በአዲስ አበባ የታክሲ ተራ አስከባሪዎች ማህበራት ከስራ ውጪ ሆኑ

በአዲስ አበባ ላለፉት 14 ዓመታት ያህል በስራ ላይ የነበሩ የታክሲ ተራ አስከባሪዎች ማህበራት ከስራ ውጪ ከሆኑ ዛሬ ሦስተኛ ቀን እንደያዙ ተገለጸ፡፡

በአዲስ አበባ በሁሉም አከባቢዎች የታክሲ ተራ ማስከበር ስራ ላይ የነበሩ እስከ 9ሺ የሚደርሱ ተራ አስከባሪዎች ከረቡዕ እለት ጀምሮ ከስራ ውጪ መሆናቸው ተሰምቷል፡፡

ማህበራቱ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በየወረዳቸው በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ ተደራጅተው በዚህ ስራ ላይ ቆይተዋል፡፡

ማህበራቱ ስራ ያቆሙት በከተማዋ በሁሉም አካባቢዎች ያሉ የታክሲ ተራ አስከባሪዎች በአዲስ ሊተኩ እንደሆነ ከተነገረ ከአንድ ወር በኋላ ነው፡፡

በዚህ ወቅት በሁሉም የተከተማዋ አካባቢዎች የታክሲ መነሻ እና ማቆሚያ ተርሚናሎች ላይ ተራ አስከባሪዎች አለመኖራቸውን ቁም ነገር ሚዲያ ባደረገው ምልከታ ለማወቅ ችሏል፡፡

ከ150 በላይ በሆኑ በዚህ ዘርፍ ውስጥ በተደራጁ ማህበራት ውስጥ እስከ 9ሺ ሰዎች በዚህ ስራ ሲተዳደሩ መቆየታቸውን በተራ ማስከበር ስራ ተሰማርተው የቆዩ ግለሰቦች ነግረውናል፡፡

ከዚህ ቁጥር ውስጥ አብዛኛው የማህበራቱ አባላት ደግሞ በስራቸው የሚያስተዳድሯቸው የቤተሰብ አባላት ያላቸው መሆናቸውንና በግምታዊ ቁጥርም ከ40ሺ ሰዎች በላይ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ በስራው እንደሚተዳደሩ በዚሁ ስራ ላይ የቆዩ ሰዎች ገልጸውልናል፡፡

ከአንድ ወር በፊት ሁሉም  የተራ አስከባሪዎች ማህበራት በአዲስ መልክ ይተካሉ ሲባል እንደ ምክንያት ቀርቦ የነበረው ማህበራቱ በየሁለት ዓመቱ ይፐወዛሉ የሚል ነበር፡፡

የአዲስ አበባ ስራና ክህሎት ቢሮ ማህበራቱ በየሁለት ዓመቱ በአዲስ እንደሚተኩ ገልጾ አሁን የሚደረገውም ይህ ነው ብሎ ነበር፡፡

ቢሮው የታክሲ ተራ አስከባሪዎች ጥሪት እንዲያፈሩ በቢሮው ስር የሚደራጁት ለሁለት ዓመት ብቻ ነው ማለቱ ይታወሳል፡፡ ስለዚህ አሁን በአዲስ የሚተኩት የተሰጣቸውን ጊዜ በመጨረሳቸው ሌሎች ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ሲባል በአዲስ የመተካቱ ስራ እንደሚሰራ ማብራሪያ መስጠቱም ይታወሳል፡፡

አሁን ከዚህ ስራ ውጭ የሚደረጉት ተራ አስከባሪዎች በከተማው ስራ ክህሎት ቢሮ በመካከለኛ ኢንተርፕራይዝ በስድስት ዘርፎች መደራጀት እንደሚችሉም መግለጹ ይታወሳል፡፡

እስካሁን የነበሩት ተራ አስከባሪዎች ጊዚያቸው አብቅቷል፤ንብረትም አፍርተዋል አሁን ለሌላ ለከተማው ስራ አጥ ወጣት ቦታውን ይለቃሉ እነርሱም ወደ ሌላ ዘርፍ እንዲገቡ ይደረጋሉ ነው የተባለው፡፡

ነገር ግን በዚህ ስራ ላይ የቆዩት ወጣቶች እንደ ሚባለው ያፈራነው ጥሪትም የለም ውሳኔውም ድንገቴ ነው የሆነብን በስጋት ውስጥ ወድቀናል ብለዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በየሁለት ዓመቱ እንደ አዲስ እንደሚደራጅ ታውቁ ነበር ወይ በሚል ላነሳንላቸው ጥያቄም ይህንን አናውቅም ብለውናል፡፡//

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe