ግጭት በማስነሳት 69 ግለሰቦችና 8 የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ዋሉ

(አብመድ) በቤኔሻንጉል ጉሙዝ እና በአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረውን ችግር ለመፍታት ሲሰራ የነበረው የመጀመሪያው ምዕራፍ የማረጋጋት ስራ መጠናቀቁን የኢፌዴሪ ሰላም ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

በቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን እና በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር አዋሳኝ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው ግጭት በሰው ሕይዎት እና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ይታወቃል፡፡ ግጭቱን ለማረጋጋትም የፌዴራል መንግስት ከሁለቱ ክልሎች ጋር በመሆን ሲሰራ ቆይቷል፡፡

የሠላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ስዩም መስፍን ለአብመድ እንደተናገሩት በሁለቱም ወገኖች መካካል የነበረውን የቆየ የመከባበር፣ የመደጋገፍ እና የመተሳሰብ ሂደት ለማጠናከር ከቀበሌ ጀምሮ ሕዝባዊ ውይይቶች ሲካሄዱ ነበር፡፡ ግጭት እና ወንጀሎች እንዲባባሱ እጃቸው አለበት የተባሉ ተጠርጣሪዎችን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ ሲሰራ መቆየቱንም ዶክተር ስዩም ጠቅሰዋል፡፡

በመጀመሪያው ምዕራፍ ስምንት የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች እና 69 ሌሎች ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ነው ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡ ቀሪ ተጠርጣሪዎችን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነም ታውቋል፡፡ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ሥራ እየተሰራ መሆኑን እና የተፈናቀሉ ዜጎችን በፍጥነት ወደ ቀድሞ ቀያቸው መመለስ እንደተጀመረም ዶክተር ስዩም ነግረውናል፡፡

በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ሁከት እና ብጥብጥ እንዲነግስ በማድረግ ስራ ላይ የተጠመዱ ተጠርጣሪዎችን ተጠያቂ ለማድረግ ጥረት ሲደረግ ተሳታፊ ናቸው የሚባሉ አካላትን ክልሎች ወይም ዞኖች አሳልፎ ለመስጠት ፈቃደኛ ያለመሆን ሁኔታ እያጋጠመ መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል፤ ይህ ደግሞ ለሁከትና ብጥብጥ ምክንያት የሆኑ ግለሰቦችን ተጠያቂ ለማድረግ እንቅፋት እየፈጠረ መሆኑን ነው የጠቆሙት፡፡

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe