ሩሲያ ትላንት አዳሩን የባላስቲክ ሚሳኤሎችን በመጠቀም ዩክሬን ላይ ጥቃት አድርሳለች፡፡
ሞስኮ በዩክሬን ላይ የምታደርሰውን የአየር ጥቃት በከፍተኛ ሁኔታ አባብሳ ገፍታበታለችም ተብሏል፡፡
አምስተኛ ዓመቱን ሊደፍን እየተንደረደረ ባለው ጦርነት ሞስኮ ከ1.4 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ተዋጊዎቿን እንዳጣችም ተነግሯል፡፡ ሩሲያ እስካሁን እያደረገች ባለው ጦርነት ከጠቅላላ ህዝቧ ወስጥ አንድ ፐርሰንት የሚሆነው ሞቶባታል አልያም ቆስሎባታል ተብሏል፡፡
በአንጻሩ ዩክሬን ደግሞ ከ525ሺ እስከ 625ሺ የሚገመት የሰው ሃይል ማጣቷ ተነግሯል፡፡
በርግጥ እንዲህ አይነቱ የጦርነት ኪሳራዎችን ሪፖርት ያደረጉት ለዩክሬን ውግንና እንዳላቸው የሚታወቁ የምዕራብ ሀገራት ምንጮች እንጂ ሁለቱም ሀገራት የሚያምኑበት ቁጥር አይደለም፡፡
ሞስኮ የትላንት ምሽቱን ጥቃት ያደረሰችው የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት በዩክሬን ጉብኝት ካደረጉ ከጥቂት ስዓታት በኋላ መሆኑ የጉዳዩን ክብደት ጨምሮታል፡፡
ሩሲያ ካለፈው ወር ወዲህ ለመቀልበስ በጣም አስቸጋሪና ፈጣን የሆኑ ባላስቲክ ሚሳኤሎችን በመጠቀም ዩክሬንን ቁምስቅል እያበላቻት ነው፡፡ ዩክሬን እነዚህን የባላስቲክ ሚሳኤልን ለመቀልበስ የሚያስችል የአየር መከላከያ ስርዓት ከመጪው ዓመት ጀምሮ ማምረት እንድትጀምር ፈቃድ መሰጠቱን ፕሬዝዳንት ትራምፕ መግለጻቸው ይታወቃል፡፡
አሁን ይህ ሁሉ የሚሳኤል ውርጅብኝ እየወረደባት የሚገኘው የአየር መከላከያ ስርዓት በእጇ ላይ ባለመኖሩ እንደሆነ ይነሳል፡፡
የምሽቱ የሩሲያ ባላስቲክ ሚሳኤል የዩክሬንን ዋና መዲና ኢላማ ያደረገ ነበር ተብሏል፡፡
ጥቃቱ ሁለት ሰዎችን ሲገድል፤ስድስት የሚሆኑትን ደግሞ ማቁሰሉ ተሰምቷል፡፡ የአስተዳደር ህንጻዎች እና መጋዘኖችም በባላስቲክ ሚሳኤል መመታታቸው ተገልጻል፡፡
ሞስኮ የትላንቱን ጥቃት ጨምሮ በሃምሌ ወር ብቻ ስድስት የአየር ጥቃቶችን ፈጽማለች ተብሏል፡፡
የዩክሬን አየር ሃይል ጥቃቱ ከመድረሱ አስቀድሞ የአደጋ ጊዜ ማስጠንቀቂያ ደውሎችን ሲያሰማ እንደነበርም ተነግሯል፡፡
የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በሌሎች አካባቢዎች ተጨማሪ ጉዳት መድረሱንና አለመድረሱን ለማወቅ ስራዎችን እየሰሩ እንደሆነ ኪቭ ፖስት ዘግቧል፡፡
የትላንት ምሽቱ ጥቃት የተፈጸመው የሩሲያ ሃይሎች ከሰሞኑ በዩክሬን ላይ እጅግ ከባድ የተባለውን ጥቃት ካደረሱ በኋላ ነው፡፡ በሰሞንኛው ጥቃት የሞስኮ ሃይሎች 13 ሰዎችን ሲገድሉ፤ተጨማሪ 50 የሚሆኑትን ደግሞ አቁስለዋል፡፡
ሩሲያ ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ የዩክሬን ከተሞችን በረጅም ርቀት ሚሳኤል ማጥቃቷን አጠናክራ ቀጥላለች፡፡ በዚህ የተነሳም በአራት ዓመቱ ጦርነት የንጹሃን ሞት በዚህ ወር እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ዩክሬን አስታውቃለች፡፡
የመንግስታቱ ደርጅት በሰኔ ወር ብቻ 293 ሲቪሊያን ሲገደሉ እንዲሁም 1ሺ 990 የሚደርሱት ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል ብሏል፡፡ ከተመዘገበው ጉዳት ውስጥ 45 በመቶ የሚሆነው የደረሰው በረጅም ርቀት ሚሳኤል እና በድሮን መሆኑ ይፋ ተደርጓል፡፡//

