ፈረንሳይ በ1994ቱ ጭፍጨፋ የነበራትን ሚና ለመለየት የተካሄደውን ምርመራ በጸጋ እንደምትቀበል ሩዋንዳ አስታወቀች

የሃብያ ሪማና መንግስት ደጋፊ የነበረችው ፈረንሳይ ከጭፍጨፋው ጋር በተያያዘ በተለያዩ ምክንያቶች ትወቀሳለች፡፡

ከጭፍጨፋው ጋር በተያያዘ ላለፉት 5 ዓመታት በራሷ ስታካሂደው የነበረውን ምርመራ ውጤት በቅርቡ ይፋ እንደምታደርግም ሩዋንዳ አስታውቃለች፡፡

በአንድ መቶ ቀናት ውስጥ 800 ሺ ገደማ ቱትሲዎች በተጨፈጨፉበት የ1994ቱ ጭፍጨፋ ፈረንሳይ ምን ሚና እንደነበራት ለመለየት የተካሄደውን ምርመራ እንደምትቀበል ሩዋንዳ አስታወቀች፡፡

ምርመራው 15 ፈረንሳውያን አባላት ባሉት እና በፕሬዝዳንት ማክሮን በተቋቋመው የምርመራ ኮሚሽን የተካሄደ ነው፡፡

ኮሚሽኑ በታሪክ ተመራማሪው ቪንሶ ዱክለርት ነበር የሚመራው፡፡

ቪንሶ ዱክለርትም ኮሚሽኑ በምርመራው ያጠናቀረውን ባለ 1 ሺ 200 ገጽ ሪፖርት ትናንት ለፕሬዝዳንት ማክሮን አቅርበዋል፡፡

በፍራንሷ ሚተራንድ ትመራ የነበረችው ፈረንሳይ የዩቬናል ሃብያ ሪማና መንግስት ደጋፊ ነበረች፡፡

በዚህም ለጭፍጨፋው ሲደረጉ የነበሩ ዝግጅቶችን አይቶ እንዳላየ ከማለፍም በላይ አላስቆመችም በሚል በጭፍጨፋው ተባባሪነት ጭምር ትወቀስ ነበረ፡፡

የሃገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነትም በዚሁ ምክንያት ሻክሮ ቆይቷል፡፡

ባለፉት 2 ዓመታት በታሪክ ተመራማሪዎቹ ሲደረግ የነበረው ምርመራም ፈረንሳይ ሲደረጉ የነበሩ ዝግጅቶችንና ጭፍጨፋውን ችላ ማለቷን አመልክቷል፡፡

ሆኖም በጭፍጨፋው ተባባሪነት አልጠቀሳትም፡፡

ሪፖርቱ በፈረንሳውያን ባለሙያዎች ብቻ መካሄዱ ብዙዎችን አጠራጥሯል፡፡ በወጉ እና አካታች በሆነ መንገድ አልተካሄደም ሚዛናዊነትም ይጎድለዋል ከሚሉ ትችቶችም አላመለጠም፡፡

ሆኖም የፖል ካጋሜ መንግስት ሪፖርቱን መቀበሉን አስታውቋል፡፡

ከ5 ዓመታት በፊት ባቋቋመው ኮሚሽን በኩል ሲካሄዱ የነበሩ ምርመራዎች ውጤት ሪፖርት በመጪዎቹ ሳምንታት ይፋ እንደሚያደርግም ነው ያስታወቀው፡፡

ይህ የዱክለር ሪፖርትን የበለጠ የተሟላ ለማድረግ ያስችላልም ብሏል፡፡

የአፍሪካ ህብረትም የዱክለርን ሪፖርት ተቀብሎታል፡፡

ሪፖርቱ በወጉ እና በተጨባጭ ሁኔታዎች መደራጀቱን የገለጹት የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ተግባሩን አድንቀዋል፡፡

በዘመነኛ የአፍሪካ ታሪክ ድራማዊ ስለሆነው ስለዚህ ጉዳይ እውነታውን ለማወቅ ስለተደረገው ስለዚህ ጠቃሚ ውሳኔ ለማመስገን እፈልጋለሁ ሲሉም ነው ኮሚሽን ሊቀመንበሩ በማህበራዊ ገጾቻቸው ያሰፈሩት፡

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe