ኢትዮጵያ ያላትን የፀሐይ ኃይል ለመጠቀም በሁሉም ሕንፃዎችና ቤቶች ውስጥ የፀሐይ ኃይል መጠቀም በሒደት አስገዳጅ እንደሚሆን ተገለጿል።
ይህ የተገለጸው የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከኢንተርናሽናል ሶላር አሊያንስ ጋር የፀሐይ ኃይል በጋራ ለማልማት የሚያስችል ስምምነት ነሐሴ 7 ቀን 2017 ዓ.ም. ሲፈራረሙ ነው፡፡
‹‹ኢትዮጵያ ከፍተኛ የፀሐይ ኃይል አላት›› ያሉት የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ደኤታ ሡልጣን ወሊ (ኢንጂነር)፣ ይህን አቅም ጥቅም ላይ ለማዋል ከዚህ ቀደም አለመሠራቱን፣ ለዚህም ሲባል በሒደት በእያንዳንዱ ቤትና ሕንፃ ጣሪያ የፀሐይ ኃይል ቴክኖሎጂ እንደሚገጠም አስታውቀዋል፡፡
ሪፖርተር እንደዘገበው ከዚህ ቀደም አዲስ አበባ ውስጥ በእያንዳንዱ ቤት ጣሪያ ላይ የፀሐይ ኃይል መሰብሰቢያ (Solar Panel) ቢኖር ምን ያህል ኃይል ማግኘት እንደሚቻል የሚያሳይ ጥናት ተደርጎ እንደነበር አስታውሰው፣ ማኅበረሰቡ የፀሐይ ኃይል እንዲጠቀም የግንዛቤ ሥራዎች እንደሚቀድሙና በሒደት ግን በሌሎች አገሮች እንዳለው አሠራር አስገዳጅ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡
ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ማድረግ ቀላል አይሆንም ያሉት ሚኒስትር ደኤታው፣ ነገር ግን ያለውን አቅም ለመጠቀምና የኃይል ተደራሽነትን ለማስፋት ተግባራዊ ማድረጉ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ‹‹የተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና የመንግሥት ተቋማት፣ እንዲሁም ሕንፃዎች በቀጣይ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማድረግ ዕቅድ ተይዟል፤›› ብለዋል፡፡

