ፓኪስታን 4 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ የጦር መሳሪያዎችን ለሊቢያ ልትሸጥ ነው

ፓኪስታን አራት ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ የጦር መሳሪያዎችን ለሊቢያው ሀሊፋ ሀፍታር መንግስት ልትሸጥ ነው ተባለ።
የፓኪስታኑ ፊልድ ማርሻል አሲም ሙኒር የቻይናን ተዋጊ ጄቶች ለሊቢያ ለመሸጥ እንደተስማሙ ታውቋል።
ሊቢያ በዚህ ስዓት በሁለት የተለያዩ ሀይሎች ነው የምትመራው። ምስራቃዊ የሊቢያ ክፍል የሚተዳደረው በሀሊፋ ሀፍታር ሲሆን ይሄው ሀይል ቤንጋዚንን ዋና ከተማው ያደረገ ነው። ይህ አካባቢ የሊቢያ ትልቁ የነዳጅ ሀብት ያለበትም ጭምር ነው።
ምዕራባዊ የሊቢያን ክፍል እያስተዳደረ የሚገኘው በመንግስታቱ ድርጅት እውቅና ያለው መንግስት ሲሆን ትሪፖሊ ዋና መቀመጫው እንደሆነች ይታወቃል።
ባለፈው ሳምንት አሲም ሙኒር ወደ ቤንጋዚን ተጎዘው ከሀሊፋ ሀፍታር ጋር መነጋገራቸውን የፈርስት ፖስት ዘገባ አስታውሷል። የጦር መሳሪያ ሽያጭ ስምምነቱም በዚያው ወቅት እንደተፈረመ ተነግሯል።
ፓኪስታን ለሊቢያ ከምትሸጣቸው የጦር መሳሪያዎች መካከል 16 ከቻይና ጋር በጋራ በመሆን የተሰሩ ተዋጊዎች እንዳሉበት ተዘግቧል።
የጦር መሳሪያ ሽያጩ በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ የሚደረጉ ናቸው የተባለ ሲሆን ጠቅላላ ወጪያቸውም 4.6ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ ተሰምቷል። ገንዘቡ ለፓኪስታን ትልቅ ገንዘብ ነው ተብሏል።
የሀሊፋ ሀፍታር አስተዳደር ትኩረቱን ወደ ኢስላማባድ እንዲያዞር የተገደደው ዋነኛ አጋሩ የሆነችው ሩሲያ በጦርነት ላይ በመሆኗ ነው ተብሏል። የትሪፖሊውን መንግስት አሜሪካ እንደምትደግፈው ይታወቃል።
የቤንጋዚኑ መንግስት ቁልፍ አጋሮች ሩሲያ እና የተባበሩት አረብኤምሬትስ ናት። ሊቢያ በሙአመር ጋዳፊ ዘመን ከፓኪስታን ጋር ጥብቅ የሚባል ወዳጅነት የነበራት ናት።
በዚህ ምክንያት ሊቢያ የፓኪስታንን የኒውክሌር ፕሮግራም በገንዘብ እንደ ደገፈች ጭምር ይነገራል። በወቅቱም የ1ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አድርጋለች የሚባል ሲሆን በምላሹም ሊቢያውን ሳይንቲስቶች ደግሞ ስለ ኒውክሌር ሳይንስ እውቀት እንዲያገኙ ተደርጓል ተብሏል።
ፓኪስታን እራሷን የእስልምና ሀይማኖት ጠባቂ አድርጋ ነው የምትወስደው። ባለፈው ሚያዚያ ፓኪስታን ከፍተኛ የጦር ሰዎቿን በዓለማችን ትልቋ የሙስሊሞች መገኛ ወደሆነችው ናይጄሪያ ልካ ነበር።
ወደ 2ሺ የሚጠጉ የናይጄሪያ ወታደሮችም በፓኪስታን ጦር እንዲሰለጥኑ ተደርገዋል። በመስከረም ወርም ወደ ሳውዲ ልዑክ በመላክ በአንቺ የሚደርስ ጥቃት በእኔም እንደደረሰ ነው የምቆጥረው የሚል መልዕክት አስተላልፋ ነበር። በቅርቡም ወደ ኢንዶኔዥያ እና ጆርዳን የፓኪስታን ባለስልጣናት ተጉዘው ነበር።
ሁሉም እነዚህ ጉዞዎች ፓኪስታን እራሷን የእስልምና ጠባቂ መሆኗን ለማሳየት የተደረጉ ጥረቶች መሆናቸውን ዘገባው አትቷል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe