክሰኞ ጠፋ ተባለ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቋሚ መኖሪያዬን ካናዳ አደረግሁና የሙዚቃ ስራዎችን ብቻ መስራት ጀመርኩ፡፡

Ali Birra and Mohamud Ahmed
Ali Birra and Mohamud Ahmed

ቁምነገር፡- ስንት ካሴቶችን ሠራህ?

ዓሊ፡– አንድ አምስት ይሆናሉ፡፡ ከዚያ ሌላ ከአፍሪካ በቀር ሌሎቹ አህጉሮችን በሙሉ ተመላልሼ የሙዚቃ ስራዎችን አቅርቤአለሁ፡፡ በዓመት ውስጥ ለዘጠኝ ወር ያህል ቤቴ አልቀመጥም ነበር፡፡ ኮንሠርቶች ይበዙ ነበር፡፡

ቁምነገር፡- አሜሪካ እያለህ አንድ ሽልማት ተሰጥቶህ አልቀበልም ብለህ ነበር፤ ለምንድነው?

ዓሊ፡- ሽልማቱ የአፍሪካ ሜሪት አዋርድ የሚባል ነው፡፡ ወቅቱ ትንሽ ጥሩ ስላልነበርኩና የግል ምክንያት ስለነበረኝም ሽልማቱን አልቀበልም አልኩ፡፡

ቁምነገር፡- ሌሎች ያገኘሃቸው ሽልማቶች የሉም?

ዓሊ፡- በጣም ብዙ ሽልማቶች ከተለያዩ የኦሮሞ ኮሚኒቲ አባላት ተሰጥቶኛል፡፡ ከ32 በላይ ይሆናሉ፡፡

ቁም ነገር፡- ከ40 ዓመታት በላይ በሙዚቃ ውስጥ ስትቆይ ድምፅህ ብዙም ለውጥ የለውም፤እንዴት እንዲህ ሊሆን ቻለ?

ዓሊ፡- እግዚአብሔር ይመስገን የእግዚአብሔር ስጦታ ነው ማለት ነው የምችለው፡፡ ፍላጎቱ አለኝ፡፡ ሁሌም እዘፍናለሁ፤ሌላ ምክንያት የለኝም፡፡ አንድ ዘፋኝ ራሱን ድምፁን ከጠበቀ መጠበቅ የሚችል ይመስለኛል፡፡ በሌላ በኩል ግን እድሜ እየጨመረ ሲመጣ እንደድሮው የግድ ካልዘፈንኩ ማለት አይገባም፡፡ ብዙ ሰው ድምፅህ ያው ነው ይሉኛል፡፡ እኔ ግን ድምፄ ወጣት የነበረኩ ጊዜ የነበረኝን ያህል እንዳልሆነ ይታውቀኛል፡፡ ግን ብዙ አይደለም ለውጡ፡፡

ቁምነገር፡-  ‹‹አማለ.ለ.›› የሚለውን ዘፈን ከማህሙድ ጋር የምትጫወተው ዘፈን አለ፤ እንዴት ሠራችሁት?

ዓሊ፡- ዘፈኑ የድሮ የገጠር የኦሮሞዎች ዘፈን ነበር፡፡ አንድ ወቅት ላይ የሀገር ፍቅር ሙዚቀኞች ወደ ክፍል ሀገር ሲሄዱ ህዝቡ ውስጥ የሰሙትን ጥሩ ዜማ ይዘው ይመጡ ነበር፡፡ ይሄም ዘፈን በዚህ መልኩ የመጣ ነው፡፡ ራስ ሆቴል ናይት ክለብ ከማህሙድ ጋር ስንሰራ ዘፈኑን አመጣሁና እኔ በኦሮሚኛ ስጫወት እሱ በአማርኛ እንዲጫወተው አደረኩ፡፡ ዘፈኑ በዚህ መልኩ ሲቀርብ ብዙ አድናቆት ስለነበረው፤ በዛው ዓመት ሙሉ ካሴት ሳወጣ ይህንን ዘፈን ለሁለት ነበር የተጫወትነው፡፡ የሚገርምህ ካሴቱ ያሳተመው ራሱ ማህሙድ ነበር፡፡

ቁምነገር፡ አሁን በቅርቡ ያወጣኸው ካሴት ምንያህል ጊዜ ፈጀብህ?

ዓሊ፡- ብዙ ጊዜ ወስጄ የሠራሁት አይደለም፡፡ እኔ ወደዚህ ልመጣ አንድ አምስት ሲቀረኝ ነው የወጣው፡፡ አጠቃላይ ሥራውን ግጥም ከተለያዩ ባለሙያዎች ሰብስቤ ዜማውን ሁሉንም እኔ ነኝ የሠራሁት፡፡

ቁምነገር፡- ከማጊ አሮን ጋር እንዴት ተገናኛችሁ?

