ባለፈው ዓመት ሀምሌ ወር ላይ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ማሻሻያ ከተደረገ በኋላ የዶላር ምንዛሬ 128 በመቶ ጭምሪ አሳይቷል፡፡
አዲሱ የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ይፋ ከመደረጉ በፊት አንድ የአሜሪካን ዶላር የመግዣ ዋጋ በንግድ ባንኮች 57 ብር ገደማ ነበር፡፡ ዛሬ ባለው የእለቱ ምንዛሬ ዋጋ ደግሞ አንድ የአሜሪካን ዶላር 131 ብር እየተገዛ ይገኛል፡፡
የኢትዮጽያ ንግድ ባንክ ለበርካታ ወራት አንዱ የአሜሪካን ዶላር 124 ብር እየገዛና ሁለት ብር ጨምሮ ሲሸጥ ከርሞ ነበር ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ግን አራት ብር ጭማሪ አድርጎ 128 ሲገዛ ቆይቷል፡፡ ባንኪ በአንድ ሳምንት የ7 ብር ጭማሪ በማድረግ አንዱን ዶላር 131 ብር ገዝቶ በ133 ብር እየሸጠ ነው፡፡
ብሔራዊ ባንክ ለባንኮች የውጭ ምንዛሬ በጨረታ እየሸጠ ሲሆን ባለፈው ሳምንት በነበረው ስድስተኛው ዙር ጨረታ 50 ሚሊዮን ዶላር ቀርቦ 14 ባንኮች በአማካኝ 133 ብር ከ17 ሳንቲም ገዝተዋል፡፡ የውጭ ምንዛሬ ዋጋ በገበያው እንዲመራ መደረጉ የብላክ ማርኬቱን ያዳክመዋል ተብለው የነበረ ቢሆንም በዚህ ወቅት አንዱ የአሜሪካን ዶላር እስከ 154 ብር ድረስ ይመነዘራል፡፡//

