ዩክሬን ይህንን ምርጫ የምታደርገው ግን ዩናይትድስቴትስ ለመራጮች የደህንነት ዋስትና ስትሰጥ ብቻ ነው ብለዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ዩናይትድስቴትስ ለዩክሬን የደህንነት ዋስትና የምትሰጥ ከሆነ ምርጫ እንዲደረግ እንደሚፈቀዱ አስታውቀዋል፡፡
ዘለንስኪ በመጪዎቹ ሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ ዩናይትድስቴትስና ሌሎች የኪቭ ወዳጆች ምርጫውን ለማድረግ የሚያስችል የደህንነት ዋስትና የሚሰጡ ከሆነ መዘጋጀታቸውን ትላንት በይፋ ተናግረዋል፡፡
ዩክሬን አሁንም በጦርነት ውስጥ የምትገኝ፡በየቀኑም የሚሳኤል ጥቃቶች እየደረሱባት ቢሆንም ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ ሀገራት ለመራጮች የጸጥታ ዋስትና የሚሰጥ ከሆነ በመጪዎቹ ሁለትና ሦስራት ወራት ጊዜ ውስጥ ምርጫው ይደረጋል ብለዋል፡፡
የፕሬዝዳንት ዘለንስኪ የስልጣን ዘመን ባለፈው ዓመት ያበቃ ቢሆንም በጦርነቱ ምክንያት አስቻይ ሁኔታ ስሌለ ምርጫ ማድረግ አልተቻለም፡፡ ሩሲያ በተደጋጋሚ ስምምነት ላይ እንኳን ቢደረስ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ የስልጣን ጊዚያቸው ያበቃ በመሆኑ ከእርሳቸው ጋር ስምምነት መፈራረም እንደማይቻል ስትገልጽ ትሰማለች፡፡
በዚህ ስዓት እኔ ምርጫው እንዲደረግ ዝግጁ ነኝ ነገር ግን አሜሪካ እና የአውሮፓ ሀገራት ምርጫውን ለማድረግ የሚያስችል ድጋፍ እንዲደርጉ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ይህ ከሆነ ዩክሬን በቀጣዮቹ 60 እና 90 ቀናት ውስጥ ምርጫውን ለማድረግ ዝግጁ ትሆናለች ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ዘለንስኪ ይህንን የተናገሩት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከፖለቲኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ዘለንስኪ ጦርነቱን ምርጫ እንዳይደረግ እንደ ሰበብ እየተጠቀሙበት ነው የሚል አስተያየት ከሰጡ በኋላ ነው፡፡
ዘለንስኪን ጨምሮ ሌሎች ባለስልጣናትም የሩሲያ የአየር ጥቃት በቀጠለበት፡በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወታደሮች በጦር ግንባር ባሉበት እንዲሁም ሚሊዮኖች በተፈናቀሉበት ሁኔታ ምርጫን ማድረግ እንደማይቻል ነው የሚያምኑት፡፡
ከዚህ ውጭ አንድ አምስተኛው የሚሆነው የዩክሬን ግዛት በሩሲያ በተያዘበት ወቅት እንዴት ተደርጎ ምርጫውን ማድረግ ይቻላል የሚል መከራከሪያንም ያቀርባሉ በዩክሬን በኩል ያሉ ባለስልጣናት፡፡
በዩክሬን ህግ በጦርነት ጊዜ ምርጫ እንዲከናወን አይፈቀድም፡፡ ዘለንስኪ ከ2019 አንስቶ በስልጣኑ ላይ ይገኛሉ፡፡//