ዓሊ፡- ማጊ መጀመሪያ ስዊድን ነበር የምትኖረው፡፡ ተገናኘነው ስዊድን ነው፡፡ ቀደም ሲል ደርግ እንደወደቀ ገደማ አንድ ካሴት አንድ ላይ አውጥተን ነበር፡፡ ከዚያ እሷ አሜሪካ ስትኖር እኔ ካናዳ መኖር ጀመርኩ፡፡ ከዛ በኋላ ተገናኝተን አንደበፊቱ ስራ ለመስራት አልቻልንም፡፡ አሁን ግን በቅርቡ የመገናኘት ዕድሉን ስናገኝ ነው ይህንን ካሴት የሠራነው፡፡ ከሙዚቃው ሌላ እሷ ዲዛይነር ነች፡፡ በፋሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ነው የምትንቀሳቀሰው፡፡

ቁምነገር፡- ‹‹ኦሮሚያ›› የሚለውን ቃል ለመጀመሪ ጊዜ በዘፈን ውስጥ የገለፅከው አንተ እንደሆንክ ይነገራል፡፡ ትክክል ነው?

ዓሊ፡- አይደለም፡፡ ከእኔ በፊት የተለያዩ የኦሮሞ ዘፈኞች ብለውታል፡፡ በፊት የኦሮሚኛ ዘፈን ካሌትም ሆነ ሸክላ በማይታተምበት ወቅት በቴፕ እየባዙ የሚሸጡ ካሴቶች ውስጥ ሌሎች ዘፈኞች ፍነውበታል፡፡ እኔ ኦሮሚያ የሚለው ዘፈን የዘፈንኩት 1983 ዓ.ም ላይ ነው፡፡ ከእኔ በፊት ግን ተዘፍኗል፡፡ እኔ የማውቃቸው እንኳን ሶስት የኦሮሚኛ ዘፈኞች ዘፍነውታል፡፡

ቁምነገር፡- ከድሬደዋ ወደ አዲስ አበባ ከመምጣትህ በፊት ታስረህ ነበር፤ ለምንድን ነው?

ዓሊ፡- በወቅቱ እኛ በኡርጂ በኩልቻ ባንድ የኦሮምኛ ዘፈኖችን ስንጫወት የመንግስት ሰዎች ደስ አይላቸውም ነበር፡፡ እንደማንኛውም ዘፈን እንድንጫወት አይፈቀድም ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ እኛ ዝም ብለን ስንዘፍን መሣሪያዎቻችንን ሁሉ ሰባበሩብንና አሠሩን፡፡ ከዚያ እኔ በዋስ ከወጣሁ በኋላ እንኳን ድሬደዋ ውስጥ የትም እንዳልንቀሳቀስ ተደርጌ ግዞት ላይ ነበርኩ፡፡ ሙዚቀኞቹ ሁሉ ተጎድተው ነበር፡፡ የንጉሱ ባለስልጣናት ኦሮሚኛ የሚጫወቱትን ፖለቲካ ነው እያሉ ያሳድዱ ነበር፡፡

ቁምነገር፡- በሀረር ራዲዮ ጣቢያ የኦሮሚኛ ፕሮግራም አልነበረም እንዴ?

ዓሊ፡- ንጉሱ ሀረር ላይ ራዲዮ አቋቁመው የኦሮሚኛ ፕሮግራም ያስጀመሩት እኮ ቀደም ሲል ከሱማሊ ሌላ የኦሮሚኛ ራዲዮ ጣቢያ የሚያስተላልፈው ፕሮግራም ስለነበር ነው፡፡ ከ40 ዓመታት በፊት ነበር ኦነግ የራዲዮ ፕሮግራም ከዚያ የሚያስተላለፈው፡፡ ህዝቡ ያን ጣቢያ ይከታተል ስለነበር ነው ሀረር ላይ ተመሳሳይ ጣቢያ የተከፈተው፤ ዘፈኖችም በወቅቱ እኛ እንዘፍን የነበረውን ነበር የሚተላለፈው፡፡ በኋላ ያ ሁሉ ችግር ከደረሰብን በኋላ ነው እኔ ከድሬደዋ አዲስ አበባ መጥቼ ክቡር ዘበኛ የተቀጠርኩት፡፡

ቁምነገር፡- ምን ያህል ቋንቋዎችን ታውቃለህ?

ዓሊ፡- ወደ ስምንት ቋንቋዎችን አውቃለሁ፡፡ ኦሮሚኛ፣አማርኛ፣አረብኛ፣እንግሊዘኛ፣ሐረሪ፣ሶማልኛ፣ስዲሽ፣ትንሽ ትንሽ ደግሞ ፊሊፒኖ እችላለሁ፡፡

ቁምነገር፡- የፊሊፒንስን ቋንቋ እንዴት ለመድክ?

ዓሊ፡- አሁን አብራኝ የምትኖረው ጓደኛዬ የፊሊፒንስ ዜጋ ናት፡፡ ለ11 ዓመት ያህል አብረን ስለሆንን ስታወራ በማዳመጥ ብቻ ነው የለመድኩት፡፡

ቁምነገር፡- ከረጅም ዓመት በኋላ ነው ሀገር ቤት ወጥተህ የአዲስ አመትን ያከበረከው እንዴ ነበር በዓሉ?

ዓሊ፡- በጣም በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡ ሁኔታው ሁሉ ያን ጊዜ ድሮ እዚህ ሀገር እያለሁ ያሳለፍኩትን ትዝታ ነው የቀሰቀሰብኝ፡፡ ውጪ ሀገር አዲስ ዓመት ብናከብርም የዚህን ያህል ስሜት አይፈጥርም፡፡ ብዙ ኢትዮጵያውያን ያሉበት ከተማ ካልሆንክ በዓል በዓል አይመስልም፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ እኔ የኖርኩበት ከተማ ውስጥ ያሉት ሀበሾች ጥቂት መሆናቸው ብቻ ሳይን ተራርቀው ስለሆነ የሚኖሩት እዚህ እንዳለው አናከብርም ነበር ለማለት እችላለሁ፡፡

ቁምነገር፡- ንጉሱ ባሉበት ዘፈኖችህን ያቀረብክበት አጋጣሚ አለ?

ዓሊ፡-ብዙ ጊዜ አለ፡፡ ክቡር ዘበኛ በነበርኩበት ወቅት ኢዮቤልዩ ቤተመንግስት እየተጠራን እንዘፍን ነበር፡፡ አንድ ጊዜ የማስታውሰው በአንድ ጊዜ የሮማኒያ መሪ ይመስለኛል መጥቶ ለእነሱ ሙዚቃ ለማቅረብ የሄድን ጊዜ ሁላችንም መሣሪያዎችችንን ገጥመን ስንጨረስ እኔ ቀደም ሲል ጫት እቅም ስለነበር ስዓት ሲደርስ በኪሴ ይዤ ነበር የሄድኩት፡፡ በኋላ ሙዚቃው እስኪጀምር ወደ ሽንት ቤት ሄጄ ስቅም መቶ አለቃው መጣ፡፡ ከዚያ ሊያየኝ ተቆጣ ‹‹እንዴት ቤተመንግስት ውስጥ ጫት ትቅማለህ›› አለኝ፡፡ እኔ በወቅቱ ቤተመንግስት ውስጥ መቃም እንደሚቻልና እንደማይደቻል አላውቅም /ሳቅ/ ድሬደዋ እያለሁ ምግብ ከበላን በኋላ ጫት መቃም የተለመደ ስለሆነ እንደዛ መስሎ ነው የቃምኩት አልኩት፡፡ ከእዛ ትቶኝ ሄደ፤

ቁምነገር፡- ትርፍ ጊዜህን በምን ታሳልፋለህ?

ዓሊ፡- የአሁን እና የድሮው ትርፍ ጊዜ የተለያየ ነው፡፡ ድሮ የተለያዩ ስፖርቶች መመልከት እወድ ነበር፡፡ ቅርጫት ኳስ በጣም እወዳለሁ፣ጎልፍ እያለሁ፡፡ አሁን ግን ሙሉ ጊዜዬ ኮምፒውተር ነው የሚወስድብኝ ስራውም ጌሙም እዛው አለ፡፡

ቁምነገር፡- የምትወደው ምግብስ?

ዓሊ፡- ስኳር ህመም ስላለብኝ ከስጋ ይልቅ ወደ አትክልቱ ነው የማዳላው፡፡ አሳና ዶሮ ግን እወዳለሁ፡፡ ጋባዥ ከተገኘ ንገርልኝ /ሳቅ/

ቁምነገር፡- ብዙዎች ከዘፈነካቸው ዘፈኖች ሁሉ ስለ ኦሮሚያ በዘፈንካቸው የትግል ዘፈኖች ያስታውስሃል፡፡ ዘፈኖችን አሁን ስታስባቸው ምን ይሰማሃል?

ዓሊ፡- ሁሉንም ዘፈኖች ደስ እያሉኝ ነው የተጫወትኳቸው፡፡ ሁሉም ከጊዜአቸው አንፃር የሚታዩ ናቸው፡፡ በተዘፈኑበት ወቅት የየራሳቸው ውበት አላቸው፡፡ መጀመሪውኑ ዜማውን ካልወደድኩትን ዘፈን አልጫወትም፡፡ ስለ ኦሮሚያ የተጫወትኳቸው ዘፈኖችም ከወቅቱ አንፃር አስፈላጊ ነበሩ፡፡ በአጠቃላይ በትግል ወቅት በዘፈንኳቸው ዘፈኖች ደስተኛ ነኝ፣አላፍርባቸውም፡፡

ቁምነገር፡- አመሰግናለሁ፡፡

(ምንጭ፡- ቁም ነገር መፅሄት ቅፅ 10 ቁጥር 222 ሕምሌ 1998)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe