ገነነ መኩሪያ (ሊብሮ) ከቁም ነገር መጽሄት ጋር የዛሬ 11 አመት

ገነነ መኩሪያ በኢትዮጵያ እግር ኳስ አፍቃሪያን ዘንድ የሚታወቅ ስም ነው፤ገነነ በስፖርት ጋዜጠኝነት የረዥም ዓመታት ልምድ አለው ፤ ገነነ ላለፉት በርካታ ዓመታት የኢትዮጵያ እግር ኳስ መሠረታዊ ችግር የሥልጠና ችግር ነው በሚል በየመድረኩ እየተሟገተ ይገኛል፤የአገራችን ተጫዋቾች ተፈጥሯዊ እና አካላዊ ብቃት መሠረት ያደረገ ስልጠና ያስፈልጋል ሲል ሐሳቡን በመጽሐፍ መልክ አዘጋጅቶ አሳትመዋል፤ 29 ኛው የአፍሪካ ዋንጫ (የዛሬ 11 ዓመት ) የተሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን አቋምና ተሳትፎ ዙሪያ የራሱን ግምገማ አድርጎ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የአገራችን እግር ኳስ የስልጠና ሂደት እንዲፈትሽ ጥሪ አቅርበዋል፤
<ፌዴሬሽኑ የስልጠና መንገዱን መቀየር አለበት>
ቁም ነገር፡ በ29 ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የተሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ወደ ውድድሩ ያለፈው በውጤቱ ነው? ወይስ በዕድል ነው ብለህ ነው የምታምነው?
ገነነ፤ ብሔራዊ ቡድኑ ያለፈበትን መንገድ ለመናገር ከዚህ በፊት በማጣርያው ላይ የነበረውን ሂደት መመልከት ያስፈልጋል፤ ከዚህ በፊት ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሚደለደለው የነበረው ከሰሜንና ከምዕራብ አፍሪካ አገራት ጋር ማለትም ከግብጽ፤ ናይጄሪያ ቱኒዚያና ሞሮኮ ጋር ነበር የሚደለደለው፤ ለምሳሌ ባለፈው የ 28 ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ላይ ከእኛ ጋር ተደልድለው የነበሩት ናይጄሪያ እና ጊኒ ነበሩ፤እነዚህ ቡድኖች የመረጡት የጨዋታ ስልት እና የወሰዱትና የተሻለ ስለነበር ስለሆነ አሸንፈውናል.፤ከዚያ በፊት የነበረው ሁኔታም ተመሳሳይ ነው. የዘንድሮውን /2005 ዓመተ ምህረት ማለቱ ነው/ ቡድን የተመደበው ግን ከሱዳንና ከቤኒን ጋር ነበር፤ እነሱ ደግሞ ከእኛ ጋር ተመሳሳይ የሰውነት አቋም እና አጨዋወት ያላቸው ፤ ስለዚህ ወርቃማ ዕድል ነበር ያጋጠመው ለማለት እችላለሁ፤
ቁም ነገር፤ የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ግን ጥሩ አልነበረም?

Genene mekuria
ገነነ፤ ብሔራዊ ቡድኑ በአፍሪካ ዋንጫ ላይ ያጋጠሙት ከዚህ በፊት በማጣሪያው አግኝተው ያስወጡት ቡድኖች ናቸው፤ ለምሳሌ ከቡርኪና ፋሶ ጋር በማጣሪያው ተገናኝተን 3 ለ 0 አሸንፈውናል፤ ከናይጄርያ ጋር ደግሞ ለረጅም ጊዜ አብረን እየተመደብን ከማጣሪያው የሚያስወጡን ነው፤ ለምሳሌ የናይጄሪያን ብቻ ያለፈውን የ 45 ዓመት ታሪክ ሪከርድ ብናይ ለ 22 ጊዜ ከናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን ተጫውተናል፤ እኛ ያሸነፍናቸው ለ2 ጊዜ ብቻ ነው፤ ለሶስት ጊዜያት አቻ ተለያይተናል፤ ለአስራ ሰባት ጊዜ አሸንፈውናል፤ እኛ ናይጄሪያ ላይ ያገባነው 11 ጎል ብቻ ሲሆን እነርሱ ያገቡብን 63 ጎል ነው፤ ናይጄሪያ አሁን የእኛ ቡድን ከሚሰለጥንበት የስልጠና መንገድ የተሻሉ መሆናቸውን ያሳያል፤ እኛ ሁልጊዜ እነሱ ጠንካራ በሆኑበት መንገድ ስለምንሰለጥን ሁሌም እነርሱ ይበልጡናል፤. ይህ ናይጄሪያ ብልጫ በታዳጊ ቡድን በሴቶች በወንዶች ብሔራዊ ቡድኑ እና በኦሎምፒክ ቡድን ጭምር ነው፤ ይሄ ለምን ሆነ ለምን መሰለህ? የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን በረጅም ርቀት በዓለም ላይ ይታወቃል አይደል? ናይጄሪያ የረጅም ርቀት ሩዋጭ ታውቃለህ?
ቁም ነገር፤ አላውቅም፤
ገነነ ፤ የካሜሮን ወይም የጋና አትሌትስ?
ቁም ነገር፤አላውቅም፤
ገነነ፤ አመሰግናለሁ፤ በዚህ ርቀት ስለማይሠሩ ይመስልሃል ውጤት ያላመጡት? ይሰራሉ፤ ግን እኛ ጋር ሲነፃፀሩ በተፈጥሯቸው የእኛ አይነት ስላልሆኑ ውጤት ሲያመጡ አይታይም፤ እነርሱ በአጭር ርቀት ላይ ጥሩ ናቸው፤ እኛ ደግሞ በአጭር ርቀት ሩጫ ላይ ጥሩ አይደለንም፤ ለምን መሰለህ? ተፈጥሮ ስለሆነ ነው፤ እግር ኳስ ደግሞ ፍጥነትና ጉልበት የሚፈልግ ነው፤ መሰረት የሚያደርገው ፍጥነትና ጉልበት ነው፤ ቶሎ ቶሎ ማጥቃት አለ ፤ ቶሎ ቶሎ መሮጥ፤ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ሁልጊዜ በቀላሉ የሚያሸንፉን እነርሱ የተሻለ ፍጥነትና ጉልበት ስላላቸው ነው፤ እኛ ደግሞ በተነፃፃሪነት ከነሱ ያነሰ ፍጥነትና ጉልበት ስላለን እንሸነፋለን፤ ስለዚህ ለሁሉም አሰልጣኞች የምነግራቸው ተደጋጋሚ ነገር ከዚህ አይነት ስልጠና ወጡ ብዬ ነው፤ ነገር ግን ማንም የሚሰማ የለም፤ ለእግር ኳስ በጣም አስፈላጊ ተብሎ በሚታመንበት ፍጥነት ላይ ብልጫን ሲወሰድብህ ችግሩ ምንድነው ብሎ በመጠየቅ ያንተ ፋንታ ነው፤ አለበለዚያ ዶሮ ማባረር ነው የሚሆነው፤
ቁም ነገር፤ ማለት?
ገነነ፤ ቤት ውስጥ ዶሮ አባረህ ለመያዝ ሞክረህ ታውቃለህ?
ቁም ነገር፤ አዎ፤
ገነነ፤ ስታባርር ምንድነው የምታደርገው? ዶሮዋን ወደ አንድ ኮርነር ላይ ለመውሰድ አይደለም የምትሞክረው? ያን ጊዜ መውጫ ታጣለች ማለት ነው፤ ሜዳ ለሜዳ ስታራሩጣት ብትውል ግን ውጤቱ እንደ ሀገራችን እግር ኳስ ነው የሚሆነው፤ ስለዚህ የቴክኒክ እውቀትህን መጠቀም አለብህ ማለት ነው፤
ቁም ነገር፤ በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለው የዓለም እግር ኳስ ፍጥነትና ጉልበት ላይ ያተኮረ ነው፤በዚህም የብዙዎቹ አገሮች ውጤታማ ሆነዋል፤ አሁን አንተ በምትለው መንገድ ከፍጥነትና ጉልበት ወጥቶ ውጤት ያመጣ ሀገር አለ?
ገነነ፤ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ቡና ክለብ በዚህ መንገድ በ1995 ውጤት አሳይቷል፤ ካሳዬ አራጌ አሰልጣኝ የነበረ ጊዜ ማለት ነው፤ ያን ጊዜ በአንድ ዓመት ብቻ ነው የሰራው፤ ግን ተስፋ ያለው ቡድን እንደነበር ሜዳ ላይ አሳይቷል፤
ቁም ነገር፤ ግን አሁን እየተተገበረ ያለው የስልጠና መንገድ ሙሉ ለሙሉ ትክክል አይደለም ብለህ ነው የምታምነው?
ገነነ፤ እኔ ሳልሆን ውጤቱ ነው የሚናግረው፤
ቁም ነገር፤ የኛ ሀገር አሰለጣጠን አብዛኛውን አለም የሚጠቀምበት ስልጠና ነው፤አሰልጣኞቻቸንም የተማሩት በምስራቅ አውሮፖ ሃገራት ነው፤ችግሩ የአሰልጣኖቹ ከሆነ እነዚያ የአውሮፓ ሀገራት ለምን ውጤታማ ሆኑ?
ገነነ፤ ትክክል ነህ፤ አብዛኛዎቹ የሃገራችን አሰልጣኖች የተማሩት በምስራቅ አውሮፓ ሀገራት በተለይም በጀርመን ነው፤ ለምሳሌ እኔ በግሌ የጀርመን እግር ካስ ፌዴሬሽንን አነጋግሬያለሁ፤ ደብዳቤ ጽፌላቸው ምላሽ ሰጥተውኛል፤ደብዳቤውን ላሳይህ እችላለሁ፤እኔ የጠየካቸው ጥያቄ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን አጠቃላይ ውጤት መሰረት አድርጌ ይህ ውጤት እናንተን ተጠያቂ ያደርጋችሃል፤ ምክንያቱም አሰልጣኞቻችንን ያሰለጠናችሁት እናንተ ናችሁ፤ ትችላላችሁ ብላችሁ ያሰለጠናችሃቸው እናንተ ስለሆናችሁ ባለፉት 40 አመታት ለመጣው ውጤት ተጠያቂ ናችሁ የሚል ነው፤
ቁም ነገር፤ ምን አሉህ?
ገነነ፤ የእነርሱ መልስ የሰጠናቸው ስልጠና መሰረታዊ ነው፤ከዚህ መሰረታዊ የእግር ካስ ስልጠና ተነስተው ወደሚያዋጣቸው መንገድ መሄድ ይችላሉ ነው ያሉት፤ ያ ማለት ምን ማለት ነው? ጀርመኖች ራሳቸው ባስተማሩት መንገድ አይጠቀሙም፤ ሽረውታል ማለት ነው፡፡
ቁም ነገር፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ታዲያ ከአሰልጣኞቻችን ጋር ለመነጋገር አልሞከርክም?
ገነነ፤ ደብዳቤውን ይዤ ከአሰልጣኞቻቸን ጋር በተደጋጋሚ ተነጋግሪያለሁ፤ጀርመኖች እንደዚህ ብለዋል፤ስለዚህ ከዚህ የተለመደ የአሰለጣጠን መንገድ መውጣትና ሌላ መንገድ መከተል አለባችሁ አልኩ፤ ግን የሰማኝ የለም፤ውጤቱን ደግሞ አሁን ድረስ እያየነው ነው፤
ቁም ነገር፤ መሰረታዊ የእግር ካስ አሰለጣጠን ሳይንሳዊ ዘዴ አይጠቅምም አያስፈልገንም ብለህ ታምናልህ?
ገነነ፤ አላልኩም፤ በነገራችን ላይ ሳይንስ ማለት ምን ማለት ነው? ዝርዝር ውስጥ ሳይገባ ማረጋገጫ ያለው ነገር ማለት ነው ሳይንስ ማለት፡፡ ስለዚህ በዚህ መንገድ ውጤቱን ምን እንደሚያሳይ ሁላችንም እናውቃለን፤ እኔ እያልኩ ያለሁት ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ እየተከተልነው ያለነው የስልጠና ዘዴ ውጤት እንደማያስገኝ የቀረበ ማረጋገጫ የለም፡፡ ስለዚህ መንገዳችሁን ቀይሩ፤ የእኛ ተጫዋቾች ያላቸውን ተፈጥሯዊ ሁኔታ መሠረት ባደረገ ሥልጠና ቀይሩ ነው. እያልኩ ያለሁት፡፡
ቁም ነገር፤ ግን ይህንን ዘዴ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ መጀመር ያለበት ወይስ ከስር ጀምሮ መኮትኮት ነው ያለባቸው?
ገነነ፡ በዋናው ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች ላይ መጀመር ይቻላል. ብዬ ነው የማምነው፤ ምክንያቱም ሌላ አዲስ ነገር አታመጣም፤ ልጁ ያለውን ችሎታ እንዲጠቀም ብቻ ነው ዕድል የምትሰጠው፤ ልጁ በሚችለው ነገር እንዲጫወት ማድረግ ነው፤ የአንድ ቡድን የአጨዋወት ስልት የሚመሰረተው ባሉት ተጫዋቾች ችሎታ ላይ ነው፤ ስለዚህ የእኛም ሀገር ስልጠና የእኛም ሀገር ተጫዋቾች መሠረት ባደረገ መልኩ መሰጠት አለበት፤ እንደዚህ ከተደረገ በእርግጠኝነት ለመናገር የኢትዮጵያ እግርኳስ በዓለም ላይ ትልቅ ደረጃ ይደርሳል፡፡ት
ቁም ነገር፤ በአንድ ወቅት ብሔራዊ ቡድኑ ይሰጠኝና ማሰልጠን እችላለው ብለህ ጠይቅ ነበር ልበል?
ገነነ፤ ሃሳቡን ሜዳ ላይ ለማሳየት ጠይቄያለሁ፤
ቁም ነገር፤ የአሰልጣኝነት ትምህርት ተምረሃል?
ገነነ፤ ኮርስ ወስጃለሁ፤ ብሔራዊ ደረጃ የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ ለመሆን የምትፈልጉ ተወዳደሩ ሲባል ተወዳድሪያለሁ፤ እኔ በግሌ የጠየቀሁት ነገር ምንድን ነው? ብሔራዊ ቡድኑ የሚሰጠው አሰልጣኝ የራሱን ተጨዋቾች መርጦ ከተቀሩት ካልተመረጡ ተጫዋቾች መካከል የራሴን ቡድን አደራጃለሁ፤ ለዚህ የስልጠና የሚሆኑ ተጫዋቾች ከያዝኩ በሃላ ለስልጠና ክፍያ አልጠይቅም፤ ተጫዋቾች አበል አይጠይቁም፤ ትጥቅ አይጠይቁም፤ የምፈልገው አንድ ነገር ብቻ ነው፤ የልምምድ ሜዳ ብቻ እንዲፈቅዱልኝ ብቻ ነብር የምፈልገው፤ ከዚያ በሃላ ህዝብ በተሰበሰበበት በአዲስ አበባ ስታዲየም ከዋናው ብሄራዊ ቡድን ጋረ እንድንጫወትና እንድንታይ ነብር የጠይቅሁት፤ከዛ በሃል እኔ እያልኩ ያለሁት የአሰለጣጠን መንገድና የእስከ ዛሬው የስልጠና መንገድን ህዝብ አይቶ እንዲፈርድ ነብር የጠይቅሁት፤
ቁም ነገር፤ ምላሹስ?
ገነነ፤ እስከዛሬ መልስ የሰጠኝ የለም፤
ቁም ነገር፤ ግን ይህንን ሃሳብህን ወደ ተግባር ለመቀየር የፌዴሬሽኑ ፈቃድ የግድ አስፈላጊ ነው?
ገነነ፤ የበጀት ጉዳይ አንስተው አይቻልም እንዳይሉ ነው በዚህ መልኩ የጠየቅሁት፤
ቁም ነገር፤ በቃል ነው ወይስ በደብዳቤ ነው የጠየቅክው?
ገነነ፤ መጀመሪያ በቃል የፌዴሬሽኑን የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ አነጋግሬያለሁ፤ በደብዳቤ ጠይቅ ባለኝ መሰረት በደብዳቤ አስገብቻለሁ፤ መልስ ግን የለም፤
ቁም ነገር፤ አመሰግናለሁ፡፡
(ቁም ነገር መጽሄት ቅጽ 12 ቁጥር 146 የካቲት 2005)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe