የትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመውጫ ፈተናን አስመልክቶ ባወጣው መመሪያ መሠረት 90 የሚሆኑ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከሚያስፈትኗቸው ተማሪዎች 75 በመቶ ማለፍ ባለመቻላቸው መዘጋታቸው ተሰምቷል፡፡
መንግስት ከዚህ በፊት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመውጫ ፈተና ከሚያስፈትኗቸው ተመራቂዎች ውስጥ 75 በመቶና ከዚያ በላይ በማያሳልፉት ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ከገለጸ በኋላ ነው አሁን 90 የትምህርት ተቋማት መዘጋታቸው የተሰማው፡፡
አብዛኛዎቹ እርምጃውን የወሰዱት ራሳቸው እንደሆነም ታውቋል፡፡ መመሪያውን ካዩ በኋላ በመዝጋት እየወጡ እንደሆነ ተነግሯል፡፡ ከመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች እስካሁን የተዘጋ ባይኖርም ዝቅተኛ ውጤት ያስመዘገቡ እንዳሉ ገን ተገልጻል፡፡ ተዘግተዋል የተባሉት የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በመላው ሀገሪቱ ሲያስተምሩ የነበሩ ናቸው ከመባል ውጪ በዝርዝር ስማቸው አልተገለጸም፡፡
ተቋማቱ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የወጡ መመሪያዎችን በማየት ብቻ በራሳቸው ፈቃድ ከማስተማር ሂደቱ የወጡ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከዚህ በፊት ከተሰሩ ጥናታዊ ጽሁፎች እየተቀዱ የሚቀርቡበት ሁኔታ ስለተበራከተ ዩኒቨርሲቲዎች ፕላጃሪዝምን ለመከታታል በቴክኖሎጂ ታግዘው እንደሚሰሩ ተመላክቷል፡፡

