ሊዎ ቴልስቶይ በማስታወሻ ደብተሩ ላይ ይህንን ቁምነገር ጽፏል

ቶልስቶይ ስለ ስነፅሁፍ በማያውቁት ዘንድ ሁሉ ስሙ ይታወቃል። ለመሆኑ ቶልስቶይ ማነው? ስለ ቶልስቶይ በአንድ ፖስት ማውራት ውቅያኖስን በማንኪያ እንደመጨለፍ ቢሆንም፣ ለመጨለፍ እነሞክር፦
❶
The Last Station ከታላላቆቹ የሩስያ ልብወለድ ደራሲያን አንዱን የሊዎ ቶልስቶይ የህይወቱን የመጨረሻ ጥቂት ወራት የሚተርክ መጽሐፍ ወይም የሚያሳይ ፊልም ነው። በቶልስቶይ ህይወት ውስጥ እነኚህን ቁንጽል ወራቶች ብቻ ቆርጦ ማሳየት ለምን አስፈለገ?ትክክለኛ ጥያቄ ነው። እንግዲህ እህ ብላችሁ አዳምጡኝ!
❷
ቶልስቶይ ውልደቱ ከታላቅ ጥንታዊ የመሳፍንት ዘር ነው። ቤተሰቦቹ በውል የሚታወቁና ‘ሁሉ በእጁ፣ ሁሉ በደጁ’ የሚባሉ አይነት ነበሩ። ወላጆቻቸው በልጅነታቸው ቢሞቱባቸውም፣ ቶልስቶይና አራት ወንድምና እህቶቹ አንድም ሳይጎድልባቸው ተንደላቀው ነው ያደጉት።
❸
ሊዎ ቴልስቶይ በማስታወሻ ደብተሩ ላይ ይህንን ቁምነገር ጽፏል። ላካፍላችሁ፦
በልጅነቴ ከእናቴ ጋር ዘወትር ትያትር ቤት እንሄድ ነበር። ቤተሰቦቼ ቢጠሯቸው የማይሰሙ ሃብታም ነበሩ። ሞስኮ ውስጥ በክረምት በረዶ ያለማቋረጥ ይወርዳል። ያኔ እናትና ልጅ ትያትር ቤት ውስጥ ነን።
ትያትር ቤቱ የትራጄዲ ተውኔት የሚያሳይ ከሆነ እናቴ ታለቅሳለች። እንባ በአይኖቿ ግጥም ብሎ በጉንጮቿ ያለማቋረጥ ይወርዳል። እኔ በልቤ ‘እናቴ ምን አይነት ሩህሩህ ሴት ናት!’ ብዬ አስባለሁ።
ተውኔቱ አልቆ ከትያትር ቤት ስንወጣ ሹፌራችንን መኪናው ውስጥ በቅዝቃዜ ተኮራምቶ እናገኘዋለን። እንግዲህ ሹፌራችን መኪናውን ጥሎ መሄድ አይችልም። መቼ ከትያትር ቤቱ እንደምንወጣ አይታወቅም። ሁሌም ዝግጁ እና ንቁ ሆኖ መጠበቅ አለበት። እንደዚያ ተጨብጦ፣ ተኮራምቶ እናቴ ዘወር ብላ እንኳን አታየውም። አንዳንዴ ሹፌራችን በቅዝቃዜ ሞቶ በሌላ ሹፌር የሚተካበት ግዜ ነበር። እናቴ አንድ ዘለላ እንባ እንኳን አታፈስም። በመጨረሻ የእናቴ እንባ የማስመሰልና የሃሰት መሆኑን ተረዳሁ።
❹
ቶልስቶይ ዩኒቨርስቲ ለመግባት ቢታደልም ብዙም ሳይቆይ አቋርጦ ወጣ። መምህራኑ ሲገልጹት ”ለመማር የተሳነው፣ ፍላጎቱም የሌለው ነበር“ ይሉታል። ከኮሌጅ ወጥቶም ቁማርተኛ፣ ሰካራምና ብኩን ሆነ። ቶልስቶይ በአንድ ወቅት በቁማር ቤት እስከመበላት ደርሷል።
የቶልስቶይ የህይወት መስመር መለወጥ የጀመረው ሁሉን እርግፍ አድርጎ የጦር ሰራዊቱን ሲቀላቀል ነው። ይህ አጋጣሚ የጦርነት አስከፈነትን የተረዳበትና በቀላሉ የወታደሮች አኗኗር የተማረከበት ግዜ ነበር። መንፈሳዊ ማንነቱ የተጸነሰው ያኔ ነው። ቶልስቶይ ከሃብታም ቤተሰብ ቢወለድም ቀላሉን የገጠር ኑሮ ይመርጥ ጀመር።
ቶልስቶይ የተገኘው ከሃብታም ቤተሰቦች ነበር። አባካኝ ቁማርተኛ ነበር። የጦር ሰራዊት አባል ከሆነ በኋላ ግን ተለወጠ። ድህነት ትክክለኛው የህይወት መንገድ ነው ብሎ አመነ። የግል ሃብት ለምኔ ማለት አመጣ። የመፅሀፎቹን የቅጂ መብት ለህዝብ አደረገ። ይህ ከሚስቱ ሶንያ ጋር አጋጨው። እሷ የባላባትነት ኑሮ የሚጥማት የልጆቿ የወደፊት ህይወትም የሚያሳስባት ነበረች።
ተገልጦለት ይሁን ተደፍኖበት መጻፍ የጀመረውም በዚህን ግዜ አካባቢ ነው ተብሎ ይታመናል።
በእንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ጀርመንኛ፣ ጣሊያንኛ፣ ላቲን፣ ግሪክ፣ ስፓኒሽ ይፅፋል፣ ያነባል፣ ይናገራል። በቤቱ በ39 ቋንቋዎች የተፃፉ 23,000 መፅሀፍት ነበሩት። ከወታደርነቱ ባሻገር በመላው አውሮፓ እየተዟዟረ ያደረጋቸው ጉብኝቶች ቶልስቶይን እስከወዲያኛው ለውጠውት አረፉ።የተደላደለ ኑሮ የነበረው ቶልስቶይ የግል ሀብት ለምኔ ማለት አመጣ። ገንዘብ የማይበቃው ቶልስቶይ ሶሻሊስታዊ ዝንባሌ አዳበረ።ቶልስቶይ እንደገና ተወለደ።ሌላ ሰው ሆነ።
❺
ቶልስቶይ የ34 አመት ወጣት እያለ የ18 አመቷን ሶፊያ አገባ። 48 አመት በጋብቻ ሲኖሩ 13 ልጆች አፍርተዋል። 3ቱ ለጆቻቸው ግን በህጻንነት ሞተውባቸዋል።
እድሜው 40ዎቹ መጨረሻ ሲደርስ በጥልቅ ድብርት ተዋጠ። ህይወቴ መራር ቀልድ ነው ብሎ ተናገረ። ከዚህ ድብርት መንጭቆ ያወጣው የክርስቶስ አስተምህሮ ነበር። ቶልስቶይ ሃይማኖትን የሚቃወም፣ ነገር ግን ጥልቅ መንፈሳዊ ህይወትን የሚተገብርና የሚያበረታታ ነበር። ቀለል ያለ ኑሮ ለመኖር፤ የስራዎቹንም የቅጂ መብት ለህዝብ ለማድረግ ሞከረ።
ቶልስቶይ ክርስቲያን ነበር፤ ተጠምቋል። ነገር ግን ከሩስያ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጋር የማይስማማባቸው ጉዳዮች ነበሩ። ፀሐፊ ስለሆነም ልዩነቱን በግልፅ ይናገራል። በዚህም በ1901 ቤተክርስቲያን አውግዛው ነበር።
ስለዚህ ጉዳይ ቶልስቶይ ሲጠተቅ እንዲህ ይል ነበር፦
“የማምነውም የምክደውም ነገር የለም። የእናንተን ትምህርት ግን ጥሼዋለሁ”
በ50 አመቱ ቶልስቶይ ስጋ መብላት አቆመ፤
ከዚያን ግዜ ጀምሮ ቶልስቶይ ቬጅቴሪያን (አትክልት ተመጋቢ) ሆነ። በዘመኑ ብርቅ ነበር። ቶልስቶይ ከግዜው የቀደመ ሰው ነበር። ወደፊት ሁሉም ሰው ቬጅቴሪያን ይሆናል የሚል እምነት ነበረው። አልኮል መጠጣት ተወ። የግል ሃብት ለምኔ ማለት ያመጣው ደግሞ ገና ድሮ ነው። ይሄ ሁሉ ተደማምሮ በቶልስቶይና ሚስቱ መካከል ያለውን ግንኙነት በውጥረት የተሞላ እንዲሆን አድርጎታል።
❻
War and Peace ታላቅ የሪያሊዝም ልብወለድ ነው። የቶልስቶይ የአመታት ጥረት ውጤት ነው። ልብወለዱን ሲጽፍ የታሪክ መዛግብትን በጥልቀት መርምሯል፤ ከጦርነቱ ለተረፉ ሰዎች ብዙ ቃለመጠይቅ አድርጓል። ተጽፎ ሲያልቅ የሩስያ ብሎም የአለም ስነፅሁፍ አብይ ስራ ሆነ።
ልብወለዱ 1500 ገጾች አሉት። ከ200 በላይ ገፀባሕርያት አሉት። ግማሾቹ የእውነት ሰዎች ሲሆኑ የተቀሩት ፈጠራ ናቸው—ታሪካዊ ልብወለድም አይደል።
ታዲያ ለዚህ ልብወለድ መታተም ቶልስቶይ ብቻ አልበቃም—ሚስቱ ሶፊያም ተጨምርበታለች። ቶልስቶይ የድንቅ ደራሲነቱን ያህል እጅ ፅሁፉ ለማንበብ የማይመች አሰቸጋሪ ነበር።
ታዲያ ቶልስቶይ የቸከቸከውን ወደ የሚያምር የእጅ ፅሁፍ የምትቀይረው ሶፊያ ነበረች። ሁሌ ማታ ራት ተበልቶ፣ ሁሉም ወደ እንቅልፍ ከሄደ በኋላ አለም ሁሉ ሲያንቀላፋ ሶፊያ ትነቃለች። በአጉሊመነፅር ጭምር እየታገዘች ዋር ኤንድ ፒስን ትገለብጣለች። ቢያንስ 7 ግዜ ሙሉውን ገልብጣለች። ከ10,000 ገፆች በላይ ነው—ከባድ መስዋእትነት።
ቶልስቶይ የእጅ ፅሁፉ አይነበብም ነበር። በተለይ ለአሳታሚዎች የቀን ቅዠት ነበር። እንዲያውም አንዱ አሳታሚ አፍ አውጥቶ “እጅ ፅሁፍህ አስቀያሚ ነው!” ብሎታል። ሃሳብን በፅሁፍ ውበት አትመዝኑ ማለት ይሄኔ ነው። ነገር ግን እነዚህ ውብ ሃሳቦች እንዲታተሙ መነበብ ስላለባቸው የቶልስቶይ ሚስት ሶንያ ማገዝ ጀመረች። የቶልስቶይን ፅሁፍ በእጆቿ እየገለበጠች ለአሳታሚዎች ትልክ ነበር።
በነገራችን ላይ ይሄ ድንቅ ልብወለድ ተፅፎ፣ ታትሞ፣ ተነቦ አለምአቀፍ ተወዳጅነት ከማግኘቱ በፊት 20 ግዜ ያህል አይረባም፣ አንቀበልም፣ አናሳትምም የሚል መልእከት ደርሶታል። ሶፊያም 7 ግዜ ደጋግማ በእጇ ለመገልበጥ የተገደደችው፣ ወደ ተለያዩ አሳታሚዎች ረቂቁን ለመላክ ነው። በነገራችን ላይ ቶልስቶይ እና ሚስቱ ሶፊያ በጣም የሚዋደዱ ነበሩ። ሶፊያ 10000 ገፅ ለመገልበጥ ያልከበዳት፣ ከልቧ ስለገለበጠች ሳይሆን ይቀራል። የሰው ልጅኡኡፅናትና ጥንካሬ አጃኢብ ነው! እኔ አንዴ ገልጦ ለማንበብ ከብዶኛል!
378 ምእራፎች አሉት! ካነበቡት አፍ እንደሰማነው ታሪኩ ሊገባን የሚጀምረው ፣ ውሉ የሚጨበጥልን ቢያንስ 100 ገፅ ካነበብን በኋላ ነው። ፈጣን አንባቢ ከሆናችሁ በ10 ቀናት ውስጥ አንብባችሁ ትጨርሱታላችሁም ተብለናል።
አንድ “ዘገምተኛ” አንባቢ “War and Peace”ን አንብቦ ለመጨረስ 17 አመት ፈጅቶበታል። ጥንቸሎች ቢፈጥኑም መንገዱን በደንብ የሚያውቁት ኤሊዎች ናቸው። ይሄ አንባቢኮ በደንብ እያጣጣመ ይሆናል ያነበበው።
❼
ታላላቅ ደራሲያን የጻፏቸው ሁሉም መጽሀፍት ምርጥ ላይሆኑ ይችላሉ።አሁን ሊዎ ቶልስቶይ ቀሽም መጽሀፍ ጽፏል ብሎ ማን ያስባል?እራሱ ሊዎ ቶልስቶይ!ቶልስቶይ ወጣት እያለ አንድ የግጥም መድብል ጽፎ፡አሳትሞ ነበር።ኋላ በበሰለ አእምሮው ቢያነበው፡ አሳፈረው።የታተሙ ቅጾቹንም ባገኘ ቁጥር እየገዛ ያቃጥል ነበር። አለመብሰል ከመጽሀፉ ጋር አብሮ ባይቃጠልም፡ ግዜ እና ሌሎች ጉልበታሞች የሚያመጡት የአስተሳሰብ ለውጥ ጉልህ ነው። እስቲ ከአስር አመት በፊት የጻፋቹትን ደብዳቤ አንብቡና ተደነቁ—በሀሳቡ፡በቋንቋው፡በፊደላት ስህተቱ ጭምር!
❽
አና ካሬኒና አሳዛኝ የፍቅር ታሪክ ነው። ያለ ጥርጥር በስነፅሁፍ ታሪክ ውስጥ ከምርጦቹ አስር ልብወለዶች አንዱ ነው። ከሌላው የቶልስቶይ ልብወለድ “ዋር ኤንድ ፒስ” ጋር የሪያሊዝም ቁንጮ ስራዎች ናቸው። ሌቪን የተባለው ገፀባህሪ ከራሱ ከቶልስቶይ የተቀዳ መሆኑን አንብቤያለሁ። በሌቪን አንደበት የቶልስቶይ ሃሳብ፣ እምነትና አስተያየት ይገለፃል።
ቶልስቶይ ገፀባህሪዎቹን ሚዛን ላይ እያስቀመጠ የሚመዝን ደራሲ አይደለም። በብእሩ እየፃፈ ይታዘባቸዋል እንጂ። አፃፃፉ አንባቢም እንደራሱ ታዛቢ እንዲሆን የሚጋብዝ ነው።
ልብወለዱ ሲጀምር እንዲህ የሚል መግቢያ ጥቅስ አለው፦
“ሁሉም ደስተኛ ቤተሰቦች ደስተኛ የሚሆኑት በተመሳሳይ መንገድ ነው። ደስተኛ ያልሆኑት ግን በየራሳቸው መንገድ ነው”
በ800 ገፅ ቶልስቶይ ደስተኛ ስላልሆኑት ቤተሰቦች ይነግረናል።
አና ካሬኒና ባለትዳር ሴት ናት። ባሏ የመንግስት ባለሥልጣን ሲሆን አናን በ20 አመት ይበልጣታል። ባሏን ትታ ከአንድ መልከመልካም ጎልማሳ ጋር በፍቅር ወደቀች። ባሏን እንዳትተወው ባህልና ወግ አስሮ ይይዛታል። ከዚህ ቭሮንስኪ ከተባለ ሰው ጋር ደግሞ ቅልጥ ያለ ፍቅር ይዟታል። በመጨረሻ ግን ትወስናለች ባሏን ጥላ ከቭሮንስኪ ጋር ወደ ጣሊያን ኮበለሉ። አዲሱ ቤታቸው ብዙም አልተመቻቸውም። ተመልሰው ወደ ቅዱስ ፒተርስበርግ ይመጣሉ። ነገር ግን እዚህ በማህበረሰቡ መገለል ይደርስባቸዋል።
ልብወለዱ ሌላም ታሪክ አለው። ሌቪን የተባለው ገፀባህሪ በብዙ መልኩ ቶልስቶይን ይመስላል። የመኳንንት እና የሃብታም ዘር ቢሆንም ሁሉንም እርግፍ አድርጎ ወደ ገጠር ይሰደዳል።
ልብወለዱ በአጠቃላይ በብዙ ገጾቹ ስለ ቤተሰብ፣ ጋብቻ፣ ታማኝነት፣ ግብረገብነት፣ ሃይማኖት፣የመደብ እና የፆታ ልዩነት ይዳስሳል። ብታነቡት ሁለት ነገሮች ትረዳላችሁ፦
፩) ልብወለዱ ጥሩ ስለሆነ ግዜያችሁን እንዳተረፋችሁበት ትረዳላችሁ
፪) ሊዎ ቶልስቶይ በጣም የተዋጣለት ደራሲ እንደሆነ ትገነዘባላችሁ
በአማርኛ ማንበብ ለምትፈልጉ በወጋየሁ በለው ተተርጉመዋል። ከጥቂት አመታት በፊት ሸገር ሬዲዮ በአዘቦት ተረክ ይተረክ ነበር። ከዚህ ባሻገር በፊልም፣ በኦፔራ ፣ በባሌት ፣ በመድረክ ቲያትር፣ በቴሌቪዥን ፣ በሬዲዮ እንዲመች ተደርጎ ተደጋግሞ ተሰርቷል።
➒
ቶልስቶይ ብዙ ደራሲዎችን ያደንቃል። በዘመኑ ከነበሩት ደራሲዎች ጋር ጓደኛ ነበር። ግን ጭራሽ የማይወደው አንድ ደራሲ ነበር። እሱም ታላቁ ሼክስፒር ነው።
ቶልስቶይ የኖቤል ሽልማት አይፈልግም። የኖቤል ሽልማት ቢፈልግ 100 ይገባው ነበር። ቶልስቶይ ያለፈው ዘመን ብቻ ሳይሆን ከሆሜር እና ሼክስፒር ዘለአለማዊነት ጋር የሚገዳደር ችሎታ እና አስተዋጽኦ ያለው ደራሲ ነው። ግን ቶልስቶይ ለሽልማት የሚጓጓ ስብእና አልነበረውም።
በ1860ዎቹ ቶልስቶይ ፊቱን ወደ ትምህርት አዞረ። የመንግስትን ስርአተ-ትምህርት ወደጎን ብሎ የተማሪዎቸን ጉጉት መኮትኮት እንደሚሻል ተረዳ። የተማሪዎችን አካላዊ ቅጣትና የክፍል ፈተና አስቀረ። መንግስት ግን ትምህርትቤቱን በጥርጣሬ መመልከት ስለጀመረ ብዙም ሳይቆይ ተዘጋ።
❿
ታዲያ ቶልስቶይ የመጣበት የባላባትና ሎሌ ስርዓት በአንድም በሌላ መልኩ በቀላሉ የሚላቀቀው አልሆነም።ከሚስቱ ጋር የሚፋቀሩና የሚተሳሰቡ ቢሆኑም እሷ የጌትነት ኑሮ ይበልጥ የሚጥማት አይነት ነበረች።
ወደ ፊልሙ ታሪክ ስንመጣ ግዜው 1910 ሆኗል። ቶልስቶይ አሁን የ82 አመት የእድሜ ባለጸጋ ነው። ገጠር በሚገኘው ይዞታው ላይ ከሚስቱና ከልጆቹ ጋር ይኖራል። የቶልስቶይ ደቀ-መዛሙርት(ቶልስቶያውያን)እና ሚስቱ ትልቅ ጦርነት ውስጥ ናቸው። ደቀ-መዛሙርቶቹ ከቶልስቶይ ሞት በኋላ መጽሀፎቹ የህዝብ ሀብት(public domain) እንዲሆኑ ይፈልጋሉ። ቶልስቶይ የግል ንብረት ማካበት ተቃራኒ ስለሆነ የቶልስቶያውያኑ ደጋፊ ነው። ይህ ደግሞ ሚስቱንና ልጆቹን ያለምንም ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ የሚያስቀር ነው።
⓫
ተርጊኔቭ ወዳጁን ፍሉቤርን ለመኡጎብኘት ፓሪስ ውስጥ ነው። ቶልስቶይም መላ አውሮፓን እየዞረ ነው። ፈረንሳይ ሲደርስ ሁለቱ ተገናኙ።
(ካፌ ውስጥ ቁጭ ብለው ምን ሊያወሩ ይችላሉ በምናብ የተፃፈ)
ተርጊኔቭ፦ ልብወለድህ ምን ደረሰ?
ቶልስቶይ፦ ታሪኩ እየተበታተነብኝ ነው። የናፖሌዎን ወረራ መልከ ብዙ ነው። በስም የሚጠቀሱ ገፀባህሪያት ከ200 አልፈዋል። ትልቅ ጦርነት ትልቅ ታሪክ ስለሆነ ትልቅ መፅሀፍ ይወጣዋል
ተርጊኔቭ፦ ለመሆኑ ዶስቶቭስኪ እንዴት ነው?
ቶልስቶይ፦ ደህና ነው ከዛች ከምትጥለው ነገር በስተቀር። ደግሞ እንደሚወዳት ታውቃለህ። ሊጥለው ሲል ውብ ውብ ሃሳቦች ይከሰቱለታል። የዚህ አለም ነገር እንዲህ ነው። ማሩን ለመብላት የንቧን ንድፊያ መቻል አለብህ!
ተርጊኔቭ፦ የኔ ብድር ደሞ ነበረበት። ባለፈው መቶ ሩብል ተበደረኝ። እሱን ሳይመልስ ሃምሳ ጨመርኩለት።
ቶልስቶይ፦ ቢበደርህስ! አይደለም ገንዘብ ነፍስህንስ ቢበደር። ዶስቲቭስኪ እኮ ነው። በዚያ ላይ ቁማርተኝነቱን ታውቃለህ ፤ ብኩን ነው። አንተም ሃብታም ነህ። ገንዘብ የሚቸግርህ ሰው አይደለህም። እንደሱ ውብ ሃሳቦችን የሚያፈልቅ አእምሮ ስለ ሩብል እና ኮፔክ(የሩስያ ገንዘብ እና ሳንቲም) መጨነቅ የለበትም። የሱን ብድር እኔ እከፍላለሁ። ለሱ እንዳትነግረው።
⓬
ቶልስቶይ ብዙ የብእር ጓደኞች ነበሩት። ከአንባቢዎቹ ጋርም ደብዳቤ ይፃፃፋል። ከታዋቂ የብእር ጓደኞቹ መሐል ማህተመ ጋንዲ አንዱ ነበር። ሁለቱም ክፋትን በጉልበት ወይም በጥላቻ ማሸነፍ እንደማይቻል ይስማማሉ። የቶልስቶይ The Kingdom of God is within you/የእግዚአብሔር መንግስት በውስጣችሁ ነው የሚለው ስራው በማህተመ ጋንዲ ላይ ግዙፍ ተጽእኖ አሳርፎበታል። ምን ጋንዲ ብቻ?! ማርቲን ሉተር ኪንግም “በሰላማዊ እንቢተኝነት” ፍልስፍና ይምላል።
በ1910 ቶልስቶይ 82 አመት ሞልቶታል። ከቤቱ ወጥቶ በእግሩ መጓዝ ጀመረ። ከጥቂት ቀናት በኋላ አስከሬኑ በአንድ የባቡር ጣቢያ ተገኘ። ለመጨረሻ ግዜ ሲያነበው የነበረው መጽሐፍ የዶስቶቭስኪ የካራማዞቭ ወንድማማቾቸን ነበር።
በቶልስቶይ ውብ መልእክት ብንጨርስስ?!
እያንዳንዱ ታላቅ ደራሲ ራሱን የቻለ መንግስት ነው። ለዚህ ነው መንግስታት የገዛ ደራሲዎቻቸውን የሚጠሉት።
ሊዮ ቶልስቶይ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe