በኢትዮጵያ ከ4 ሚልየን በላይ ህፃናት ከትምህርት ገበታቸዉ ተሰናክለዋል” በኢትዮጵያ የአሜሪካው አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ

 በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠረ ግጭት ምክንያት፤ ከ 4 ሚልየን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸዉ መሰናከላቸዉንና 4 ሺሕ 178 የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸዉን ገለጹ፡፡
አምባሳደሩ ይህን ያሉት ትናንት ሰኞ መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም አመሻሹን በሸራተን አዲስ ሆቴል በተዘጋጀው የዩኤስ ኤድ መዝጊያ ፕሮግራም ላይ ሲሆን፤ በሥነ-ስርዓቱ ላይ በኢትዮጵያ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች የወንጀል ድርጊቶች እየጨመሩ መምጣታቸውን ተገልጿል፡፡
የመርሃ ግብሩ ቁልፍ ተናጋሪ የነበሩት አምባሳደር ማሲንጋ፤ በትግራይ ክልል በጦርነቱ ለችግር የተጋለጡ ሰዎች የድህረ ጦርነት የዓዕምሮ ማገገም እንዲያገኙ ጥረት መደረጉን ገልጸው፤ ግጭቱ በሕፃናት ሕይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማስከተሉን ተናግረዋል፡፡
አክለውም፤ በቅርቡ በአማራ ክልል የደረሰውን የከፋ ሁኔታ እና በክልሉ 4 ሺሕ 178 ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸው ሪፖርት መደረጉን ያነሱ ሲሆን፤ ሰላም ሕፃናትን ወደ ትምህርት ቤት እና ወደ ጤናቸው እንደሚመለሱ ቁልፍ ጉዳይ ስለመሆኑ አፅንዖት ሰጥተዋል።
በኢትዮጵያ ከአስር ዓመት በፊት ለተከታታይ ዓመታት ይመዘገብ የነበረው የኢኮኖሚ እድገት በባለፈው የፈረንጆቹ 2023 ዓመት መቀነሱን አስረድተዋል። ለዚህ የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ በሀገሪቱ ያለው ግጭት “ዋነኛ ሚና” መጫወቱንም አስገንዝበዋል።
አምባሳደር ማሲንጋ በንግግራቸው የሰላም እና የውይይትን አስፈላጊነትን በተደጋጋሚ አንስተዋል። ግጭቶችን ለማስቆም፣ የጋራ መግባባት እና መፍትሔን ለማበጀት “ብቸኛው መንገድ” ውይይት ማድረግ መሆኑንም አበክረው ገልጸዋል።
አምባሳደሩ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ባደረጉት የፖሊሲ ንግግር፤ ተመሳሳይ ሀሳብ አንጸባርቀው እንደነበር ይታወሳል። አምባሳደሩ በወቅቱ በኢትዮጵያ ያሉ ሁሉም የታጠቁ ኃይሎች “ጊዜያዊ ሀገር አቀፍ የተኩስ ማቆም” እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።
በዚህ የዩኤስ ኤድ የመዝጊያ ፕሮግራም ላይ በኢትዮጵያ የአሜሪካን አምባሳደርን ጨምሮ የዩስ ኤድ በኢትዮጵያ ሰራተኞች፣ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ የ”ምን ሆኛለሁ” መፅሐፍ ደራሲ እና የስነ ልቦና አማካሪ ትዕግስት ዋልተንጉስ እንዲሁም ሌሎች የስነልቦና አማካሪዎች ተሳትፈዋል። የሥነ ልቦና አማካሪዎቹም ከግጭት ጋር ተያይዞ ስለሚፈጠሩ የሥነ-ልቦና እክሎች የፓናል ዉይይት አድርገዋል።
በዳግም ተገኝ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe