‹አንጋፋ የሙያ ጓደኞቼ ይህንን ክብር ሳያገኙ እየታመሙ ከዚህ ዓለም መለየታቸው ቢቆጨኝም ለዚህ ክብር ስላበቃችሁኝ ከልቤ አመሰግናለሁ ›
አንጋፋው ድምፃዊ ማህሙድ አህመድ ላለፉት 63 ዓመታት ከነገሰበት መድረክ ሰሞኑን በታላቅ አክብሮት አድናቆትና ምስጋና ተሰናብቷል፡፡ በአሜሪካ ቨርጂኒያ በሙያ ጓደኞቹና የቅርብ ወዳጆቹ በተዘጋጀው በዚህ ‹አክብረን እንከበር› የምስጋና ፕሮግራም ላይ ወጣትና አንጋፋ አርቲስቶች የተሳተፉበት በአይነቱ ልዩ የሆነ ኮንሰርት ተካሂዷል፡፡ ተወዳጁ አርቲስት ታማኝ በየነ የተዘጋጀውና በአዳራሹ ውስጥ ላሉ ታዳሚያንነና ለማህሙድ የተበረከተው የማህሙድን የሙዚቃ ጉዞ የሚያሳየው ዘጋቢ ፊልም ብዙዎችን በትዝታ ውደ ኋላ መልሷል፡፡
‹ዝቅ ብሎ ጀምሮ ከፍታውን የጨበጠ ድምፃዊ› በሚል ርዕስ ተዘጋጅቶ የቀረበው የታማኝ ዘጋቢ ፊልም የማህሙድን ከሊስትሮ ጠራጊነት ተነሰቶ እንዴት በዝና ማማ ላይ እንደደረሰ ይተርካል፡፡ ዘጋቢ ፊልሙ ከታየ በኋላ የዋሽንግተን ዲሲ ከንቲባን ጨምሮ የተለያዩ ወዳጆቹና የሙያ ባልደረቦቹ ያመጡለትን ስጦታ ተቀበሏል፤ ማህሙድ በዚህ የመሸኛ ፕሮግራም ላይ ባደረገው ንግግር ‹አንጋፋ የሙያ ጓደኞቼ ይህንን ክብር ሳያገኙ እየታመሙ ከዚህ ዓለም መለየታቸው ቢቆጨኝም ለዚህ ክብር ስላበቃችሁኝ ከልቤ አመሰግናለሁ › ብሏል፡፡ የእለቱ ፕሮግራም ከመካሄዱ ቀናት በፊት ትኬት ያለቀ ሲሆን ‹ማህሙድ ራሱ ትኬት አላገኘም› ብሚል እስከመቀለድ ተደርሷል፡፡ የማህሙድ ሽኝት ፕሮግራም የፊታችን ጥር 3 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚካሄድ ቀደም ሲል ተገልፃል፡፡
ተወዳጁ ድምጻዊ ግርማ ተፈራ ‹እናመሰግንሃለን!› የተሰኘ ዜማ ለማህሙድ አህመድ ያቀነቀነ ሲሆን ማህሙድ ራሱ ‹እግዚአብሔር ይመስገን፤ እግዚአብሔር ይመስገን ለዚህ ያደረሰን እግዚአብሔር ይመስገን › የተሰኘውን ሃይማኖታዊ መዝሙር በፕሮግራሙ መክፈቻ ላይ ዘምሯል፡፡ ለጨረታ የቀረበው የማህሙድ አህመድ ስዕል በከፍተኛ ዋጋ ተሸጧል፡፡
ከዓመታት በፊት ለያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት ተማሪዎች የህይወት ልምዱን ያካፈለው አንጋፋው ድምፃዊ ማህሙድ አህመድ ‹ብታምኑም ባታምኑም ጉሊት ቁጭ ብዬ እንጀራ እሸጥ ነበር › ብሏል፡፡ማህሙድ ለአንድ ሰዓት ያህል የሙዚቃ ህይወቱን ሂደት ከተናገረ በኋላ ልዩ ልዩ ጥያቄዎች ከተማሪዎችና ከጋዜጠኞች ተጠይቆ መልሷል፡፡
ትውልድና ዕድገት
ቤተሰቦቼ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ነበሩ፡፡ አሁን በሕይወት የሉም፡፡ የተወለድኩት አሜሪካ ግቢ በ1933 ዓ.ም ነው፡፡ እስከ ሶስት ዓመቴ ድረስ አሜሪካ ግቢ ካደግኩ በኋላ በሶስት ዓመቴ ወደ ጉለሌ አርበኞች ት/ቤት ፊትለፊት ያለው ኦሎምፒያ ኳስ የሚባል የግሪክ ክለብ ነበር እዚያ ውስጥ አባቴ ይሰሩ ነበር፡፡ በዚያ ስፖርት ክለብ ውስጥ እየሄድኩ የቅርጫት ኳስ፣ የእጅ ኳስ ሜዳ፤ ስፖርተኞች ከተጫወቱበት በኋላ ሜዳውን ውሃ እያጠጣሁ እየደመጥኩ አስተካክል ነበር፡፡ አባቴ በሌሉበት ጊዜ የዚያ ስራ ሀላፊነት የኔ ነበር፡፡
ትምህርት ቤት
ትምህርት ቤትን በተመለከተ ብዙ ባይገባኝም መማር ጀምሬ ነበር፤ ትምህርት ቤት ስገባ ምናልባት 8 ዓመት 9 ዓመት ይሆነኝ ይሆናል፡፡ ቄስ ት/ቤትም ከጓደኞቼ ጋር ገብቼ ነበር፤መጀመሪያ በእርግጥ ሙስሊም ት/ ቤት ነበርኩ፡፡ ወደ 15 ዓመት ሲሆነኝ አባቴ የሚሰሩበት የግሪክ ክለብ ሲዘጋ ስራ ፈቱ፡፡ ከእናቴ ጋር ሆኜ የቤተሰቡን ህይወት ለማገዝ ከእናቴ ጋር ብታምኑም ባታምኑም ጉሊት ቁጭ ብዬ እንጀራ እሸጥ ነበር፡፡ ወደ ጫካ ሄጄ ጭራሮ ና ማገዶ ለቅሜ በማምጣት ለእናቴ እንጀራ መጋገሪያ አቀርብላት ነበር፡፡
በዚህ ሁኔታ ለ6 ዓመት ያህል ትምህርት ቤት እየሄድኩ ስመለስ ሊስትሮ ሆኜ ጫማ እጠርግ ነበር፡፡ ከጓደኞቼ መሀከል ሰነፉ ተማሪ እኔ ነበርኩ፡፡ ጥያቄ ሲቀርብ ግን የምመልሰው እኔ ነበርኩ፡፡ ግን ፈተና ላይ ስንቀመጥ ነርቨስ ስለምሆን መስራት አልችልም ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ መማር መቀጠል አልቻልኩም፡፡
ሊስትሮና ሙዚቃ
ማታ ማታ እናቴ ዘፈን ታንጎራጉር ስለነበር ስሜቴ ሁሉ ወደ ሙዚቃ ሆነ፤ በ1949 ዓ.ም የንጉሰ ነገስቱ የክብር ዘብ ግቢ ውስጥ የጠቅል ሬዲዮ የሚባል ነበረ፤ ማክሰኞና ሀሙስ ዘፈንና አንዳንድ ፕሮግራሞች ይለቀቁ ነበር፡፡ የዚያን ጊዜ በሬዲዮ ቀርበው ይዘፍኑ የነበሩት እነ ካሳ ተሰማ፣ ተዘራ ሀ/ሚካኤል፣ መቶ አለቃ ኑር ወንዳፍራሽ (የብዙነሽ በቀለ የልጆቿ አባት የነበረው) ብዙነሽ በቀለ፣ ጥላሁን ገሠሠ፣ አየለ ማሞ፣ እሳቱ ተሰማ ወዘተ ነበሩ፡፡ የዚያን ጊዜ እነዚህ ድምፃውያን በሳምንት ሁለት ቀናት ሙዚቃቸውን እየመጡ ያሰሙ ስለነበር እኔ ቡና ቤት በር ላይ ሊስትሮ ሳጥኔ ላይ ቁጭ ብዬ ዘፈናቸውን አዳምጥ ነበር፡፡ የሚገርማችሁ ማታ የሰማኋቸውን ዘፈኖች ጠዋት ት/ቤት ከመግባታችን በፊት ለክፍል ጓደኞቼ እዘፍንላቸው ነበር፡፡
በወቅቱ ሞዴሌ አድርጌ የምቆጥረው ትልቁ ወንድሜን በአሁኑ ወቅት በዚህ ዓለም ላይ የሌለው ገሠሠ ነው፡፡ ሌላ ደግሞ በወቅቱ ከውጪ ሀገር የሚመጡ ፊልሞችን እመለከት ስለነበር በተለይ የኤልቪስ ፕሪስሊን ዘፈን አዳምጥ ነበር፡፡ ኤልቪስ ፕሪስሊ ሲዘፍን እግሩን እንዴት ያንቀጠቅጥ እንደነበር፡፡ በፊልም ላይ እመለከት ስለነበር እኔም ወደፊት መድረክ ላይ ስወጣ እግሬን አንቀጠቅጣለሁ እል ነበር፤ የኤልቪስ ፕሪስሊን ብቻ ሳይሆን የነ ሳምኩክን፣ የነጀምስ ብራውንን ዘፈኖች አዳምጥ ነበር፡፡

ወደ ሙዚቃው እየተሳብኩ ስመጣ የትምህርቱ ነገር እየቀረ መጣ፤ ከ8ኛ ክፍል በላይ ማለፍ አልቻልኩም፡፡ ጎረቤታችን ወ/ሮ የሺሀረግ ለእኛ የሰጡን አራት በአራት የምትሆን አንድ ክፍል ነበረችን፡፡ ጎረቤታችን አንድ ግብፃዊ ጠበቃ ነበር፤ ያ ጠበቃ ሹፌሮች ቡና ቤት ከሚባለው ቤት ባለቤት ጋር በመሆን ራስ ሀይሉ ቤት ውስጥ ናይት ክለብ ሊጀመር ነው የሚል ወሬ ስሰማ ለእናቴ ሄጄ ሥራ እንዲያስገባኝ ለምኚልኝ አልኳት፡፡ እሷም እሺ አለችና ሄዳ ስትጠይቀው ጥሩ ይምጣና ከአናፂዎች ጋር እመድበዋለሁ አለ፡፡ እሺ አልኩና ሄድኩ፡፡ ከአናፂዎች ጋር ሰርቻለሁ፡፡ ከቀለም ቀቢዎች ጋር ሠርቻለሁ፡፡ ቡና ቤቱ ለናይት ክለብ በሚሆን መልኩ ይሰራ ስለነበር ከነሱ ጋር ሰራሁ፤ በየግድግዳው ላይ ሰዎች ሲጨፍሩ ሁሉ የሚያሳይ ስዕል ተሰርቶ ተጠናቀቀ፡፡
ምሽት ክለብ
በ1954 ዓ.ም ገደማ የሚገርማችሁ ምሽት ክበቡ ተሠርቶ ከተጠናቀቀ በኋላ ሲከፈት እኔ ወደ ወጥ ቤት ነበር የገባሁት፡፡ ወጥ ቤት ስገባም የወጥ ቤት ረዳት ተደርጌ ነበር የተመደብኩት፡፡ ረዳት ሆኜ እየሰራሁ ማታ ማታ ምሽት ክለቡ ውስጥ እየመጡ የሚዘፍኑትን እነ እሳቱ ተሰማ፣ ጥላሁን ገሠሠ፣ ተፈራ ካሳ፣ ታምራት ሞላ፣ አባይ በለጠ (ነፍሳቸውን ይማረውና) እመለከት ነበር፡፡ እነሱ ዘፍነው ለእረፍት ሲቀመጡ እኔ ሳንድዊችና ሻይ አቅራቢ ነበርኩ፡፡ እነሱ ስር ስር ጉድ ጉድ እያልኩ ዘፈናቸውን በደንብ ነበር የማደምጠው፤ ታዲያ በአንድ አጋጣሚ እነ ጥላሁን ድሬዳዋ ለስራ ታዘው ሲሄዱ ሙዚቀኞች ብቻቸውን ቀሩ፡፡
ሙዚቀኞቹ የተፈራ ካሳን አልጠላሽም ከቶ ዘፈን መጫወት ሲጀምሩ ከወጥ ቤቴ ሹልክ ብዬ ወጥቼ ‹‹ይህቺን ዘፈን እሺ ልዝፈናት›› አልኳቸው፡፡ ቀጭን ስለነበርኩ አይተውኝ ‹‹ትችይዋለሽ እንዴ›› አሉኝ፡፡ እሞክራሁ አልኳቸውና መድረክ ላይ ወጥቼ ስጫወት እንደአጋጣሚ እዚያ ቤት ከምድር ጦርም ከጦር ሰራዊትም የኮንጎ ዘማቾች ነበሩና ሰምተው ተገረሙ፡፡ ስጨርስ ቢስ ብለው አስደገሙኝ፤ ስጨርስ እንደገና ለሶስተኛ ጊዜ አስደገሙኝ፤ ‹ይህም አለ ለካ› የተሰኘውን የተዘራ ኃ/ሚካኤልን ስጫወትም ይደገም ተባለ፤ ደገምኩ፤ ያንን ዘፍኜ ከመድረክ ልወርድ ስል የምሽት ክለቡ ባለቤት ፊት ለፊቴ ቆሞ ‹‹ያ አላህ፤ለመሆኑ መዝፈን ትችላለህ እንዴ?›› አለኝ ‹‹እሞክራለሁ›› ስለው ከነገ ጀምሮ ወደ ወጥ ቤት አትመለስም እነ ጥላሁን እስከሚመጡ ድረስ እዚሁ ትዘፍናለህ›› አለኝ፡፡ በማግስቱም መርካቶ ወሰደኝና ሙሉ ልብስ፣ ጫማና ሸሚዝ ከነልዋጩ ገዛልኝ፡፡ እነ ጥላሁን ከድሬዳዋ ሲመለሱ መድረኩ ላይ ቂብ ብዬ ጠበኳቸው፡፡
መድረክ ላይ ቆሜ ስዘፍን ሲያዩኝ ሠራዊት፣ የፖሊስ እና የቀዳማዊ ሀይለስላሴ የሙዚቃ ክፍሎች ባሉበት ዝግጅት ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ የቀዳማዊ ሀይለ ስላሴ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት እነ ተሾመ ምትኩን ይዞ ተሳትፏል፡፡ በዚህ የሙዚቃ መድረክ ላይ ነው እንግዲህ ተፈትነህ ካለፍክ ትቀጠራለህ የተባልኩት፡፡ በዕለቱ ትዝ ይለኛል የመድረክ አስተዋዋቂ በዚያን ወቅት የ10 አለቃ ገዛኸኝ ደስታ ነበር፡፡
የተናገረው ነገር አሁን ድረስ አይረሳኝም፡

