ዶክተር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ የፍርድ ቤት ዕግድ በመጣስ ሌላ ክስ ቀረበባቸው

በኦሎምፒክ ኮሚቴ ላይ የተጣለው ዕግድ እንዲፀናም ተወስኗል
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደ ጊዮጊስ፣ የኦሊምፐክ ኮሚቴ የባንክ ሒሳቦች እንዳይንቀሳቀሱ በፍርድ ቤት የተጣለውን ዕግድ በመጣስ ሌላ ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ፍትሐ ብሔር ምድብ ችሎት፤ እነ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ያቀረቡትን የክስ አቤቱታ፣ ችሎቱ ትናንት ማክሰኞ መስከረም 21 ቀን 2017 ተመልክቶ ትዕዛዝ ሰጥቶበታል፡፡
በእነ ኃይለ ገብረ ሥላሴ የቀረበው ክስም ‹‹ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ መስከረም 8 ቀን 2017 በኦሎምፒክ ኮሚቴ የባንክ ሒሳብ እንዳይንቀሳቀስ ዕግድ መሰጠቱ እየታወቀ፣ ሁለተኛ መልስ ሰጪ ዶክተር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ እግድ በተሰጠ በማግሥቱ መስከረም 9 ቀን በአዲስ አበባ ማሪዮት ሆቴል ለሚዲያ አካላትና “እሸልማቸዋለሁ” ላሏቸው አካላት ጥሪ አድርገው፣ ከታገደው ገንዘብ ላይ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ በአደባባይ ሲሸልሙ ውለዋል›› የሚል ነበር።
ከዚህም ባለፈ ዶክተር አሸብር ባዘጋጁት የሽልማት ፕሮግራም ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹ምንም እንኳን ሽልማት እንዳንሰጥ በእነ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ የታገድን ቢሆንም እኛ ግን ሽልማቱን እንሰጣለን፤›› በማለት፣ የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ባሉበት መናገራቸውን የቀረበው ክስ ያስረዳል።
‹‹በመሆኑም ሆነ ብለው በአደባባይ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ባለማክበር የፈጸሙትን የዕግድ ጥሰት ፍርድ ቤቱ አጣርቶ በወንጀል ሕግ አንቀጽ 443 መሠረት ዕርምጃ እንዲወስድ በአክብሮት እናመለክታለን፤›› ሲሉ ከሳሾች እነ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ (አራት ሰዎች) ጠይቀዋል።
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ፍትሐ ብሔር ምድብ ችሎት በእነ አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ የቀረበውን የዕግድ ጥሰት አቤቱታና እነ አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ (ዶ/ር) በጽሑፍ የሰጡትን ምላሽ ተመልክቶ፣ መስከረም 21 ቀን 2017 ዓ.ም. ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ችሎቱ በሰጠው ትዕዛዝም፣ ዕግዱ መጣስ አለመጣሱን አስመልክቶ የቀረበው ክርክር መደበኛው የችሎት ጊዜ ሲጀምር በመደበኛው ችሎት የሚታይ ይሆናል በማለት ትዕዛዝ የሰጠ ሲሆን፣ የመደበኛ ክርክሩን ቅሬታ ለመስማት ለጥቅምት 1 ቀን 2017 ዓ.ም. ቀጠሮ መስጠቱን ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል።
ከዚሁ አቤቱታ ጋር ተያይዞ ለችሎቱ የቀረበው ሌላው ጉዳይ፣ የኦሎምፒክ ኮሚቴ የባንክ ሒሳብና የኦሎምፒክ ኮሚቴው ያካሄደው ምርጫ ታግዶ መቆየት አለበት ወይስ የለበትም የሚል ነው።
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ፍትሐ ብሔር ምድብ ችሎት የሁለቱን አካላት ክርክር ከተመለከተ በኋላ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቀደም ሲል የሰጠውን ዕግድ ያነሳበት አግባብ ስህተት በመሆኑ ሊታረም ይገባል አይገባም የሚለው ክርክር በመደበኛው የችሎት ጊዜ ታይቶ ዕልባት እንደሚያገኝ ገልጿል፡፡
ይህ የይግባኝ ክርክር ዕልባት እስኪያገኝ ድረስም የተሰጠው ዕግድ ትዕዛዝ ጸንቶ እንዲቆይ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe