መንግሥት በኢንተርኔት ላይ በጣለው ገደብ ከ7 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ኪሳራ ደርሷል ተባለ

ሐሙስ ሐምሌ 6 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ መንግሥት ከየካቲት 04/2015 ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ ባሉት አምስት ወራት በኢንተርኔት አገልግሎት ተደራሽነት ላይ በጣለው ሕጋዊ መሰረት በሌለው ገደብ ምክንያት በአገሪቱ የደረሰው የኢኮኖሚ ጉዳት ከ7 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ማለፉን የመብቶችና ዴሞክራሲ እድገት ማዕከል ገልጿል፡፡

“ፖለቲካዊ አለመረጋጋቶችን ተከትሎ፤ ከ2008 ወዲህ የበይነመረብ ግንኙነትን ማቋረጥ በኢትዮጵያ እየተባባሰ የመጣ ችግር ነው” ያለው ማዕከሉ፤ የበይነመረብ ግንኙነት መቋረጡ የዴሞክራሲና የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዕድገት ጸር መሆኑን አመላክቷል፡፡

መንግሥት ዋና ዋና የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች በኢትዮጵያ እንዳይጎበኙ እገዳ መጣሉ ሕጋዊ መሰረት የሌለው ነው ሲልም ገልጿል፡፡

የበይነመረብ ግንኙነት መቋረጥ ትኩረት ሊያገኝ ባለመቻሉም የሰብዓዊ መብቶች እሴቶችን እንዲሁም በሕገ መንግሥቱ የተጠበቁ የሰብዓዊ መብቶችንና ነፃነቶችን እየገፈፈ መሆኑንም ነው የጠቀሰው።

በዚህም በኢንተርኔት አገልግሎት ላይ በተጣለው ገደብ ከ140 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር በላይ የኢኮኖሚ እንዲሁም፤ 27 ነጥብ 8 ሚሊየን ዶላር የውጭ ቀጥታ የምርት ገበያ ኪሳራ ማድረሱን እና 2 ሺሕ 372 ሰዎች ሥራ እጥ እንዲሆኑ ማድረጉንም አዲስ ማለዳ ከማዕከሉ ያገኘችው መረጃ አመላክቷል፡፡

በዚህም የበይነመረብ ግንኙነት መቋረጥ ዘመናዊ ንግዶችን በማደናቀፍ ኢኮኖሚው በየጊዜው በሚሊዮን ዶላሮች እንዲያጣ እንደሚያደረገውና፤ የምርጫ ተዓማኒነትን የሚያጎድል መሆኑን ማዕከሉ ገልጿል።

ማዕከሉ በኢትዮጵያ የበይነመረብ ግንኙነትን የማቋረጥ ተግባር “ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ እና መረጃ የማግኘት መብቶችን” እያደናቀፈ መሆኑን ገልጾ፤ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ይህንን የመንግሥትን ሕጋዊ መሠረት የሌለው ተግባር በፍርድ ቤት ሊሞግቱት እንደሚገባም አሳስቧል።

እንዲሁም የኢትዮጵያ ሕዝብ የበይነመረብ ግንኙነት ማቋረጥን መቃዎም አለበት ያለው ማዕከሉ፤ በኢንተርኔት ገደብ የሚጣለው የመረጃ የማግኘት ማዕቀብ እንዲነሳ የራሱን ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁሟል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe