ፍቅር እስከ መቃብር መጽሐፍ በ41 ሚሊዮን ብር ወደ ፊልም ሊቀየር ነው

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) “ፍቅር እስከ መቃብር” ልብ ወለድ መጽሐፍን ወደ ተከታታይ የቴሌቭዥን ድራማ ቀይሮ ለማቅረብ ከ’ሰው መሆን ፊልም ፕሮዳክሽን” ጋር በዛሬው ዕለት ይፋዊ የሥራ ውል ተፈራርሟል።
ውሉን የኢቢሲ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፍስሐ ይታገሱ እና እውቁ የፊልም ዳይሬክተር ሰውመሆን ይስማው (ሶሚክ) መፈራረማቸውን አቢሲ አስታውቋል።
በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደተገለጸው፣ ኢቢሲ ወደ ፊልም/ድራማ የመቀየር መብት ባለቤት የሆነለትን የፍቅር እስከ መቃብር የልብ ወለድ መጽሐፍን ‘ሰው መሆን ፊልም ፕሮዳክሽን’ ወደ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ በመቀየር በአራት ምዕራፍ፣ በ48 ክፍሎች ፕሮዳክሽን ሠርቶ እንዲያቀርበለት ተስማምቷል።
ድራማው በአማካይ 45 ደቂቃ ርዝማኔ ሲኖረው ለእያንዳንዱ የድራማ ክፍል (Episode) ተጨማሪ እሴት ታክስን ጨምሮ 863 ሺህ 75 (ስምንት መቶ ስድሳ ሦስት ሺህ ሰባ አምስት) ብር ለመክፈል ስምምነት ላይ ተደርሷል።
በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ መጽሐፉ ታሪካዊ ይዘት ያለው እንደመሆኑ ወደ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ እንዲለውጥ በሚደርግበት ጊዜ የዋናውን መጽሐፍ ታሪክ በማያፋልስ እና በማይበርዝ መልኩ ለመሥራት ከስምምነት ተደርሷል።
‘ሰው መሆን ፊልም ፕሮዳክሽን’ በአምስት ወራት ጊዜ ውስጥ የድራማውን የመጀመሪያ ምዕራፍ ማለትም (ከክፍል1-12) የተጠናቀቁ ሥራዎችን እንዲሁም በቀጣይ ዘጠኝ ወራት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ (48 ክፍሎች) አጠናቅቆ ለማስረከብ ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋር ስምምነት ላይ ደርሷል ሲል ተቋሙ ገልጿል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe