ሴኔጋል በፊፋ ቅጣት ሊጣልባት ይችላል ተባለ

በኳታሩ የአለም ዋንጫ ትናንት ኢኳዶርን 2ለ1 በመርታት 16 ውስጥ መግባት የቻለችው የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት አገር ሴኔጋል ከጣፋጩ ድሏ ማግስት መጥፎ ዜና ሰምታለች። ሴኔጋል የፊፋን ህግ ጥሳለች በሚል ከአለም እግር ኳስ አስተዳዳሪው ቅጣት ሊጣልባት እንደሚችል ጠቁመዋል።
የቴራንጋ አንበሶቹ አሰልጣኝ አሊዩ ሲሴ ከኢኳዶሩ ወሳኝ ጨዋታ በፊት ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሲሰጥ ከቡድኑ ተጫዋቾች መካከል አንዱን ይዞ መገኘት ሲገባው ብቻውን መግለጫ መስጠቱን ተከትሎ ሴኔጋል በፊፋ ቅጣት እንደሚጣልባት ዘ ሰን ያወጣው ዘገባ ያመለክታል።
በፊፋ ህግ መሰረት የአንድ አገር ብሔራዊ ቡድን ጨዋታ ከማድረጉ አንድ ቀን ቀደም ብሎ በተዘጋጀ የሚዲያ ማእከል ውስጥ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠት አለበት። ጋዜጣዊ መግለጫው ሲሰጥም ዋና አሰልጣኙና የቡድኑ አንድ ተጫዋች የግዴታ መገኘት አለባቸው። ሲሴ ከኢኳዶሩ ጨዋታ ቀደም ብሎ የሰጠው መግለጫ ላይ አንድም የቡድኑ ተጫዋች አብሮት አለመገኘቱን ተከትሎ ፊፋ በጉዳዩ ዙሪያ ምርመራ መጀመሩ ታውቋል።
ሲሴ በመጀመሪያዎቹ ሁለት የምድብ ጨዋታዎች ወቅት ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጥ ክሬፒን ዲያታን እንዲሁም ካሊዶ ኩሊባሊን ይዞ የተገኘ ቢሆንም ከሶስተኛው ጨዋታ በፊት በሰጠው መግለጫ ተመሳሳይ ነገር ማድረግ አልቻለም። ይህም ፊፋ የማይታገሰው ጥፋት መሆኑን ዘገባው አክሏል።
የፊፋ ዲሲፕሊን ኮሚቴ በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው መግለጫ “የዲሲፕሊን ኮሚቴው የሴኔጋል እግር ኳስ ፌዴሬሽን የኳታሩን የአለም ዋንጫ የሚዲያና ማርኬቲንግ ደንብ አንቀጽ 44ን ተላልፎ በመገኘቱ ምርመራ ጀምሯል” ብሏል።
ተመሳሳይ የፊፋን ደንብ ከቀናት በፊት ተላልፋ የተገኘችው ጀርመን 8800 ዩሮ ቅጣት እንደተላለፈባት የሚታወስ ሲሆን ሴኔጋልም ተመሳሳይ የገንዘብ መጠን ልትቀጣ እንደምትችል የዘ ሰን ዘገባ አመልክቷል።
የጀርመኑ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሃንሲ ፍሊክ ከስፔን ጋር ካደረጉት ጨዋታ አንድ ቀን በፊት በሰጡት መግለጫ አንድም የቡድናቸው ተጫዋች አልተገኘም ነበር። አሰልጣኝ ፍሊክስ ቡድናቸው ያረፈው በሰሜን ዶሃ እንደመሆኑ ተጫዋቾቻቸው ከወሳኝ ጨዋታ በፊት የሶስት ሰአት ጉዞ አድርገው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዲገኙ ማስገደድ እንዳልፈለጉ ኋላ ላይ ተናግረዋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe