የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የገነተልዑል ህንጻን ሊያድስ ነው ተባለ፡፡ ለእድሳቱም አራት ሚሊዮን ዩሮ በጀት ተይዟል መባሉም ታውቋል፡፡
በስድስት ኪሎ ጊቢ ውስጥ የሚገኘው የገነተልዑል ህንጻ የኢትዮጽያ ጥናት ተቋም ቤተመጽሀፋትን፡የዩኒቨርሲቲው ሴኔት መሰብሰቢያ አዳራሽን፡ የአስተዳደር ቢሮዎችን እና የኤትኖግራፊክ ሙዚየምን በመያዝ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡
ህንጻው ታሪካወዊነቱን በጠበቀ መልኩ ይታደሳል የተባለ ሲሆን ከዚህ በፊት መጠነኛ እድሳቶች ሲደረጉለት መቆየቱን የዲጂታላይዜሽንና የመሠረተ ልማት ምክትል ፕሬዜዳንት ወንደሰን ሙሉጌታ ተናግረዋል፡፡
የእድሳት ንድፉን የሰራው አማካሪ ድርጅት መቼ ምን አይነት ግብዓት መጠቀም እንዳለበት የሚገልጽ ዝርዝር ጥናት ማቅረቡንም ገልጸዋል፡፡
በእድሳት ጥናቱ የኢትዮጽያ ቅርስ ጥበቃ ባለሙያዎች እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአርክቴክቸር ሙህራን ተሳትፈዋል ተብሏል፡፡ በጣሊያን መንግስት የገንዘብ ድጋፍ እድሳቱ እንደሚከናወንም ታውቋል፡፡//

