‹በእስራኤል መንግስት በኩል ይሄ ኃላፊነት ሲሰጠኝ  በደስታ የተቀበልኩት ታሪካዊ እድል ነው ብዬ ነው› በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ክቡር አምባሳደር አብርሃም ንጉሴ

በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር   ክቡር አምባሳደር አብርሃም ንጉሴ

ባለፈው ዓመት መጨረሻ በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ሆነው የተሾሙት ክቡር አምባሳደር አብርሃም ንጉሴ ጎንደር ጎርጎራ አካባቢ ባለች ትንሽ መንደር ነው ተወልደው ያደጉት፡፡ አምባሳደር አብርሃም ወደ እስራኤል ቤተሰባቸውን ይዘው ከሄዱ በኋላ ራሳቸውን ከእስራኤል ማህበረሰብ ጋር ለማዋሃድና በትምህርት ራሳቸውን ለማብቃት አመዛኙን ጊዜያቸውን ያሳለፉት በትምህርት ነው፡፡

ከሂብሩ  ዩኒቨርሲቲ  የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን  በማህበራዊ ጥናት ዘርፍ ከጨረሱ በኋላ  ሌላ የህግ ዲግሪ እንዲሁም  በምጣኔ ሃብትና የስራ ፈጠራ ሌላ ሁለተኛ የማስተርስ ዲግሪ ተቀብለዋል፡፡ ሶስተኛ ዲግሪያቸውንም ከእንግሊዝ ሀገር በትምህርት አስተዳደር አጠናቀዋል፡፡ በእስራኤል ፖለቲካ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ያላቸው አምባሳደር አብርሃም በምርጫ ተወዳድረው የእስራኤል ፓርላማ አባል ሆነው  ለአራት ዓመታት አገልግለዋል፡፡

‹ኢትዮጵያ ውስጥ ተወልጄ እውቀት ቀስሜ በማደጌ ለኢትዮጵያ ያለኝ ህልም ከፍ ያለ ነው› የሚሉት አምባሳደር አብርሃም ‹የኔ ህልም የእስራኤልን ያንን በረሃ  ምድረ ገነት  አረንጓዴ ያደርገውን ቴክኖሎጂ ወደዚህ በማምጣት ከኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብትዋ ጋር በማገናኘት ኢትዮጵያ  ከአፍሪካ  በምጣኔ ሀብት  መሪ ሀገር እንድትሆን መስራት ምኞቴ ነው › ይላሉ፡፡ ከአምደባሳደር አብርሃም ጋር በኢትዮጵያ የእስራኤል ኤምባሲ  በግል የህይወት ተሞክሯቸው፤ በሁለቱ ሀገራት ግንኙነትና በሚያዝኗኗቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከመፅሔቱ ዋና አዘጋጅ ታምራት ኃይሉ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

ቁም ነገር፦ በቅደሚያ ክቡር አምባሳደር አብርሃም ንጉሴ ለጊዜዎት በጣም አመሰግናለሁ፤  አምባሳደር የት ተወለዱ የት አካባቢ ነው ያደጉት በሚለው ጥያቄ እንጀምር?

አምባሳደር አብርሃም፦ እኔም ወደ ኤምባሲያችን በደህና መጥታችሁ ለቃለ መጠየቅ ስለጋበዛችሁኝ በጣም አመሰግናለሁ፤ የተወለድኩት ጎንደር ዙሪያ  ጎርጎራ አካባቢ ከጎርጎራ  ትንሽ ራቅ ብላ  የምትገኝ   ፈንታ የተባለች መንደር ነው፡፡  እዚያ ተወልጄ  እንደማንኛውም  የኢትዮጵያ ገጠር ልጆች ወላጆቼን በእረኝነት ሳገለግል ኖሬያለው፡፡

ቁም ነገር፦ትምህርትስ?

አምባሳደር አብርሃም፦ በወቅቱ  በአካባቢያችን ትምህርት ቤት ስለሌለ እድሜዬ ረጅም መንገድ ተጉዞ መማር የምችልበት ደረጃ ላይ ስደርስ ጀንዳ የተባለ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማርኩ፤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ያጠናቀቅኩት በጎንደር ከተማ ውስጥ ፋሲለደስ  ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው፡፡  ትምህርቴን ካጠናቀቅኩ በኋላ በአንድ የህፃናት ማሳደጊያ በዚያው በጎንደር ከተማ ውስጥ የሚገኝ  ህፃናት ማሳደጊያ  ስሰራ  ቆየሁ፡፡  ትዳር እስክመሰርት ድረስ በዚህ ስራ ላይ  ነን የቆየሁት፤

ቁም ነገር፦ ወደ እስራኤል የሄዱት እንዴት ነው?

አምባሳደር አብርሃም ፦ ወደ እስራኤል የሄድኩት የመጀመሪያ ልጃችን እንደተወለደ  ነው፤ እዚያ እንደገባሁ በሂብሩ  ዩኒቨርሲቲ ትምህርት  ጀመርኩ፤ በዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ  የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪዬ በማህበራዊ ጉዳይ ዘርፍ ተምሬር ጨረስኩ፤   ከዚያም በእየሩሳሌም ማዘጋጃ ቤት በማህበራዊ ጉዳይ ዘርፍ ተቀጥሬ ስሰራ ቆየሁ፤ ትምህርቴንም እየሰራሁ በመቀጠል ምጣኔ ሃብትን በተመለከተ የስራ ፈጠራ ላይ ሌላ ሁለተኛ የማስተርስ ዲግሪ አገኘሁ፤   ከዚያም ህግ የማወቅ ዝንባሌ ስለነበረኝ  ህግ ተምሬ የመጀመሪያ ዲግሪ ተቀበልኩ፡፡ ሶስተኛ ዲግሪዬን በእንግሊዝ አገር ነው የተማርኩት፡፡

ቁም ነገር፦ ምን አጠኑ?

በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ክቡር አምባሳደር አብርሃም ንጉሴ

አምባሳደር አብርሃም፦የዶክትሬት ዲግሪዬን የሰራሁት ሳሴክስ ዩኒቨርሲቲ በትምህርት አስተዳደር ነው፡፡ እነዚህን ሁሉ ትምህርቶች የተማርኩት ስራዬን እየሰራሁ  እንደገናም ማህበራዊ አክቲቪስት ሆኜ ነው፡፡  በተለይ እኛ ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል ሀገር የሚሄደው ማህበረሰብ ትምህርትን የመሰለ መሰረታዊ አጀንዳዎች የማግኘት ችግር ስለነበር እንደዚህ ያሉ አጀንዳዎችን ከሌሎቹ ጓደኞቼ ጋር በመሆን ግብረ ሰናይ ድርጅት በሀገሪቱ ህግና ደንብ መሰረት በማቋቋም አውንታዊ ተፅእኖ በመንግስት ላይ በማሳደር ለውጦችን አምጥተናል፡፡

ቁም ነገር፦ ለምሳሌ?

አምባሳደር አብርሃም፦ ለምሳሌ በወቅቱ ከቤተሰባችው ጋር ተለያይተው ኢትዮጵያ ውስጥ የቀሩ ወገኖችን ችግሮች እንዲፈቱ አድርገናል፡፡የመብት ጥያቄዎችንም አንስተን በተለይም የአንድ ህብረተሰብ የእድገት መሰረት ቁልፉ ትምህርት በመሆኑ

ማህበረሰባችን የትምህርት እድል እንዲያገኝ ጥረት አድርገናል፡፡እንደሚታወቀው የኛ ማህበረሰብ   ከገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሄደ ስለሆነ የትምህርት መብት እንዲያገኝ በሀገሪቱ ላይ በተለይ በወሳኝ መንግስታዊ አመራሮች ላይ ተጽዕኖ እናደርግ ነበር፤    የፓርላማ አባላቱም በሚኒስትሮች ምክር ቤትም ከፍተኛ ተጽዕኖ እናደርግ ነበር፡፡

ቁም ነገር፦ ተጽዕኖ ሲሉ ምን አይነት?

አምባሳደር አብርሃም፦ ለምሳሌ  የሀገሪቱን  ዲሞክራሲያዊ  ሰርዓት መሰረት በማድረግ ሰላማዊ ሰልፍ የምናዘጋጅበት ጊዜ ነበር፡፡  ለከፍተኛው ፍርድ ቤት አቤቱታ ተፈራርመን እናቀርብ  ነበር፡፡ ያም በመንግስት ላይ  ፖለቲካዊ ተጽዕኖ ያደርግ ነበር፡፡  ይሄንን ካልረዳኸን በምርጫ ጊዜ አንመርጥህም በማለት መብታችንን እንጠይቅ ነበር፡፡    ሎቢም (የማግባባት ስራ) እንሰራ  ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ  የማህበረሰባችን ገጽታ ሊቀየር ችሏል፡፡በተለይ  በትምህርት መስክ  መንግስት ቅድሚያ  በመስጠት የትምህርት በጀትን በመመደብ ልዩ ድጋፍ በማድረግ ለማህበረሰባችን  በጥሩ ሁኔታ ከማህበረሰቡ ጋር እንዲዋሃድ ማድረግ ችለናል፡፡

ቁም ነገር፦  ወደ ፖሊቲካወ ዓለምስ እንዴት ገቡ?

አምባሳደር አብርሃም፦ ይህ አቅም ነው ወደ ፖለቲካው ዓለም እንድገባ በር የከፈተው፡፡ የሶሻል አክቲቪስትነቱ  ነው  ወደ ፖለቲካው የመራኝ ለማለት እችላለሁ፡፡እናም  የአንጋፋዉ የእስራኤል የፖለቲካ ፓርቲ ሊ ኩ ድ ፖርቲ  አባል መሆን ቻልኩ፡፡  በፓርቲው ዉስጥ ተወዳድሬ በፓርቲው ቅድሚያ ውድድር ላይ ቀርቤ  አፈላጊውን ቁጥር አግኝቼ ወደ ፓርላማ ገባዉ፡፡  በፓርላማው  ዉስጥም       የአዲስ ስደተኛ ገቢዎች ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆኜ አገልግያለሁ፡፡

ቁም ነገር፦ ለስንት አመት?

አምባሳደር አብርሃም፦ለአራት አመት  ነው የሰራሁት፡፡ ከአራት አመት በኋላ ደጋሚ ተወዳድሬ በቂ ቁጥር ስላላገኘሁ አልተመረጥኩም፡፡ ሆኖም  የጠቅላይ   ሚኒስተሩ አማካሪ በመሆን በጠቅላይ ሚኒስተሩ ቢሮ ስሰራ  ከቆየሁ በኋላ አሁን    ደግሞ  ተወልጄ ባደኩበት የእውቀት ምንጭ ከቀዳሁባት  ወደ ኢትዮጵያ  በአምባሳደርነት  የሁለቱን ሀገሮች ግንኙነት  ታጠናክራለህ በማለት በአምባሳደርነት  ተመድቤ የኢትዮጵያና የአፍሪካ ህብረት  አምባሳደር ሆኜ በመስራት ላይ እገኛለሁ፡፡

ቁም ነገር፦ ይሄ የመጀመሪያ ተልእኮዎ ነው ማለት ነው በአምባሳደርነት?

አምባሳደር አብርሃም፦ ትክክል የመጀመሪያዬ ነው፡፡

ቁም ነገር፦  ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል እንደ እርስዎ አይነት ለሄደ ሰው በእስራኤል ፖለቲካ ውስጥ መግባት ምን ያህል ፈታኝ ነው?

አምባሳደር አብርሃም፦ ፈተና አለው፤ ግን ፈተናውን የመቋቋምና የማለፍ ሁኔታ እንደግለሰቡ ይለያያል፡፡ ቀላል  አይደለም፤ ብዙ መሰናክሎች አሉ፤ ችሎታን እና ትእግስትን ይጠይቃል፡፡  እኔ ወደ ፓርላማ  የገባሁ ከአራት ጊዜ የምርጫ ሙከራ በኋላ ነው፤

ቁም ነገር፦ ይሄ ነው የራስዎን የፓለቲካ ፓርቲ ለማቋቋም ምክንያት የሆኖት ለማለት ይቻላል?

አምባሳደር አብርሃም፦ ትክክል፤ ሁለት፤ ሶስት ጊዜ ከሞከርኩ በኋላ ለምን የራሴን ፓርቲ አላቋቋምም በሚል ነው ለመጀመሪያ ጊዜ ከኢትዮጵያ ውጪ በኢትዮጵያዊ የሚመራ የፖለቲካ ፓርቲ ያቋቋምኩት፡፡ ምክንያቱም ሃይሌን ማሳየት ፈለግኩ፤ ብዙ ጊዜ በፖለቲካ ምርጫ ጊዜ የእኛ ማህበረሰቦችን የሚወክሉ ሰዎች  በተለያየ ፓርቲ ተበታትነው ስለሚገቡ ያሉት ጥቂት ድምዖችን ይከፋፈላሉ፡፡  ይሄን መሰለ አስተያየት ስላለ ያንን መስበር አለብኝ በሚል የኢትዮጵያ ፓርቲ በሚል አቋቋሜ  በ2006 እኤአ ተወዳድሪያለሁ፡፡

ቁም ነገር፦ ውጤቱስ ?

በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ክቡር አምባሳደር አብርሃም ንጉሴ ከጋዜጠኞች ጋር

አምባሳደር አብርሃም፦ ውጤቱ እንደጠበቅሁት አልነበረም፤ ወደ ፓርላማው ለመግባት  ትንሽ ቁጥር ጎደለኝ፡፡ነገር ግን  ሂደቱ ለሌሎች ፓርቲዎች ትልቅ ትምህርት የስጠ ስልነበረ ነው አንጋፋው ሊኩድ ፓርቲ እኛ ጋር ግባ ብሎ  የጋበዘኝና የገባሁት፡፡በነገራችን ላይ ፓርላማ በመግባት እኔ የመጀመሪያ አይደለሁም፤  ከእኔም በፊት፤ ከእኔም በኋላ ከእኛ ማህበረሰብ በፓርላማ አባልነት የገቡ አሉ፤በአሁኑ ሰአትም  ሶስት የማህበረሰባችን ተወካዮች በፓርላማ ውስጥ  አሉ፡፡

ቁም ነገር፦   ቤተ እስራኤልያን እንግዲህ ከ100  በላይ ሀገሮች ውስጥ ተበታትነው የነበሩ ህዝቦች ናችው፤ እና ከዚያ ተሰባስበው ነው እስራኤልን መመስረት የቻሉት፤እና በተለያየ ሀገር ውስጥ ኖሮ ከዚያ በኋላ ተሰባስበው ለአንድ አላማ በመቆም  ሀገርን መስራት ከእስራኤል  ምን እንማራለን?

አምባሳደር አብርሃም፦ እንደሚታወቀው በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ጀምሮ በስደት የኖረ ህዝብ ነው የአእስራኤል ህዝብ፡፡በሙሴ መሪነት  ከግብጽ ባርነት ተመልሰው ለአብርሃም፤ ላይስሃቅ፤ ለያቆብ እግዚአብሄር ቃል የገባላችውን መሬት የወረሰ ህዝብ ነው፡፡በብዙ ነገስታትና መሳፍንት ሲገዙት ኖረዋል፡፡ታሪክ እንደሚነግረን ከሆነ መጀመሪያ  ያው ናቡከደነ ጽዎር፤ የባቢሎን መንግሥት፤ ከዚያ የፓሪስ መንግሥት፤ ከዚያ የግሪክ መንግሥት፤ የሮማ መንግሥት፤ የቱርክ መንግሥት ከዚያም መጨረሻ ላይ የእንግሊዝ ኢምፓየር ገዝተውታል፤  ከዚያ ከ1948 እኤአ ነው  ነፃ  ውጥተን ዘመናዊት እስራኤል የተመሰረተችው፡፡ እስከ 1948  በየሀገሩ በአራቱም ማዕዘን የተበተነ ህዝብ ነበር፡፡ በነብያት ትንቢት  <ከአራቱም ማዕዘን እሰባስባችሃለሁ  ፤ወደ አገራችሁ አመጣችኋለው፤ ካልሰራችሁበት ቤት ትገባላችሁ፤ ያልተከላችሁትን ወይንም ትበላላችሁ>  በማለት እግዚአብሄር የሰጠውን ቃል መሰረት በማድረግ ነው እስራኤላውያን ከመላው አለም የገቡት፡፡ይህንን  የተጻፈውን በመያዝ  እስራኤል ከተቋቋመችት ማለትም  ከ1948 በይፋ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እውቀና አግኝታ  ከከእንግሊዝ ነፃ  ስትወጣ እንደተባለው ከ100 በላይ ከሆኑ  አገራት   ተሰባስቦ የመሰረታት ሀገር ነች፡፡ ዛሬ ከምንም በላይ አንድ  ቤተሰብ ሆኖ እንደ አንድ ህዝብ ሆኖ የተለያየ ቀለም  ያለው፤ የተለያየ ቋንቋ የሚናገር፤ የተለያየ ባህል እና ወግ ያለው ነገር ግን በእስራኤል ሀገር አንድ አቋም  በመያዝ ሉዋላዊነቱን በማስከበር እስከዛሬ  አንድ ጠንካራ የማህበረሰብ ለመፍጠር ችሏል፡፡ ይሄን ደግሞ ዝም ብሎ የመጣ ሳይሆን የቃል ኪዳን ሀገር ስለሆነ ነው፡፡ያስተሳሰረውም የህልውና ሁኔታ ነው፡፡ እስራኤል እንግዲህ የምትገኘው ህልውናዋን ባልትቀበሉ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት መሃል ነው፡፡ እስራኤል በተቋቋመች በአመቱ በ1949 ሊያጠፏት ጦር አዝምተውባት ነበር፡፡ አልቻሉም፡፡ በ1967ም በስድስቱ ቀን ጦርነት እንዲሁም በ1973ቱ የኩዩፑድ ጦርነት በአንድ ላይ በመቆም መመከት ችላለች፡፡ሚስጥሩ አንድ ነው፤ በጣም ትንሽ ህዝብ ቢሆንም አንድ ሆኖ መቆም ካልቻለ ድጋሚ ወደ ስደት ሊሄድ እንደሚችል በማመን የሃሳብ ልዩነት ቢኖር ሃሳቡን በዲሞክራሲ ሂደት ውስጥ በድምፅ በልጫ ብቻ በዲሞክራሲ ምርጫ እያደረገ ህልውናውን ግን በአንድነት ማስጠበቅ የቻለ ህዝብ ነው፡፡ ጦር ሲመጣ ሁሉም አንድ ሆኖ የሚቆም እና ጠንካራ  የምጣኔ ሃብትና  ጠንካራ መከላከያ ሃይልም ሊፈጥር የቻለው በአንድነት በመቆሙ ነው፡፡ልጆቻችን አስራ ስምንት አመት እንደሞላቸው ወደ ብሄራዊ ውትድርና ይገባሉ፡፤  ሽብር ፈጣሪዎች እና ሌሎችም ኃይሎች ለመመከትና ሉዋላዊታችንን ለማረጋግጥ፤ ይሄ ሁሉ ሲሆን  እንደ እኔ እምነት ከሆነ መለኮታዊ ኃይል አለ ብለን እናምናለን፡፡  በዚህ ዓለም የእግዚአብሔርን ኃይል አለ፡፡  በዚህ ዓለም ላይ  እውቀት እና ጥበብን የሚሰጥ እግዚአብሔር ነው፡፡ ምድረ በዳውን  አረንጓዴ የሚያደርግ ቴክኖሎጂን ለመፍጠር፤ በመከላከያ ኃይሉም በቁጥር አምስት መቶ ሚሳኤል ሲተኮስ በሰማይ ላይ መመከት የሚችል መከላከያ ለመገንባት የእግዚአብሄር ሀይል ያስፈልጋል ብለን እናምናለን፡፡

ቁም ነገር፦ በቱሪዝም ዘርፍ ላይ እስራኤል እንግዲህ በርካታ የሚጎበኙ ቦታዎች ያሏት አገር ነች፤ በየአመቱ  በሚሊዮን የሚቆጠሩ የተለያየ እምነት ተከታዮች ይመጣሉ፤ ሂደቱ በጦርነት ውስጥም የማይቀረጥ መሆኑ   እንዴት ሊሆን ቻለ?

አምባሳደር አብርሃም፦  እንግዲህ እንደሚታወቀው  እስራኤል የሶስቱ ጥንታዊ ሃይማኖቶች መነሻ ናት፤ ማለትም የአይሁድ ወይም የእስራኤል ሃይማኖት ከዚያ ቀጥሎ ክርስትና ከክርስትና ቀጥሎ ደግሞ እስልምና መነሻ ናት፡፡ የሶስቱም ሀይማኖቶች ታሪካዊ  ቦታዎች በእስራኤል ሀገር ላይ ይገኛሉ፡፡በዚህ ሂደት ላይ  የተለያዩ በክርስትና ሀይማኖት ውስጥ የተለያዩ ዲኖሚኔሽን ወይም የተለያዩ የሀይማኖት ክፍፍሎች  አሉ’ ካቶሊክ፤ ኦርቶዶክስ ፕሮቴስታንት አሉ፡፡ ግን  ሁሉም  እያንዳንዳቸው በእምነታቸውና በሀይማኖታቸው የእስራኤል መንግስት  ዲሞክራሲያዊ በመሆኑ  ሁሉም የራሱን የሀይማኖት አምልኮ የመከተል መብቱ የተጠበቀ ነው፡፡ የየሀይማኖቱ ቅዱስ ቦታዎች ሁሉም የተጠበቁ ናቸው፡፡ የካቶሊክም በካቶሊክነቱ፤ የኦርቶዶክስም በኦርቶዶክስነቱ፤ ፕሮቴስታንትም በፕሮቴስታንነቱ፤ እንዲሁም  ሙስሊሞችም በሙስሊምነታቸው  እነዚህ ቦታዎች ሁሉ የተከበሩ ናቸው፡፡  ስለሆነ መንግስት   ህግን ከማስከበር በቀር በዚህ ጣልቃ ስለማይገባ  በአለም ላይ ያሉ የሀይማኖት ተከታዮች ሁሉ ይመጣሉ፡፡  እንደውም ከሶስቱ ሀይማኖቶች በተጨማሪ የባሃይ   እምነት ተከታዮችም ሃይፋ ከተማ ላይ ቆንጆ የሆነ የሚጎበኝ ቦታ አላቸው፡፡ እና እስራኤል ሁሉንም ሀይማኖት የምታከብር  ነጻ ዲሞክራሲ ሀገር ናት፡፡ ምናልባትም ከመካከለኛው ምስራቅ ብቸኛዋ ዲሞክራሲያዊ ሀገር ናት ብል ማጋነን አይሆንብኝም፡፡ በዚህ ሂደት ላይ በአለም ላይ ያሉ አማኞች ወደ እስራኤል ይመጣሉ፡፡ ጦርነትን አይፈሩም፤ ለምሳሌ በሰማይ ላይ የኢራን፤ የየመን፤ የሁቲ ፤የሀማስ ፤የሂዝቦላ ሮኬት እና ሚሳይሎች እየተተኮሱ  እንኳን የሚመጡ ቱሪስት አላቆሙም፡፡የኢትዮጵያ ህዝብም መምጣቱን አላቆመም፡፡ በዚሀ ረገድ የኢትዮጵያና የእስራኤልን ወዳጅነት የተለየ የሚያደርገውም ሁለት መሰረታዊ ምስሶች አሉ፡፡ አንደኛ የኢትዮጵያ ቤተ እስራኤሎች ለብዙ ሺህ አመታት በአብሮነት በኢትዮጵያ መሬት ላይ አሁንም ያሉ ሲሆን እስራኤል ደግሞ ከ180 ሺህ ያላነሱ ቤተ እስራኤላውያን ማህበረሰብ በእስራኤል ሀገር ውስጥ ትንሽቱን ኢትዮጵያን መፍጠር ችለዋል፡፡ በእስራኤል ውስጥ ባህላችን እንጀራና ወጡ ፤ ጠላውና ጠጁ፤ አልባሳቱ፤ ሙዚቃው እነዚህ ሁሉ በእስራኤል ሀገር ላይ ኢትዮጵያን ያለን የሚያስመስለን ነገር ነው፡፡   በተጨማሪ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ወላጆቻቸው አያት ቅድመ አያት የኖሩበትን ለብዙ ሺህ አመታት አባቶቻችን የኖሩበትን አካባቢ  መንደር ለማግኘት የመካነ መቃብር ቦታዎችን ለማስከበር ይመጣሉ፡፡ እረፍት ሲሆን ወደ አውሮፓ ወይም ወደ አሜሪካ አይደለም የምንሄደው፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ እስራኤል ወደዚህ ነው የሚመጡት፤ ምክንያቱም በባህሉ በቋንቋው በምግቡ ተዝናንቶ በሙዚቃው ተዝናንቶ መሄድ ነው የሚፈልገው፡፡  ይሄ ሁኔታ ሁለቱም ሀገሮች  ልዩ ያደርጋቸዋል፡፡ ሌላው ምስሶ ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከሰባት ያላነሱ አብያተ ክርስቲያናት እና ገዳማት አላት፡፡  ኢትዮጵያ በአእስራኤል ንብረት ያላት ብቸኛዋ ጥቁር ሀገር ነች፡፡  እና ይሄ ንብረት መኖሩ ብዙ ካህናት እና ብዙ መነኮሳት ንብረቱንም በመጠበቅ አገልግሎትን አብያተ ክርስቲያናት በመጠበቅ በዚያ ይኖራሉ፡፡ በየጊዜው የሚሄዱ ምእመናንም አሉ፤ በተለይ በልደትና በ ትንሳኤ በጣም ይበዛል፡፡ በመሀከሉም ይሄዳል ፤ጦርነት እያለ የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ቀን አላቆመም ወደ እስራኤል መሄድ፡፡ ሌላው እስራኤል ለመሄድ  ሶስተኛው እድል የኢትዮጵያ አየር መንገድ መኖር ነው፡፡የኢትዮጵያ አየር መንገድ  በቀን ሁለት እና ሶስት ጊዜ እየሞላ ነው ከቦሌ ወደ ቴላቪቭ የሚሄደው፡፡  ይህ ሁኔታ ደግሞ የቱሪዝምን ሁኔታ እጅግ በጣም ሊያጠናክረው ይችላል፤ የንግድና ኢንቨስትመንትን ያሳድጋል፡፡ በዚህ ረገድ በኮቪድ ወቅት  የእስራኤል ኤር ክራፍት ኢንዱስትሪ ባለሙያዎች  የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአውሮፕላኖችን  ወደ ካርጎ ፕሌን በመቀየር ተሳትፎ አድርገዋል፡፡ከኢትዮጵያ እስራኤል ምርቶችን ለመጫን በባህር ከመዞር በአራት ሰዓት ውስጥ ጤፉም ቡናውም ሰሊጡም ሌላም ጥራጥሬዎች ሆነ የአልባሳትም ሁሉ በአንዴ ወደ እስራኤል፤ከእስራኤልም  የተለያዩ ምርቶች ወደ ኢትዮጵያ በማስገባት ንግዱን እያቀላጠፉ ነው፡፡

ቁም ነገር፦ እንደጠቀሱት በእስራኤል የኢትዮጵያ ይዞታዎች እንዳሉ ይታወቃል፤ ከዴር ሱልጣን ገዳም ጋር በተያያዘ ግን ከግብፆች ጋር ያለው የይገባኛል ጥያቄ አሁንም ድረስ አልተፈታምና፤ በምን መልኩ የኢትዮጵያን ታሪካዊ ይዞታ ማረጋገጥ ይቻላል ይላሉ?

አምባሳደር አብርሃም፦ እርግጥ ነው የይዞታ ጉዳይ ነው፤ ይህ ችግር ቀደም ሲል የፓርላማ አባል በነበርኩበት ጊዜ ጀምሮ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡በመንግስት ደረጃ ይታወቃል ችግሩ፡፡ የዛሬ ሁለት ሳምንትም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ የተመራ የልዑካን ቡድን ወደ እስራኤል ሄዶ ነበር፡፡ እኔም በዚያ የልዑካን ቡድን ውስጥ ነበርኩ፡፡ጉብኝት አድርገናል፡፡ ቦታውን አይተናል፡፡የመነኮሳቱን ሁኔታና ሃሳባቸውንም ሰምተናል፡፡ይህ ችግር ዘለግ ያሉ ጊዜ የወሰደ ጭቅጭቅ ያለበት ቦታ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ግብፆች የእኛ ይዞታ ነው ይላሉ፤ ኢትዮጵያውያን ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያንና የኢትዮጵያ ህዝብ ንብረት ነው የሚሉት፡፡ ቸግሩ  ብዙ ጊዜ ወስዷል፤ እንግዲህ  እስራኤል የዲሞክራሲ ሀገር እንደመሆኗ  በየአራት አመቱ ምርጫ አለ፤ መንግስት ይቀየራል፡፡ በዚህ የተነሳ ችግሩ  በፖለቲካ ደረጃ የሚወሰን ሳይሆን በፍርድ ቤት የሚወሰን ነው ብለን ነው የምናምነው፡፡  ምክንያቱም ጥያቄው የይዞታ ይገባኛል ስለሆነ ብዙ ጊዜ የሚረጋገጠውና የሚታየው በፍርድ ቤት መስመር ውስጥ በተጨባጭ ማስረጃ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት ታሪኩ ሰፊ ነው፤ በእየሩሳሌም ላይ ብዙ ነገሥታት ተፈራርቀውባታል፤ ከናቡ ከደነ ጾር አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ብዙ ያለፉት አስተዳዳሪዎች ነበሩ፡፡ የቱርኮች አመራር እየጠናከረ በነበረበት ሁኔታም  እየሩሳሌም በሙስሊም ገዢዎች ለጊዜው  ተይዞ እንደነበረ በታሪክ ውስጥ አለ ፤እንግዲህ በዚያን ጊዜ ተቀብለናል ነው የሚሉት ግብፆች፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ደግሞ በንጉሥ ሰለሞን ጊዜ ሰለሞን ለንግስት ሳባ የሰጣት ቦታ ነው ይላሉ፡፡ ይሄ የንብረት ጥያቄ ነውና የእስራኤል መንግስት ፖሊሲው  የማንኛውም ውዝግብ  በፍርድ ቤት እስካልተረጋገጠ ድረስ እያንዳንዱ የያዘውን ይዞ  የመቀጠል ፖሊሲ ወይም ስታትስኮ  በሚለው ባለው ይርጋ ፤ባለው ይጽና ነው፡፡

ቁም ነገር፡- ግን እኮ ገዳሙ እየፈረሰ እድሳት እንኳ ለማድረግ አልተቻለም እያሉ ነው መነኮሳቱ?

አምባሳደር አብርሃም፦ ትክክል ነው፤ አሁን አንዳንድ መነኮሳት እንደገለጹት  የመፍረስ ሁኔታ ሰላለ ጥገና ያስፈለገዋል ብለዋል፡፡ አይተነዋል፤  የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ለማደስ ስትፈለግ  ግብፆች  ተቃውሞ ያቀርባሉ፤ ምክንያቱም ጥገናውን ካደረጉ ካደሱ ይዞታቸው ጸና ማለት ነው በሚል በዚህ ሁኔታ ነው ውዝግቡ፡፡ በመሆኑም እኔ የፓርላማ አባል በነበርኩበት ወቅት የተሰጠው  አንድ መፍትሄ የእስራኤል መንግስት ገዳሙን ያሳድስና ይዞታው የእከሌ ነው ተብሎ በፍርድ ቤት የተወሰነ ጊዜ ያወጣውን ይቀበላል የሚል ነው፡፡ እስካሁን እኔ እስከማውቀው ድረስ ይሄ ሁኔታ በፍርድ ቤት እልባት ያገኘው ጉዳይ አይደለም፡፡

ቁም ነገር፡-   ቀደም ሲል  እንደገለጹት  በኢኮኖሚም  በትምህርትም በተሻለ ደረጃ ላይ የደረሱ ብዙ ቤተ እስኤላውያን እንዳሉ ይታወቃል፤ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ እንደው ምን ያህል ተሳትፎ እያደረጉ ነው ማለት ይቻላል? በኢንቨስትመንቱ ላይ? ፤ ሪሚታንሰ በመላክ በኩልስ ምን ያህል አበረታች ነው?

አምባሳደር አብርሃም፦ የኢትዮጵያ ቤተ እስራኤል ማህበረሰብ በሁለቱ ሀገሮች ያለውን ግንኙነት በማጠናከር ላይ ይገኛሉ፡፡ በኢኮኖሚውም በቱሪዝምም፤ በትምህርትም፤ በባህልም  በማጠናከር ላይ  ይገኛሉ፡፡በኢኮኖሚ አንፃር ማህበረሰባችን ያው ወደ እስራኤል እግሩ ከገባበት ጊዜ አንስቶ በተለይ በትምህርት  ራሱን ለማስተማርና  ልጆቹን ከማህብረተሰቡ ጋር ለማዋሃድ በጣም ትልቅ ጥረት ሲያደርግ በመቆየቱ ብዙ ሃብታሞችን አፍርተናል ለማለት አልችልም፤ ነገር ግን በተወሰነ ደረጃ  የወጡ ባለሃብቶች አሉ፡፡ከነሱ መካከል  ብዙዎቹ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣታቸው የልማት ተሳታፊ ሆነዋል፤ በተለይ  በእርሻው፤በንግድ፤ በግብርናና በቴክኖሎጂ ጥሩ ተሳትፎ አላቸው፡፡ የኛ ማህበረሰብ ሰዎች በግንባር ቀደምትነት የሚሰሩት ስራ እንደተጠበቀ ሆኖ ካፒታል ካላቸው እስራኤሎች ጋር በአንድ ላይ በመጣመር ጆይንት ቬንቸር በመፍጠር ፋብሪካ የከፈቱ አሉ፤ በእርሻ ስራ ላይ፤ በጤናው ዘርፍም የተሰማሩ ብዙ አሉ፡፡ ኤምባሲያችን ይህንን ግንኙነት ለማጠናከር በአራት መልኩ ነው የሚንቀሳቀሰው፡፡ የመጀመሪው የመንግስት ለመንግስት ወይም G2G ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂን በተመለከተ ልዩ ልዩ  ፕሮግራሞች አሉን፡፡ አዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲን፤ ብሔራዊ ባንከንና ገንዘብ ሚንስቴር መስሪያ ቤቱን እንዲሁም የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራምን  ያሳተፉ የተለያዩ ፕሮግራሞችን አሉን፡፡ በእርሻው በኩል እስራኤላውያን በጠብታ መስኖ እርሻ የታወቅን በመሆኑ ያንን በተግባር እየሰራንበት ነው፡፡ ሁለተኛው ግንኙነት ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት ባለሃብቶች ወደ ኢትዪጵያ መጥተው ሃብታቸውን እንዲያፈሱ ብዙ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ ሶስተኛው ዘርፍ መንግስታዊ ልሆኑ ድርጅቶች በልዩ ልዩ የበጎ አድራጎት ተግባራት ላይ  እየሰሩ ነው፡፡ በተለይ በጤናው ዘርፍ ጎልቶ የሚጠቀስ እንቅስቃሴ ተደርጓል፡፡ ለምሳሌ ያህል ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ጋር በመተባባር ለህፃናትና ለአዋቂዎች የልብ ቀዶ ጥገና የሚሰጡ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ በመምጣት ህክምና በነፃ ሰጥተዋል፡፡   ኦፕሬሽን ኢትዮጵያ የሚባለው የእስራኤል ድርጅት  በየ ሶስት ወሩ እየተመላለሰ የአይን ቀዶ ጥገና የሚያደርጉ ባለሙያዎች አሉት፡፡ በጳውሎስ ሆስፒታል፤ በምንሊክ፤ በመቀሌ፤ ባህር ዳር ፤ ጎንደር በደሴ ሆስፒታሎች ተገኝተው የብዙዎችን ብርሃን መልሰዋል፡፡ በዚህ ሁሉ ፕሮጀክቶች ውስጥ ቤተ እስራኤላውያን አብረው አሉ፡፡ ያለ ጊዜያቸው የሚወለዱ ህፃናትን የሞት  ቁጥር ለመቀነስም ከአለርት ሆስፒታል ጋር በመጣመር በቴክኖሎጂ የታገዘ ህክምና ይሰጣል፡፡ከአሜሪካ ጂዊሽ ኮሚኒቲ የተሰባሰበ የገንዘብ እርዳታም በጤና ጥበቃ ሚኒሰቴር በኩል በተፈጥሮና በጦርነት ሳቢያ አካላቸው ለጎደሉ ዜጎች የመሳሪያ ድጋፍ ሁሉ ተደርጓል፡፡ በግብርናው ዘርፍም አነስተኛ ማሳ ላላቸውን አርሶ አደሮችን በቴክኖሎጂ የታገዘ ድጋፍ የሚያደርጉ አሉ፡፡

በማዕድን ዘርፍም ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሃብት የታደለች ሀገር ስለሆነች ይህንን የሚደሰሩ የእስራኤል ድርጅቶች በተለይ በወርቅ ማውጣት ስራ ላይ በደቡብ ክልል ስራ እየሰሩ ነው፡፡ፖታሲየምና ፎስፈረስን የመሳሰሉ ማዕድናትን የሚያወጡ የእስራኤል ኩባንያዎች አሉ፡፡ በቂ ነው ባልልም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ባወጣው መረጃ መሰረት ከ100 በላይ የእስራኤል ኩባንያዎች ፈቃድ ወስደው በኢትዮጵያ ውስጥ በልዩ ልዩ የልማት ስራዎች ላይ እየተሳተፉ ነው፡፡ አራተኛው ዘርፍ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ላይ  የተመሰረተ የባህል ግንኙነት ነው፡፡ ብዙ ጎብኝዎች ወደ እዚያ ይመጣሉ፤ ከዚያም ወደ እዚህ ይመጣሉ፡፡ ይህንን አጠናክረን ማስኬድ እንፈልጋለን፡፡

ቁም ነገር፦ ሰሞኑን በአንዳንድ የማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድና ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንኒያምን ኔታንያሁ በስልክ መነጋገራቸውን በመጥቀስ እስራኤል የኢትዮጵያን ወደብ የማግኘት እቅድ ኔታንያሁ ስለመደገፋቸው ተዘግቦ ተመልክተናልና ሊያረጋግጡልን ይችላሉ?

አምባሳደር አብርሃም፦  እኔ በመሠረቱ ይህንን ማረጋገጥም አልችልም ፣ መቃወምም አልችልም፤ ምክንያቱም እንደ እናንተ በሶሻል ሚዲያ  ከመስማት በቀር ሌላ የማውቀው  ነገር ስለሌለ መናገር  አልችልም፡፡   ምክንያቱም ይሄ ተሳተፍኩበት አይደለም ወይም ደግሞ ሆኗል ተብሎ የተሰጠኝ መመሪያ የለም፡፡

ቁም ነገር፦  ኢትዮጵያ አሁን በሰላማዊ መንገድ የባህር በር የማግኘት ፍላጎት እንዳለት በመንግስት በኩል ተገልጿል እና እስራኤል ይሄንን በተመለከተ  ምን አቋም አላት?

አምባሳደር አብርሃም፦  እንግዲህ ይሄን በተመለከተ በኢትዮጵያ መንግስት ጥያቄ ቀርቦ በእስራኤል ካቢኔና መንግስት በኩል የተደረገ ወይይት  እኔ የማውቀው የለም ። እንደ አንድ  ኢትዮጵያዊ  እስራኤላዊያን ግን  ማንኛውም በሰላም እና በዲፕሎማሲ መልክ የሚገኝ ነገር ሁሉ ተቀባይነት አለው ብዬ አምናለሁ፡፡ በመንግስት ደረጃ ግን የቀረበም ጥያቄ የለም ።

ቁም ነገር፦  በቅርቡ ከተወዳጁ አርቲስት ቴዲ አፍሮ ጋር እዚህ ኤምባሲ መጥቶ ግንኙነት ማድረጋችሁን በሶሻል ሚዲያ  ላይ  ተመልክተናልና ምን ተነጋገራችሁ?

አምባሳደር አብርሃም፦ እንግዲህ ቀደም ብዬ እንደተጠቀስኩት ይሄ ኤምባሲያችን በአራት አይነት መስመር ግንኙነት እና አገልግሎት እንሰራለን ብያለሁ፡፡ ከዚህ መካከል አንዱ ያው ህዝብ ለህዝብ የሚለው ፕሮግራም ነው፡፡ በዚህ ሂደት ላይ ደግሞ ብዙ የምናገኛቸው የአርቲስት ቡድኖች ደራሲያኖች አሉ፡፡ ከኢትዮጵያ ደራሲያኖች ጋር ግንኙነት እናደርጋለን፡፡  ምክንያቱም  የባህሉን መተሳሰር እንፈልገዋለን፡፡ ከዚህ አንፃር ከዝነኛው ድምፃዊ ቴዲ አፍሮ ጋር እዚህ ኤምባሲያችን ተገናኝተን ከእሱም ከባለቤቱም ጋር ተነጋግረናል፡፡ የተነጋገርነው በእርሱ ሙዚቃና ስራዎቹ ዙሪያ ነው፡፡ በእስራኤል ብዙ ህዝብ በተለይ የኢትዮጵያ ቤተ እስራኤል የእሱን ሙዚቃ የእሱን ድምፅ አድናቂ ነው፡፡ በተለይ ወጣቱ ትውልድ በጣም አድናቂው ነው፡፡ እናም ይሄም ሁኔታ እንግዲህ በሁለቱ አገሮች መካከል እና በሁለቱ ህዝቦች መካከል ያለውን ሁኔታ የበለጠ ያጠናክረዋል በሚል በሙዚቃ ሰበብ ነው የተነጋገርነው እንጂ ሌላ  አጀንዳ ውስጥ አልገባንም፤ አጀንዳችን ባህል በማጠናከር ላይ ነው፡፡

ቁም ነገር፦  እንደ አንድ ኢትዮጵያ ውስጥ ተወልዶ እንዳደገ ቤተ እስራኤላዊ እዚህ ባሎት ቆይታ ምን ለማሳካት እቅድ አልዎት?

አምባሳደር አብርሃም፦ በእውነቱ በብዙ ምኞት  አለኝ፡፡  እንግዲህ ሰው ይመኛል እግዚአብሔር ይፈጽማልና  ይሄንን ሀላፊነት በእስራኤል መንግስት በኩል ሲሰጠኝ  በደስታ የተቀበልኩት ታሪካዊ እድል ነው ብዬ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ተወልጄ ያደኩባትና እውቀት የቀሰምኩባት ሀገር ነች፡፡ የእኔ ህልም የእስራኤልን ቴክኖሎጂ ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት ትልቅ የኢኮኖሚ ልማት ማምጣት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ ወደ አፍሪካና ወደ ሌላው ዓለም ምርቶቿን ስትልክ ማየት ህልም አለኝ፡፡  ኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዋ አድጎና የአፍሪካ የኢኮኖሚ መሪ  ሀገር ሆና  ምርትዋን ወደ አፍሪካ ወደ አለም ኤክስፖርት የማድረግ ችሎታዋን እንዲጠናከር እፈልጋለሁ፡፡ እስራኤል በዚህ ሁሉ ጦርነቶች መሀል ኢኮኖሚያዋ ጠንካራ የሆነበት ምክንያት በቴክኖሎጂ በኩል ብዙ ስለተሰራ ነው እና ኢትዮጵያ ውስጥ  ያ ቴክኖሎጂ ቢመጣ እንደ እስራኤል ሀገር አያለፋም፡፡ እስራኤል ሀገር የውሃ ችግር አለ፤ ሜዲንትራንያን  ባህር አጠገብ ሆና  እንዴት የውሃ ችግር አለ? ሊባል ይችላል፡ ሜዲንትራንያ  ባህር ግን ጨዋማ ውሃ በመሆኑ ለእርሻ አይሆንም ፡፡ ለመጠጥም አይሆንም፤  ስለዚህ ችግር ብዙ ያስተምራልና እስራኤል ጨውን ጣፋጭ እንዲሆን የሚያደርግ ቴክኖሎጂ መፍጠር ችላለች፡፡ ሌላው ደግሞ  ዌስቲንግ ዋተር ወይም የተጠቀምንበትን ውሃ ሪሳይክልንግ በማድረግ ዘጠና ፐርሰንት እንደገና ጥቅም ላይ የሚያውል ቴክኖሎጂ አላት፡፡ እስራኤል ለግብርና የምትጠቀመው ሪሳይክልድ የሆነ  ዌስትድ ዋተር ነው፡፡ኢትዮጵያ ግን በተፈጥሮ የጠራ ውሃ ነው ያላት፡፡ ስለዚህ ሪኒውአል ኤነርጂውን ወደዚህ ከመጣ በዚያ ሪኒውአል ኤነርጂ ባህሩንም ሃይቁንም ወንዙንም እየሳብን በእስራኤል የጠብታ መስኖ  ከታረሰ ይሄ ለም አፈር በቀላሉ ብዙ ማምረት ይችላል፡፡  ይሄ  ደግሞ  እዚህ ደብረዘይት ሩቅ ሳንሄድ ተሞክሯል፤ የእስራኤል ካምፓኒዎች  ግሩም የሆነ ቴክኖሎጂ በማምጣት ችግኝ በማፍላት የኢትዮጵያ ገበሬዎች እያገዙ እንደ  ፓፓያ፤ አቮካዶ ያሉ ምርቶችን  ዛሬ ኢትዮጵያ በአውሮፓ ገበያ ላይ ኤክስፖርት የሚታደርግ  ሃገር ሆናለች፡፡  ይሄ አቮካዶ የእስራኤል ኢኒሼቲቭ ነው፡፡ ከእስራኤል  የመጣ  እና አሁንም ያለ ሂደት ነው፡፡ ሰሞኑን ሆልቲ ካልቸር የ ግብርና ሚኒስቴር ያዘጋጀው ኤግዚቢሽን  በመክፈቻው ሚሊኒየም አዳራሽ  ሄጄ ነበር፡፡ እያንዳንዱ ካምፓኒ ምርቱን የሚያሳይ አውደ ርዕይ አለው፡፡እና የእስራኤልን ካምፓኒዎች ብቻ ለማግኘት እና ለማነጋገር  ግማሽ ቀን ነው የፈጀብኝ፡፡  እና የኔ ህልም የእስራኤልን ያንን በረሃ  ምድረ ገነት  አረንጓዴ ያደርገውን ቴክኖሎጂ ወደዚህ በማምጣት ከኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብትዋ ጋር በማገናኘት ኢትዮጵያ  ከአፍሪካ  በምጣኔ ሀብት ጠንካራ መሪ ሀገር እንድትሆን ይሄ ምኞቴ ነው። በትክክልም አሁን ያለው የኢኮኖሚ ሪፎርም የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ፤ ካፒታል ማርኬቲት  እንዲሁም ባንኪንግ ሲስተም ላይ የታቀደው ለውጭ ሃለሃብቶች ክፍት የማድረግ እቅድ ከእስራኤል የኢኮኖሚ  ፖሊሲ ጋር አብረው የሚሄዱ ናቸው። ስለዚህ  ባለፈው ጉብኝታችን ክቡር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ጌዲዮን በመሩት ልዑካን የነበረው ሂደት ይሄንን ሁኔታ የሚያጠናክር ነው። ብዙ የእስራኤል ሀብታሞች የድርጅት ካምፓኒ መሪዎች የሚገኙበት ታላቅ የራት ግብዣ በእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተዘጋጀ  መድረክ ላይ ካሁን በፊት    ለፕራይቬት ኢንቨስተርስ መሰናክል የነበሩ እና ዲስካሬጅ የሚያደርጉ የነበሩት አሰራሮች አሁን ተለውጠው የሚያበረታቱ  ናቸው ተብሏል፡፡  አሁን ያን የሰሙ ካምፓኒዎች እየመጡ ነው።  ወደፊቱም ደግሞ ለመምጣት የሚዘጋጁ አሉ።  ሌላ ሀገር አንመልከት ነው የምለው። መሰረቱ ተጥሏል ማሳደግ ማብዛት ነው፤ 100 ካምፓኒዎች ያሉትን  300 ካምፓኒዎች እንዲገቡ ማድረግ ነው።  በዚህ አይነት ሁኔታ ህልሜ እውን ይሆናል ብዬ አምናለሁ፡፡

ቁም ነገር፦   ቤተ እስኤላውያን  እዚህ ሀገር የቀሩ እንዳሉ ይነገራል፤ የእስራኤል መንግስት ደግሞ  ወስጄ ጨርሻለሁ የሚል አቋም ይዞ ነበረና  የቀሩ ቤተ እስራኤላውያን የመሄድ እድል ይኖራቸዋል?

አምባሳደር አብርሃም፦ ከዚህ በኋላ አዎ  በትክክል፡፡ ዛሬ እዚህ በኢትዮጵያ ብዙ ወገኖቻችን አሉ፡፡ እነዚህም ወገኖቻችን ደግሞ በዘር በትውልድ የተያያዙ ስለሆነ  ወደ እስራኤል ሃገር ይሄዳሉ ብዬ እኔ አምናለሁ፡፡ ግን ይሄን የሚወስነው የእስራኤል መንግስት ነው፡፡ ምክንያቱም አሁንም ቢሆን እየሄዱ ናቸው፡፡ በእስራኤል መንግስት በኩል መብት አላቸው ተብሎ የተወሰነላቸው አሁንም በየጊዜው እየሄዱ ናቸው፡፡ አሁንም ደግሞ ለመሄድ በመዘጋጀት ላይ ያሉ አሉ፡፡ ምክንያቱም ዘ ሎው ኦፍ ሪተርን ወይም የመመለስ ህግ አለ፡፡ ዘ ሎው ኦፍ ኢንትሪ የሚል ህግም አለ፡፡ እነዚህ ሁለት ህጎች መሰረት ናቸው፡፡ ዘ ሎው ኦፍ ሪተርን የሚለው ህግ ከውጭ ያሉ ዜጎችን የመመለስን ሁኔታ የሚመለከት ሲሆን ያን ህግ የሚያሟሉ አሁንም እየሄዱ ናቸው፡፡ባለፈው ወር 33 የሚሆኑ ኤርፖርት ድረስ ሸኝቻቸዋለሁ፡፡ እስከ ትናንትና ድረስ ከ50 ያላነሱ የመጣላቸው ፈቃድ ፕሮሰስ እያደረጉ አሉ፡፡  ሁለተኛው ዘ ሎው ኦፍ ኢንትሪ የሚለው ሁኔታ በመንግስቱ ውሳኔ የተመደበ ሆኖ የተወሰነ  ፋሚሊ ሪዩኒፊኬሽን ወይም ደግሞ የቤተሰብ ግንኙነት በሚል  የእስራኤል መንግስት ካሁን በፊት በተከታታይ ውሳኔዎችን ተወስኖ የሄዱ ወገኖቻችን አሉ። ግን አሁን ላይ  ማን ይሄዳል? ማን አይሄድም? ይሄን የሚወስነው  የእስራኤል መንግስት ነው። በዚህም የተነሳ ብዙ ሺህ ወገኖቻችን ወደ እስራኤል አገር መግባት ችለዋል። ይሄ ኮርቼ እምናገርበት ትልቅ  የእስራኤልን የዲሞክራሲ ሲስተም ወይም ዘዴ  ነው፡፡ ኤምባሲያችን በዚህ በኩል ስራውን አፋጥኖ የመስራት ሂደት ያደርጋል ብዬ አምናለሁ። ግን ኤምባሲው ወሳኝ አይደለም። አምባሳደር ወሳኝ አይደለም። አምባሳደር ተግባራዊ የሚያደርግ ነው። ይሄ የእስራኤል ካቢኔት የወሰነውን ውሳኔ በኤምባሲው በኩል ተግባራዊ ይሆናል።

ቁም ነገር፦ በነገራችን ላይ ከኢትዮጵያ ብቻ ነው ወይንስ አሁንም  ከሌሎች ሀገሮች  ከራሽያም ከሞሮኮ ቤተእስራኤላውያን አሁንም የመግባት ጥያቄዎች አሉ?

አምባሳደር አብርሃም፦  በአለም አቀፍ ደረጃ ያሉ  በየሀገሩ አሁንም ቢሆን በመሰባሰባ ላይ ነው ያለው። በጦርነትም ጊዜ ቢሆን ሁሉ ጦርነቱ አይበግራቸውም። በመሰባሰብ ላይ ያሉት ከራሽያም ከፈረንሳይም ከአሜሪካም በጠቅላላ ይመጣሉ፡፡

ቁም ነገር፦ በመጨረሻ  የሚያስተላልፉት መልእክት ካለ?

አምባሳደር አብርሃም፦  ለኢትዮጵያ ሰላምን እንመኛለን፤ አንድነትን እንመኛለን፤  እግዚአብሄር ለኢትዮጵያ ሰላምን ይስጥ፤ አንድነትን እና አብሮ መኖርን ወዳጅነትን መፈቃቀርን እንዲሰጥ የዘወትር ጸሎታችን ነው፡፡

ቁም ነገር፦ አመሰግናለሁ፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe