ረቡዕ ነሐሴ 30 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት ችግር እየተባባሰ መምጣቱን እና ተጠቃሚዎች ተሽከርካሪ(ታክሲ) በመጠበቅ የሚያሳልፉት ጊዜ እንዳስመረራቸው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡
በተለያዩ አካባቢዎች ሰራተኞች ወደ መስሪያ ቤታቸው ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው በሰዓቱ ለመድረስ የታክሲ አገልግሎት ማግኘት እንዳልቻሉም ደጋግመው ሲገልጹ ይደመጣል፡፡
በተለያዩ ችግሮች አገልግሎቱን በአግባቡ መጠቀም እንዳልቻሉ የሚናገሩት እነዚህ ቅሬታ አቅራቢዎች ሰልፍ ላይ ብቻ ከአንድ ሰዓት በላይ እንቆማለን እንደዛም ሆኖ በየሰበቡ መንገድ ይዘጋል ጊዜአችንን ሁሉ በመንገድ እንጨርሰዋለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡
አክለውም ቅዳሜ እና እሁድ ደግሞ የአሽከርካሪዎች መጫወቻ ነው የምንሆነው ያለታሪፍ ይጭናሉ ፣ከባለታክሲ እና ተራ አስከባሪዎች ጋር እየተመካከሩ መንገድ ዝግ ነው ሲፈልጉም መኪና የለም እያሉ በኮንትራት ታክሲ እንድንሄድ ያስገድዱናል ብለዋል፡፡
በከተማ ውስጥ መንቀሳቀስ ከባድ ሆኗል ያሉት ነዋሪዎቹ በመንገድ መዘጋጋት፣ የመንገድ ግንባታ እና መሰል ችግሮች በሰዓቱ ካሰቡበት መድረስ እንደተሳናቸው አስታውቀዋል፡፡
በፊት በለሊት መነሳት ብቻ ነበር የሚጠበቅብን በጊዜ ለመድረስ አሁን ግን ያን ያህል ልዩነት እንኳን የለውም ወይ በተሸከርካሪ እጥረት አሊያም በመንገድ መዘጋጋት ማርፈድ የተለመደ ሆኗል በማለት ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም ከስራ አስራአንድ ሰዓት የሚወጣ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት በፊት ወደ ቤቱ መግባት ብርቅ ነው የሚሆንበት እንዲሁም ይህን ክረምት ተከትሎ በሚጥለው ዝናብ ከተማው ሁሉ ይጥለቀለቃል በዚህ ጊዜ መንገድ ላይ ያለ ሰው በተዓምር ነው ካሰበበት የሚደርሰው ሲሉ በምሬት ገልጸዋል፡፡
በእግር መሄድን አማራጭ ለማድረግ የምንኖርበት ቦታ ይወስነዋል ያሉት ነዋሪዎች ማንም ሰው ከስራው ደክሞት ወጥቶ በእግሩ ለመሄድ ሞራል አይኖረውም ብለዋል፡፡
በተለይም በከተማዋ ጥግ እንደ ቦሌአራብሳ እና አያት አካባቢ የሚኖሩ የታክሲ ተጠቃሚዎች በዋነኛነት የችግሩ ገፈት ቀማሽ ሆነው ይታያሉ፡፡
አዲስ ማለዳ ስለተደጋጋሚው የመዲናዋ የትራንስፖርት ችግር ዘላቂ መፍትሄ ምን ይሆን ስትል የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ለማናገር ያደረገችው ተደጋጋሚ ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

