ፍቅረኛውን ሳኒታይዘር በማርከፍከፍ በእሳት ተቃጥላ እንድትሞት ያደረገው ተከሳሽ የሞት ፍርድ ተፈረደበት

ሰብለ ንጉሴን ሳኒታይዘር በማርከፍከፍ ተቃጥላ እንድትሞት ያደረገው ዳግማዊ አራጋው በሞት ተቀጣ

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ ዳግማዊ አራጋው በተባለው ግለሰብ ላይ በፈጸመው ከባድ የግድያ ወንጀል በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት ክስ መስርቶ የክርክር ሂደቱን ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡

የዐቃቤህግ የክስ መዝገብ እንደሚያመላክተው ተከሳሽ የወንጀል ህግ አንቀፅ 539/1/ሀ ላይ የተደነገገውን ድንጋጌ በመተላለፍ በቀን ታህሳስ 30/2014 ዓ.ም ከሌሊቱ በግምት ከ9፡00 እስከ 10፡00 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ በአዲስ አበባ ከተማ አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 04 ሳሬም ሆቴል ጀርባ ባለው መኖሪያ ቤት ውስጥ ነው የወንጀል ድርጊቱን የፈጸመው ሲል ዐቃ ህግ በክስ ዝርዝሩ ላይ አስቀምጧል፡፡

የወንጀል ድርጊት አፈጻጸሙን በተመለከተም ተከሳሽ በዕለቱ በፍቅር ግንኙነት አብራው የምትኖረውን ሟች ሰብለ ንጉሴን በመካከላቸው በተፈጠረ አለመግባባት በእጁ ይዞት በነበረው የቤት ቁልፍ ደጋግሞ ግንባሯ ላይ እንዲሁም ፊትዋንም ደጋግሞ በጥፊ መምታቱን በክሱ ላይ ተመላክቷል፡፡

በተጨማሪም በቢላ የግራ እግሯ የታችኛው ክፍል ወይም መርገጫዋን እና የቀኝ እጅ ትንሽዋ ጣቷ ላይ በመውጋት ጥልቀት የሌለው የቆዳ መቆረጥ እንዲደርስባት ካደረገ በኃላ ሳኒታይዘር ሰውነትዋ ላይ በማርከፍከፍ ክብሪት ለኩሶ ፊትዋ፣ አንገትዋ፣ የደረት ሶስተኛ ክፍሏ፣ ሆዷ፣ እጆቿ እና እግሮቿ በእሳት እንዲቃጠል ማድረጉንም የወንጀል አፈጻጸም ድርጊቱ ያስረዳል፡፡

በደረሰባት አደጋ ምክኒያትም የተቃጠለው ሰውነትዋ ኢንፌክሽን ፈጥሮ ኢንፌክሽኑ ወደ ሳምባዋ እና አእምሮዋ ተዛምቶ የደም ዝውውሯና የእስትንፋስ ስርዓቷ ተቋርጦ ህይወትዋ ሊያልፍ ችሏል፡፡

ተከሳሽ ክሱ ተነቦለት የወንጀል ድርጊቱን አልፈጸምኩም በማለት ክዶ የተከራከረ በመሆኑ ዐቃቤ ህግ የወንጀሉን መፈጸም ያስረዱልኛል ያላቸውን ሰው ምስክሮች አቅርቦ ለፍርድ ቤቱ ያሰማ ሲሆን በተመሳሳይም የሰነድ ማስረጃዎችን ከክስ መዝገቡ ጋር አያይዞ አቅርቧል፡፡

የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኃላ ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቶ 5 የሰው ምስክር ያሰማ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም ተከሳሽ ሟች ወንጀሉ ከመፈጸሙ በፊት እራሴን አጠፋለሁ የሚል የጹሁፍ መልዕክት ልካልኛለች የሰነድ ማስረጃው ከኢንፎርሜሽንና መረጃ ደህንነት አስተዳደር እንዲቀርብለት በጠየቀው መሰረት ውጤቱን ለመጠባበቅ ፍርድ ቤቱ ለታህሳስ 13 ቀን 2015 ዓ.ም ቀጠሮ በሰጠው መሰረት የኢንፎርሜሽንና መረጃ ደህንነት አስተዳደር በበኩሉም ጉዳዩን በተመለከተ ምንም አይነት የምልዕክት ልውውጥ አለመገኘቱን ለፍርድ ቤቱ በላከው ማስረጃ ላይ አመላክቷል፡፡

በዚህም መሰረት ተከሳሽ ተከላከል በተባለበት የወንጀል ድንጋጌ ስር ክሱን ማስተባበል ባለመቻሉ ጥፋተኛ ነህ በማለት የፍርድ ውሳኔውን ያስተላለፈ ሲሆን በዛሬው ዕለት የተሰየመው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሰው ግድያና ከባድ ውንብድና የወንጀል ችሎትም በከሳሽ ዐቃቤ ህግ የቀረቡ ማስረጃዎችን እና በተከሳሽ የቀረቡ የመከላከያ ማስረጃዎች መዝኖ ተከሳሹ ጥፋተኛ መሆኑን የዐቃቤ ህግ ማስረጃ በበቂ ያስረዳ በመሆኑ ተከሳሽ በሞት እንዲቀጣ ሲል የቅጣት ውሳኔውን አስተላልፏል፡፡(ፍትህ ሚኒስቴር)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe