ዶክተር አዲስ ዓለም ባሌማ በተጠረጠሩበት ህገ መንግስቱን እና ህገ መንግስታዊ ስርአቱን በሃይል ለመናድ ሙከራ ወንጀል ምርመራ እየተከናወነባቸው ሲሆን÷ለተጨማሪ ምርመራ ከሁለት ጊዜ በላይ ፍርድቤት ቀርበው ጉዳያቸው ታይቷል።
መርማሪ ፖሊስ ከዚህ በፊት በተሰጠው ተጨማሪ 14 የምርመራ ቀናት ውስጥ በርካታ የምርመራ ስራ ማከናወኑን አብራርቷል።
ከእነዚህ መካከል ዶክተር አዲስአለም ባሌማ ጦርነት በማስነሳትና በመከላከያ ሰሜን እዝ ሰራዊት ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ከማድረግ ባለፈ በወቅቱ በትግራይ ክልል የነበረ የነዳጅ ዴፖ እንዲዘረፍ ተሳትፎ እንዳላቸው ማስረጃ መሰብሰቡን ጠቅሷል፡፡
ኢትዮጵያ ከተለያዩ የውጭ ሀገራት ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠልሽት እና ለማቋረጥ ሲሰሩ እንደነበርም ማስረጃ መሰብሰቡን የጠቀሰው መርመሪ ፖሊስ በትግራይ ክልል የተፈጸሙ ወንጀሎችን የሚያጣራ የምርመራ ቡድን መሄዱን ተከትሎ የቡድኑን የምርመራ ውጤት ለማምጣትና ቀሪ የምርመራ ስራዎችን ለማከናወን ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልገኛል ብሏል።
ተጠርጣሪው ዶክተር አዲስዓለም ከጠበቃቸው ጋር ቀርበው እስካሁን 90 ቀን መታሰራቸውን እና የተከናወነው ምርመራ በቂ መሆኑን በመጥቀስ ተጨማሪ ጊዜ ሊሰጥ አይገባም ሲሉ መቃወሚያ በማቅረብ የዋስትና ጥያቄ ጠይቀዋል።
መርማሪ ፖሊስም ዋስትናውን ተቃውሟል።
የሁለቱን ክርክር ያዳመጠው የፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት የጊዜ ቀጠሮ ችሎትም 12 ተጨማሪ ቀናትን ለምርመራ ለፖሊስ ፈቅዷል።