ካናዳን ጨምሮ ወደ ተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት ዜጎችን በስራ እንዲልኩ ፈቃድ የሰጠሁት አንድም ተቋማት የለም ሲል የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
የቪዛ የማመከር አገልግሎት እንሰጣለን የሚሉ አንዳንድ ድርጅቶች በስራ ወደ አውሮፓ ለመላክ የሚያስችለንን ፈቃድ ከሚኒስቴሩ ማግኘታቸውን የሚገልጽ ማስታወቂያ እያስነገሩ እንደሆነም ገልጻል፡፡
ነገር ግን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ወደ ካናዳ እና አውሮፓ በስራ ዜጎችን ለመላክ እውቅና የሰጠው አንድም ድርጅት አለመኖሩን ነው የገለጸው፡፡
እንደዚህ አይነት ማስታወቂያዎችን በሚል በሶሻል ሚዲያ የሚያስነግሩ አካላት መኖራቸው በመረጋገጡ በህግ ተጠያቂ ለማድረግ እየሰራሁ ነው ብሏል፡፡
ሚኒስቴሩ ህብረተሰቡን በማጭበርበር ላላስፈላጊ ወጪ እያጋለጡ ያሉ አካላትን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ መስራቱን እንደሚቀጥል ገልጾ፤ህብረተሰቡም በዚህ እንዳይታለል ብሏል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመቶ ሺዎች እና በሚሊዮኖች በጉዞ ወኪል ተጨበረበርን የሚሉ ዜናዎች በተደጋጋሚ እየተሰማ ይገኛል፡፡
በውጭ ሀገር የስራ ስምሪት የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ወደ አውሮፓ እና አሜሪካ ዜጎችን እንዲልክ በሚል እውቅና የሰጠው የትኛውም ተቋም እንደሌለ ነው ያስታወቀው፡፡
የስራና ክህሎት ሚኒስቴር በዚህ ስዓት ወደ መካከለኛው ምስራቅ ዜጎችን ለስራ ስምሪት እንደሚልክ በተደጋጋሚ ሲገልጽ ይደመጣል፡፡

