የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የትንሳኤ በዓልን በማስመልከት ከቅዳሜ ከሰዓት ጀምሮ እስከ እሁድ እኩለ ሌሊት የሚቆይ የ32 ሰዓታት የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ማወጃቸውን አስታውቀዋል፡፡
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ በበኩላቸው ዩክሬን ለስምምነቱ እውቅና እንደምትሰጥና እንደምታከብረው አረጋግጠዋል።
በዚኅም ሁለቱ ሀገራት የትንሳኤ በዓልን አስመልክቶ የ32 ሰዓታት የተኩስ አቁም ስምምነት ማድረጋቸው ታውቋል፡፡
ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ በትንሳዔ በዓል ወቅት የሕዝብ መገልገያ የሆኑ የኢነርጂ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች እንዲቆሙ ጥሪ ማስተላለፋቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ይህም በሁለቱ ወገኖች መካከል ለሰላም የሚበጁ ንግግሮች በሩቅም ቢሆን መኖራቸውን አመላካች ሆኗል።
እንደ ሲቢኤስ ዘገባ አሁን የታወጀው የተኩስ አቁም ስምምነት ለዘላቂ ሰላም እንደ መነሻ እርምጃ ሊወሰድ ይችላል የተባለ ሲሆን፣ የክሬምሊን መግለጫ የተኩስ አቁሙ ሩሲያ ለጋራ ሰላም ያላትን ፍላጎት ያንጸባረቀችበት እንደሆነ አስታውቋል፡፡
ይህ አጭር የሰላም ጊዜ በጦርነት ቀጠናው ውስጥ ላሉ ንጹሐን ዜጎች እረፍት ከመስጠቱም በላይ፣ ሁለቱ ሀገራት ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ንግግር እንዲመለሱ አዲስ ዕድል የሚፈጥር ነው ተብሏል፡፡

