ፓኪስታን አሜሪካ እና ኢራን አንዳች ስምምነት ላይ ለመድረስ ተቃርበዋል አለች፡፡
አደራዳሪዋ ፓኪስታን የኦማን እና ኢራን የሆርሙዝ አስተዳደር ድርደር በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝም ይፋ አድርጋለች፡፡
የፓኪስታን የመከላከያ ሚኒስትር አሁን ነገሮች እንደገና ወደ ሰላም ስምምነት ያዘነበሉ ይመስላሉ ብለዋል፡፡ ምንም እንኳን በቀጠናው አዳዲስ ጥቃቶች እየተፈጸሙ ቢሆንም፤አሜሪካ እና ኢራን ግን የሆነ አይነት ስምምነት ለማድረግ መቃረባቸውን ነው ፓኪስታን ያስታወቀችው፡፡
ሌላኛዋ አስታራቂ ኳታር በፊናዋ በሆርሙዝ አስተዳደር ዙሪያ የሚደረገው ድርድር በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አስታውቃለች፡፡ የፓኪስታን መከላከያ ሚኒስትር ከብሉምበርግ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ በመጨረሻዎቹ ሁለት እና ሦስት ቀናት የታዩት ምልክቶች ወደሆነ አይነት ስምምነት መቃረባችንን ያሳያሉ ብለዋል፡፡
የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ትላንት ማክሰኞ ከፓኪስታን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሞህሲን ናቅቪ ጋር መገናኘታቸውን ይፋ ቢያደርጉም፤በምን ጉዳዮች እንደተወያዩ ግን ዝርዝር መረጃ አልሰጡም፡፡
የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ የሚኒስትሩ ጉብኝት በክልሉ ደህንነት እና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ለመወያየት መሆኑን አስታውቋል፡፡ አምስተኛ ወሩን ባስቆጠረው በዚህ ጦርነት በዋናነት በኢራን እና በሊባኖስ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል፡፡ ፓኪስታን እና ኳታር ደግሞ በዚህ ጦርነት ውስጥ አስታራቂ ሆነው ዘልቀዋል፡፡ ኢራንም በኦማን፡ዮርዳኖስ፡ኩዌት፡እስራኤል፡የተባበሩር አረብ ኤምሬትስ እና ሳውዲ በሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ ቤዞች ላይ ጥቃት ስታደርስ መምጣቷ አይዘነጋም፡፡
አሜሪካ በዚህ ወቅት ኢራን በድርድር ላይ እንደምትገኝ ብትገልጽም፤ኢራን በአስታራቂዎች በኩል መልዕክቶችን ከመለዋወጥ ባለፈ በቀጥተኛ ድርድር ላይ እንዳልሆነች አስታውቃለች፡፡
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሰኞ ምሽት አሜሪካ ለደረሰባት ጉዳት ቴህራን ካሳ መክፈል አለባት ብለዋል፡፡ ይህ ንግግራቸውም ዳግም ሁኔታውን ወደ ሌላ ምዕራፍ እንዳያሸጋግረው ይሰጋል፡፡//

