የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በእንግሊዝ የእንስሳት ግቢ ውስጥ በነብር ጥቃት ህይወቱ ያለፈውን ወጣት የሚያሳይ አስፈሪ ቪዲዮ ካዩ በኋላ፣ እራሳቸውን ከነብር ጋር ሲታገሉ የሚያሳይ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የተሰራ ቪዲዮ ማጋራታቸው ከፍተኛ ቅሬታና ትችት ቀስቅሷል።
በእንግሊዝ ዮርክሼር የሚገኘው የ23 ዓመቱ ዊሊያም ቻፕማን የተባለ ወጣት በነብር ግቢ ውስጥ በመግበቱ ምክንያት በነብሩ ጥቃት ህይወቱ አልፏል።
የሟች ቤተሰቦች እና የደቡብ ዮርክሼር ፖሊስ ህዝቡ የአደጋውን ቪዲዮ በማህበራዊ ሚዲያ ከማሰራጨት እንዲቆጠብ በጽኑ ጠይቀው ነበር።
ይህ ጥሪ በተደረገ በሰዓታት ልዩነት ውስጥ ዶናልድ ትራምፕ የወጣቱ ጥቃት የሚያሳየውን ተንቀሳቃሽ ምስል በTruth Social አካውንታቸው ላይ ድጋሚ በመፖስት “ከተፈጥሮ ጋር በጭራሽ አትጫወቱ! ፕሬዚዳንት DJT” የሚል ጽሁፍ አስፍረዋል። የቪዲዮውን መለቀቅ ተከትሎ ትራምፕ እራሳቸውን ከነብር ጋር ሲሮጡ፣ ሲታገሉ እና ነብሩን ሲታቀፉ የሚያሳይ በኤአይ የተሰራ የሀሰት ቪዲዮ “The Lion Sleeps Tonight” ከሚለው ሙዚቃ ጋር አያይዘው አቅርበዋል።
የሟች ዊሊያም ቻፕማን ቤተሰቦች በሰጡት መግለጫ የዚህ አይነት አሰቃቂ እና ስሜት የሚጎዳ ምስል በሶሻል ሚዲያ መሰራጨቱ በከባድ ሀዘን ውስጥ ባሉበት ወቅት ተጨማሪ የስነ-ልቦና ስቃይ እንደፈጠረባቸው አስታውቀዋል።
የወጣቱ ቤተሰቦች፣ የፖሊስ አካላት እና የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ትራምፕ በሰው ህይወት ማለፍ እና በቤተሰብ ሀዘን ላይ ያሳዩት ድርጊት ተገቢ አለመሆኑን በመግለጽ ድርጊቱን ኮንነዋል።
በርካታ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችም ቢሆኑ የተሰራጨው ምስል የስነ-ምግባር ደንብ የጎደለው እና ሰብአዊነትን ያላገናዘበ ነው ሲሉ በጽኑ ተችተውታል።
ዶናልድ ትራምፕ በእንግሊዝ በነብር ከተገደለው ወጣት ቪዲዮ በኋላ በኤአይ የተሰራ ምስል በማጋራታቸው ትችት አስተናገዱ
Source(መናኸሪያ ሬዲዮ)

