በብልሽት ምክንያት ለቆሙ ቀላል ባቡሮች 60 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ተገለጸ!
የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ በብልሽት ምክንያት የትራንስፖርት አገልግሎት የማይሰጡ ቀላል ባቡሮችን ለማስጠገን 60 ሚሊዮን ዶላር (አንድ ቢሊዮን ብር) በጀት መያዙን አስታወቀ።
በመለዋወጫና በሌሎች ችግሮች ምክንያት ከ41 ቀላል ባቡሮች ውስጥ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡት 18 ብቻ ሲሆኑ፣ በዚህም ምክንያት የጥገና በጀት መያዝ ማስፈለጉን የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ምትኩ አስማረ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡የአዲስ አበባ ከተማ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት የተለያዩ መለዋወጫዎችና ሌሎች በርካታ ችግሮች እንዳሉበት የገለጹት ምትኩ፤ በዚህም ሳቢያ አገልግሎት እየተሰጠ ያለው በ42 በመቶ አቅም ብቻ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በዚህ መሠረት 23 ቀላል ባቡሮች የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት የማይችሉ ሲሆኑ፣ ብልሽት ያልገጠማቸው 18 ባቡሮች ግን በቀን ከ56 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ተገልጋዮች አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን የቢሮ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡በአጠቃላይ የተለያዩ ችግሮች በገጠሟቸው በብልሽት ለቆሙ ቀላል ባቡሮች 60 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግም አክለው ተናግረዋል፡፡

