ግብጽ እጅግ አነጋጋሪ እና የምድራችን ግዙፍ የደህንነት መስሪያ ቤት ገንብታ ማጠናቀቋ ተሰማ፡፡ ካይሮ ኦክታጎን ስትል የሰየመችው ይህ የደህንነት ዋና መስሪያ ቤት ከአሜሪካው ፔንታጎን በ39 እጥፍ እንደሚበልጥም ታውቋል፡፡
ግብጽ በግዙፉ ኦክታጎን ፕሮጀክት ለተቀረው ዓለም ማስተላለፍ የፈለገችው ምንድን ነው የሚሉ ጥያቄዎችም በርትተው ሰንብተዋል፡፡
የፕሬዝዳንት አልሲሲ አስተዳደር ግብጻዊያን በከፋ የኑሮ ውድነት እየተፈተኑ ባለበት በዚህ ስዓት፤አንዳች ህዝባዊ አመጽ እንኳን ቢፈነዳ የሚሸሸጉበትን ምሽግ ገንብተዋል ተብሏል፡፡
ይህ ግብጽ ገንብታ አጠናቃዋለች የተባለው የጦር መስሪያ ቤት እጅግ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ ይህ የብዙዎችን ቀልብ የሳበውንና በሀገር ውስጥ ደግሞ ከፍተኛ ትችት ያስተናገደውን ፕሮጀክት ከሁለት ሳምንት በፊት በደማቅ ስነ-ስርዓት ማስመረቃቸው ይታወቃል፡፡
በዚሁ የምረቃ-ስነ ስርዓት ላይም ፕሬዝዳንት አልሲሲ ከአስር ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በሙሉ ወታደራዊ ዩኒፎርም ታይተዋል፡፡
ይህ የግብጽ አዲስ ፕሮጀክት ከዙሪክ ወይም ከኮፐንሀገን ከተማ ጋር በስፋቱ የሚስተካከል እንደሆነ ተነግሯል፡፡ ስፋቱ 34 ስኩዌር ማይልስ መሆኑ ታውቋል፡፡
ግብጽ ይህንን ፕሮጀክት እውን ለማድረግ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ወጪ ያደረገችበት ነው፡፡
የፕሬዝዳንት አልሲሲ አስተዳደር ግብጻዊያን ከፍተኛ በሆነ የኑሮ ውድነት እየተፈተኑ ባሉበት በዚህ ስዓት እንዲህ አይነቱን ወጪ ለማውጣት የወሰነው ወደፊት ከሚነሳ የህዝብ አመጽ መሸሸጊያ ይሆን ዘንድ በማሰብ እንደሆነ ተንታኞች መላ ምታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ከዚህ ባለፈ የግብጽ ጦር በሀገሪቱ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ውስጥ ሚና ያለው ሲሆን፤አሁንም በዚህ ግንባታ ላይ ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ የተጀመረ ስለመሆኑ ይታመናል፡፡
የግብጽ ጦር በሀገሪቱ ውስጥ የሆቴል ስራዎች፡የዶሮ እርባታዎች እና የጋዝ ማደያዎችን በባለቤትነት እንደሚያስተዳድር ይነገራል፡፡ የግብጽ ጦር በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ እንቅስቃሴ እንዳለውም ይነሳል፡፡
ፕሬዝዳንት አልሲሲ ሀገራቸው ኦክታጎንን ገንብታ ያጠናቀቀችው የሀገሪቱን የጸጥታ ሁኔታ በጥብቅ ለመቆጣጠርና የሚያጋጥሙ ቀውሶችን ለመቆጣጠር በሚል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡//

