👉 የወንድ አጫሾች ቁጥር ከ 7 በመቶ ወደ 7 ነጥብ 7 በመቶ ከፍ ብሏል
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 4 ነጥብ 6 በመቶ የሚሆኑ ዜጎች ትምባሆ ተጠቃሚ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለአሐዱ ገልጿል።
ኢኒስቲትዩቱ የኢትዮጵያን የትምቧሆ ቁጥጥር ፖሊሲዎች ለማጠናከር በተደረገው ሁለተኛ ዙር የአዋቂዎች የትምባሆ አጠቃቀም ዳሰሳ ጥናት መሠረት፤ በሁለቱም ፆታዎች መሻሻሎች እንዳሉ አስታውቋል።
ከስምንት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ በተደረገው የመጀመሪያው ዙር ጥናት መሠረት 5 በመቶ ወይም 3 ነጥብ 4 ሚሊዮን አዋቂ ኢትዮጵያውያን የትምባሆ ተጠቃሚዎች እንደነበሩም ገልጿል፡፡
በወቅቱ ትምባሆ ከመጠቀም ጋር ተያይዞ በሚመጡ የጤና ችግሮች ሳቢያ በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ17 ሺሕ በላይ ሰዎች ለሞት መዳረጋቸውን አመላክቷል።
ከመጀመሪያው ዙር በኋላ ኢትዮጵያ የትምባሆ አጠቃቀምን ለመከላከል ‘መቶ በመቶ ከትምባሆ ጭስ ነጻ’ ፖሊሲን ያካተተ የፖሊሲ እርምጃዎችን እየተገበረች መሆኑን፤ በኢንስቲትዩቱ የምግብ ሳይንስ ፣ የአካባቢ ጤና እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ምርመር ዲቪዥን ተመራማሪ ኪሩቤል ተስፋዬ ለአሐዱ ገልጸዋል።
የትምቧሆ ቁጥጥር ፖሊሲዎች ለማጠናከር እ.አ.አ በ2024 በኢትዮጵያ ሁለተኛው ዙር የአዋቂዎች የትምባሆ አጠቃቀም ዳሰሳ ጥናት ተጠንቶ ውጤቱ ይፋ መደረጉንም ተናግረዋል።
የዳሰሳ ጥናቱ ውጤት እንደሚያሳየው በአሁኑ ወቅት 4 ነጥብ 6 በመቶ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን አዋቂዎች ትምባሆ ይጠቀማሉ።
በጾታ ረገድም ሲታይ 8 ነጥብ 8 በመቶ ወንዶች ሲሆኑ፤ 0 ነጥብ 5 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ሴቶች ናቸው ብለዋል።
በሌላ በኩል በሀገር አቀፍ ደረጃ 4 ነጥብ 3 በመቶ የነበረው የሚጨስ ትምባሆ መጠን አሁን ላይ ወደ 4 በመቶ መውረዱን የገለጹት ተመራማሪው፤ ነገር ግን የወንድ ትምባሆ አጫሾች ቁጥር ከ 7 በመቶ ወደ 7 ነጥብ 7 በመቶ ከፍ ማለቱን ተናግረዋል፡፡
በሴቶች በኩልም የሚጨስ የትምባሆ መጠን ከ1 ነጥብ 5 በመቶ፤ ወደ 0 ነጥብ 4 በመቶ ዝቅ ማለቱን አስረድተዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ የከፋ የጤና ጉዳት እንዲሁም ለሞት ከሚዳርጉ ግንባር ቀደም መንስኤዎች አንዱ ትምባሆን የመጠቀም ልምድ መሆኑ ይገለጻል፡፡
በአሁኑ ወቅትም በዓለም አቀፍ ደረጃ 1 ነጥብ 14 ቢሊዮን አጫሾች መኖራቸውን ጥናቶች የሚያመለክቱ ሲሆን፤ በየዓመቱም ከ8 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ሞት ምክንያት መሆኑ ተነግሯል።
ከእነዚህም መካከል 7 ሚሊየን የሚሆኑት በቀጥታ በትንባሆ ሳቢያ በሚመጡና ተዛማጅ የጤና እክሎች ምክንያት ሕይወታቸው የሚያልፍ ሲሆን፤ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች ደግሞ አጠገባቸው ሆነው ለጭሱ ተጋላጭ በመሆናቸው ሳቢያ በሚመጡ በሽታዎች ሕይወታቸውን እንደሚያጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

