በአዲስ አበባ 2 ሺሕ 500 ሕንፃዎች ምንም አይነት የደህንነት መስፈርት የማያሟሉ ናቸው ተባለ

‎ባለፋት ሦስት ወራት ውስጥ ብቻ ከ3 ሺሕ 500 በላይ ሕንጻዎች ወይም ግንባታዎች ላይ በተደረገ ልየታ 2 ሺሕ 500 የሚሆኑት የደህንነት መስፈርት የማያሟሉ ሆነው መገኘታቸውን የአዲስ አበባ ግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ለአሐዱ አስታውቋል።

በ2017 በጀት ዓመት የተጀመሩ ከ11 ሺሕ 500 በላይ እና ነባር ግንባታዎች ደግሞ ከ12 ሺሕ 200 በላይ በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት ወደ 24 ሺሕ ሕንጻዎች በአዲስ አበባ እየተገነቡ እንደሚገኝ የባልጣኑ ም/ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር አበበ እሸቱ ተናግረዋል።

ከእነዚህ ውስጥም ለደህንነት አስጊ ተብለው በተመረጡ ከ3 ሺሕ 500 በላይ ሕንጻዎች ላይ ከደህንነት አኳያ ያሉበትን ደረጃ ለማወቅ ልየታ መሰራቱን ገልጸው፤ አብዛኞቹ ግንባታዎች ላይ ክፍተት መታየቱን አስታውቀዋል።

በዚህም መሠረት ልየታ ከተደረገባቸው ውስጥ 2 ሺሕ 500 የሚሆኑት ምንም አይነት የደህንነት ሥራ ያልሰሩና ለሠራተኞቻቸውም ጥንቃቄ ያላደረጉ እንዲሁም፤ ተረፈ ምርት በአግባቡ ማስቀመጥ ያልቻሉና ለደህንነት አስጊ ሆነው መገኘታቸውን ገልጸዋል።

ይህንንም እንዲያስተካክሉ ለማድረግ በተለያዩ አማራጮች ግንዛቤ ሲፈጠር መቆየቱንና እንዲያስተካክሉ በተሰጣቸው የ7 ቀን ገደብ ውስጥ ግን መተግበር ካልቻሉ በአዋጁ መሰረት ቅጣት ሲቀጣ መቆየቱን ተናግረዋል።

በመሆኑም 2 ሺሕ 500 ሕንጻዎች ላይ ግንዛቤን በመፍጠርና ቅጣትንም በመጣል ቢያንስ ዝቅተኛ ወይም የመጀመሪያ ደረጃና አስፈላጊ የሆነውን የደህንነት መስፈርት እንዲያሟሉ መደረጉን ም/ ዋና ዳይሬክተሩ ለአሐዱ ተናግረዋል።

የግንባታ ሠራተኛው ከሕንጻው ላይ እንዳይወድቅና ተረፈ ምርት ቢወድቅ ከታች ያሉ ሠራተኞች ላይ አደጋ እንዳያደርስ የሚያስችል የሕንጻውን የውጪ አካል በስታንዳርዱ መሠረት ሙሉ ለሙሉ መሸፈን አንዱ የደህንነት ሥራ ስለመሆኑ አንስተዋል።

በተጨማሪም ሠራተኞች ከከፍታ ላይ ቢወድቁ እንኳን ከታች ተቀብሏቸው አደጋ እንዳይደርስባቸው የሚያስችል መሳሪያ እንዲተገብሩ መደረጉን ገልጸዋል።

ከዚህ ሌላም ሠራተኞች ራሳቸው ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸውን የደህንነት መጠበቂያ አልባሳት እንዲለብሱ ማድረግ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

በመሆኑም ‘አሁንም ቢሆን በቂ ሥራ ነው ‘ብሎ መውሰድ ስለማይቻል፤ ሌሎች ሕንጻዎችንም የማየትና የማስተካከል ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe