“ድርድሩን ህብረቱ ብቻ እንዲመራ እንሻለን፣ ከዚህ ቅንጣት ታክል ዝንፍ አንልም”- ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ

ኢትዮጵያ የግድቡ ሙሌት አንድ ዓመት ቢዘገይ አንድ ቢሊዬን ዶላር እንደምታጣም ነው ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ የተናገሩት፡፡

ከሰሞኑ በዴሞክራቲክ ኮንጎ ሪፐብሊክ ዋና ከተማ ኪንሻሳ በተካሄደው የግድቡ የድርድር ሂደት ግምገማ ላይ ሱዳን ድርድሩ በአፍሪካ ህብረት እንዳይመራ ፍላጎት እንደነበራት የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ ተናገሩ፡፡

ሚኒስትሩ የግመገማውን ሂደት በተመለከተ ዛሬ መግለጫን ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸው ግምገማው ዕሁድ ማታ ነበር የተጀመረው ያሉ ሲሆን ሱዳን የድርድሩን አካሄድ የመቀየር አላማ እንደነበራት ገልጸዋል፡፡

ድርድሩ በአፍሪካ ህብረት እንዳይመራ እና ሌሎች ተዋንያኖች አብረው ድርድሩን እንዲመሩ ይፈልጉ እንደነበርም ነው የተናገሩት፡፡

ግብጽ ይህን “የሱዳንን ሃሳብ ትደግፍ ነበር” ብለዋል ሚኒስትሩ፡

ሆኖም ኢትዮጵያ ይህን አልተቀበለችም፡፡ ታዛቢዎቹ ባሉበት እንዲቀጥሉም ትፈልጋለች እንደ ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ ገለጻ።

“አፍሪካ ህብረት፣ ደቡብ አፍሪካ እና ሎሎቹም ባሉበት እንዲቀጥሉ እንጂ ከህብረቱ ሊቀመንበር እኩል ድርድሩን እንዲያመቻቹ አልፈለግንም” ሲሉም ነው ያስቀመጡት።

“የደቡብ አፍሪካ የታዛቢነት ሚና መቀጠል አለበት” ማለታቸውንም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ድርድሩን የወቅቱ የህብረቱ ሊቀመንበር እና የዲ.አር.ሲ ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ሼስኬዲ በነጻነት እንዲመሩት ጽኑ አቋም እንዳላት ገልጻለች።

ከታዛቢዎች ልምድና ዕውቀት፣ሀሳብ ማግኘት ካለብን ሶስታችንም ተነጋግረን መሆን አለበት በሚል ያሳወቀችም ሲሆን ሼስኬዲ የሃገራቸውንና የህብረቱን ባለሙያዎች በነጻነት ለመጠቀም እንደሚችሉ እና እንደዚህ አድርጉ እንደዚህ አታድርጉ ሊባሉ እንደማይገባ ማሳሰቧንም ነው ሚኒስትሩ የገለጹት።

ግምገማውን ተከትሎ ዲ.አር.ሲ ባለ 9 ነጥብ ረቂቅ መግለጫ አውጥታለች፡፡ ኢትዮጵያ የመግለጫው ሁለት ነጥቦች ማለትም 4ኛው እና 7ኛው ነጥቦች ላይ መጠነኛ የማሻሻያዎች ሃሳቦችን በማቅረብ በረቂቅ መግለጫው የተካተቱት 9ኙም ነጥቦች እንዲጸድቁ ተስማምታለች፡፡

ሆኖም በሱዳን በኩል ሰፊ ለውጥ ነበረ፡፡

በተለይ ለአንድ ቀን ተኩል ያህል ሰፊ ውይይት ከተደረገበት ጉዳይ በተለየ ከሶስቱ ታዛቢዎች ውጭ ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና ወዳጆች ያግዙ የሚል ሀሳብ አቅርባለች ምንም እንኳን ኢትዮጵያ በውይይቱ ያልተነሱ ጉዳዮች ሊካተቱ አይገባም በሚል ኢትዮጵያ ብትቃወመውም።

በረቂቅ መግለጫው ከተካተቱት 9 ነጥቦች 1ኛውን፣ 2ኛውን እና 9ኛውን መቀበላቸውን ግን ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

ኢ/ር ስለሺ “የሱዳን ህዝብ ውሃ አጥቷል፣ ካርቱም ውሃ አጥሯል የሚል ነገር አንስተው ነበር” ብለዋል “ነገሩ ትክክል እንዳልሆነ፣ መረጃ ለመለዋወጥ እውነተኛ ያልሆኑ ክሶችን ማቆም ይገባል” በሚል ምላሽ መስጠታቸውን በመጠቆም።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ በየዕለቱ 90 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ ወደ ሱዳን ወደ ታችኞቹ የተፋሰሱም ሃገራት ይፈሳል፡፡

ይህ ሮዛሪየስ ግድብ ውስጥ ጭምር ውሃ ያላት ሱዳን “እንድትጠማ የሚያደርግ አይደለም፤ ኢትዮጵያ ኃይል ከማመንጨት ውጪ የሱዳን ህዝብ እንዲጎዳ አትፈልግም” እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ።

ሆኖም የግድቡ ሙሌት በዘገየ ቁጥር ለከፍተኛ ኪሳራ ይዳርጋታል፡፡ አንድ ዓመት ቢዘገይ አንድ ቢሊዬን ዶላር ያሳጣታል፡፡

“ኢትዮጵያ በዚህ ግድብ አንድ ዶላር ካገኘች ሱዳን 2 ወይም 3 ዶላር ታገኛለች” ሲሉ ገልጸዋል ኢ/ር ስለሺ።

ድርድሩ በከ15 ቀናት በኋላ የማስቀጠል ፍላጎቶች ነበሩ፡፡ ሆኖም የድርድሩን መሪ ሃሳብ ባለመያዙ ምክንያት መሪው በሚጠሩበት ጊዜ እንዲቀጥል ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

የህብረቱ ሊቀመንበር ሚና ሊሸረሸር አይገባም የሚል አቋም ያላት ኢትዮጵያ ድርድሩ አሁንም ቢሆን እንዲቀጥል ያላትን ፍላጎት ደግማ አሳውቃለች፡፡

ስለሰጠችው ከፍተኛ ትኩረትና ስላደረገችው አቀባበል ኮንጎን ያመሰገኑት ሚኒስትሩ “በአህጉራችን ሙሉ ለሙሉ እንተማመናለን፣ ድርድሩን ህብረቱ ብቻ እንዲመራ እንሻለን፣ ከዚህ ቅንጣት ታክል ዝንፍ አንልም፣ ለናይል ብቻ አይደለም፣ ዛምቤዚም ሌላም አለ” ሲሉ አክለዋል።

“በድርድሩ ያለውን ሁኔታ ከዓባይ በላይ ማየት ይገባል ባይ ነኝ”ም ነው ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ ያሉት፡፡

ሱዳን በአቢዬ ግዛት የተሰማራው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጦር እንዲወጣላት ጠይቃለች፡፡

ሰላም አስከባሪ ጦሩ በመንግስታቱ ድርጅት መሰማራቱን የገለጹት ሚኒስትሩ ጉዳዩ ከውሃ አጠቃቀም ጋርም ይሁን ከግድብ ጋር እንደማይገናኝ እና ኪንሻሳ ላይ በነበረው የግምገማ መድረክ አለመነሳቱንም ነው በመግለጫው ለተገኙት ጋዜጠኞች የገለጹት፡፡

ግድቡን ‘እናጠቃለን’ በሚል ተደጋግመው የሚሰሙ ዛቻዎች እውን ይሆናሉ የሚል ግምት እንደሌላቸውም ተናግረዋል፡፡

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe