ግድቦች በቂ ውሐ ባለመያዛቸው ምክንያት ኢትዮጵያ ለጎረቤት አገር ከምትሸጠው መብራት በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ልታጣ ነው ተባለ

በተፈጠረው እጥረት አገሪቱ ለሱዳን የምታቀርበውን የኤሌክትሪክ ኃይል ሙሉ በሙሉ ለማቋረጥ ወስናለች። DW

ኢትዮጵያ እስከ መጪው ሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ ኤሌክትሪክ በፈረቃ ማከፋፈል ልትጀምር ነው። የኃይል ማመንጫ ግድቦች በቂ ውሐ ባለመያዛቸው ምክንያት በተፈጠረው እጥረት አገሪቱ ለሱዳን የምታቀርበውን የኤሌክትሪክ ኃይል ሙሉ በሙሉ ለማቋረጥ ወስናለች። ከኢትዮጵያ ለጅቡቲ የሚቀርበው ኤሌክትሪክ ኃይል በግማሽ ገደማ ይቀነሳል።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬት ኮምዩንኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት የአገሪቱ ግድቦች በቂ የውሀ መጠን ባለመያዛቸው ምክንያት አገሪቱ በአሁኑ ወቅት የምታመነጨው የኃይል መጠን 60 በመቶ ገደማ ብቻ ነው።

የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት በየአመቱ በ13 በመቶ እንደሚያድግ የገለጹት አቶ ሞገስ መኮንን ካለፈው አመት ጀምሮ የኢትዮጵያ ግድቦች በቂ ውሐ አለማያዛቸው ኃይል በፈረቃ ለማቅረብ ገፊ ምክንያት መሆኑን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

አቶ ሞገስ “አሁን ባለው ሁኔታ በአብዛኛዎቹ ግድቦቻችን በተለይ ደግሞ በደቡብ እና በምሥራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች ያሉት እንደ ቆቃ፤ መልካ ዋከና ጊቤ ሶስተኛ ያሉት ግድቦች [የያዙት የውሐ መጠን] የሚፈለገው ከፍታ ላይ አልደረሰም” ሲሉ ተናግረዋል።

ከፍተኛ የውሐ እጥረት ከገጠማቸው ግድቦች መካከል በኦሞ ወንዝ ላይ የተገነባው የጊቤ ሶስት የኃይል ማመንጫ ይገኝበታል። ጊቤ ሶስት “አዲስ የኃይል ማመንጫ እንደመሆኑ መጠን ኃይል ያመንጭ እንጂ ሥራ እየሰራ ያለው ግድቡ የሚፈለገው ከፍታ ላይ ሳይደርስ ነው። በዚህ የተነሳ የውሐ መጠኑ እየወረደ ነው” የሚሉት አቶ ሞገስ የግድቡ የውሐ መጠን በግንቦት 5 ቀን 2011 ዓ.ም. በተደረገ ልኬት 818 ሜትር ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል። አቶ ሞገስ እንደሚሉት ግድቡ በ2010 ዓ.ም. ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው የውሐ መጠን በ16 ሜትር ገደማ ቀንሷል።

የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ስለሺ በቀለ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ግድቦቹ በገጠማቸው የውሐ እጥረት ሳቢያ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ያመነጫሉ ተብሎ ከታሰበው በአሁኑ ወቅት ከ400 ሜጋ ዋት በላይ ቀንሷል። በዚህም ምክንያት ለኢትዮጵያ የሚቀርበው የኤሌክትሪክ ኃይል ቢያንስ እስከ መጪው ሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ በፈረቃ ይሆናል።

አቶ ሞገስ “እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች የፈረቃ ሥርዓቱ የሚጀምረው በሶስት ቡድን ተከፍሎ ነው። አንደኛው ቡድን ጠዋት ወደ 11 ሰዓት አካባቢ ይጀምር እና እስከ ቀን 5 ሰዓት የሚዘልቅ፤ ሁለተኛው ቡድን ከ5 ሰዓት ይጀምርና እስከ 10 ሰዓት የሚዘልቅ፤ ሶስተኛው ከ10 ሰዓት ይጀምር እና እስከ ምሽቱ አራት ሰዓት ድረስ የሚዘልቅ ይሆናል” ብለዋል።

በውሳኔው የመድሐኒት ፋብሪካዎች፣ የሕክምና ተቋማት እና ተማሪዎቻቸውን ለመፈተን የተዘጋጁ ተቋማት ላይ የፈረቃ አገልግሎቱ ተፅዕኖ እንዳያሳድር ጥረት ተደርጓል። ለከተሞች የሚቀርበው የኤሌክትሪክ ኃይል በሶስት ፈረቃ ይሆናል።

የፈረቃ ሥርዓቱ ከፍተኛ ኃይል በሚፈልጉ የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች ላይ ከፍ ያለ ጫና ያሳድራል። “ስሚንቶ ፋብሪካዎች ከአጠቃላይ የማምረቻ ጊዜያቸው 50 በመቶውን ያህል እንዲቀንሱ፤ የብረታ ብረት እና ሌሎች ኢንዱስትሪዎች ደግሞ በፈረቃ እንዲሰሩ እና በ24 ሰዓት አንድ ጊዜ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚደረግበት የፈረቃ ሥርዓት ተዘርግቷል” ሲሉ አቶ ሞገስ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት አመታት የአገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ቀለል በሚልባቸው ሰዓታት ለሱዳን እና ለጅቡቲ ኃይል ስታቀርብ ቆይታለች። አሁን በአገሪቱ በተፈጠረው የውሀ እጥረት ምክንያት የኢትዮጵያ መንግሥት ለጅቡቲ ከሚቀርበው ኃይል ግማሽ ያክሉን ለመቀነስ መወሰኑን አቶ ሞገስ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ የኃይል እጥረት እስኪፈታ ለሚቀጥለው አንድ ወር ገደማ ለሱዳን የሚቀርበው ኃይል ሙሉ በሙሉ ይቋረጣል። አቶ ሞገስ “የኃይል እጥረቱ እስከሚፈታ ድረስ ወደ ሱዳን አይላክም። የኃይል እጥረቱ እስከሚስተካከል እና እስከሚቀረፍ ድረስ አስፈላጊ የሆኑ የጥገና ሥራዎች እየተሰሩ እንቆያለን። የጥገና ሥራው እየተሰራ ከቆየ በኋላ የኃይል ፍላጎታችንን ማሟላት የምንችልበት ደርሶ ከዚያ የሚተርፍ ነገር የሚኖር ከሆነ በዚህ መሀል የሚታሰብ ነው። ወደ ጅቡቲ ይላክ የነበረው ላይ ቅነሳ ይደረጋል” ብለዋል።

አቶ ሞገስ እንዳሉት ኢትዮጵያ ባለፈው አመት ለጅቡቲ እና ለሱዳን ካቀረበችው የኤሌክትሪክ ኃይል 82 ሚሊዮን ዶላር አግኝታ ነበር።

ምንጭ፡ DW

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe