በጎዳና ላይ እየተንቀሳቀሱ ቡና፡ሻይ፡ የእንጨት መፋቂያ ፡ማስቲካን እና ሶፍት የሚሸጡ ግለሰቦች ንግድ ፈቃድ ሊያወጡ ነው፡፡ ይህ ግን የሚሆነው በዓመት ውስጥ የሚያገኙት ገቢ 200ሺ ብር የሚደርስ ከሆነ ነው ተብሏል፡፡
መደበኛ ባልሆነ ንግድ መሰማራት የሚችሉት የከተማዋ ነዋሪዎች ብቻ መሆናቸውን የሚደነግግ ደንብ መጽደቁም ተሰምቷል፡፡
መደበኛ ያልሆነ የጎዳና ላይ ንግድን ስርዓት ለማስያዝ ይረዳል ተብሎ በፀደቀው ደንብ ላይ በዚህ ስራ መሰማራት የሚችሉት የአዲስ አበባ መታወቂያ ያላቸውና ነዋሪ የሆኑ ብቻ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ፍትህ ቢሮ ገልጻል፡፡
መደበኛ ያልሆነ የጎዳና ንግድ ላይ የብቃት ማረጋገጫና የተለየ የፈቃድ አይነት ያስፈልገዋል የተባለ ሲሆን እነዚሁ ጎዳና ላይ የሚነግዱ ግለሰቦች በአንድ ዓመት ውስጥ የሚያገኙት ገቢ 200ሺ ብር ከደረሰም ወደ መደበኛ ንግድ የሚሸጋገሩበት አሰራር እንደሚኖር ታውቋል፡፡
ደንቡ በጎዳና ንግድ ምክኒያት ሊፈጠር የሚችልን የጸጥታ እና ደህንነት ስጋት ፡የትራፊክ እንቅስቃሴ መስተጓጎልን ለማስቀረት እንዲሁም ህግና ስርዓት ተከትለው የሚሰሩ ነጋዴዎች እንዳይጎዱ ይረዳል ተብሏል፡፡
እነዚሁ አካላት በከተማዋ መሬትና ልማት ቢሮ ለመነገጃ ተብሎ በተለዩ ዋና ዋና መንገዶችና በሚሰጡ ሌሎች ቦታዎች ገደብ ተቀምጦ ለተወሰኑ ስዓታት እንዲሰሩ የሚፈቀድበት ሂደት እንደሚኖርም ታውቋል፡፡
በኢመደበኛ ንግድ ለመሰማራት ከተቀመጡ መስፈርቶች መካከል እድሜ የሚገኝበት ሲሆን ከ18 ዓመት በላይ የሆናቸው ዜጎች ብቻ በዘርፉ ፈቃድ አውጥተው መስራት እንደሚችሉ ተገልጻል፡፡//

